1ከነቢያትም፡ወገን፡ሚስቶች፡አንዲት፡ሴት።ባሌ፡ባሪያኽ፡ሞቷል፤ባሪያኽም፡እግዚአብሔርን፡ይፈራ፡እንደ፡ ነበረ፡አንተ፡ታውቃለኽ፤ባለዕዳ፡ልጆቼን፡ባሪያዎች፡አድርጎ፡ሊወስዳቸው፡መጥቷል፡ብላ፡ወደ፡ኤልሳዕ፡ ጮኸች።
2ኤልሳዕም፦አደርግልሽ፡ዘንድ፡ምን፡ትሻለሽ፧በቤትሽ፡ያለውን፡ንገሪኝ፡አላት።ርሷም፦ለእኔ፡ለባሪያኽ፡ ከዘይት፡ማሰሮ፡በቀር፡በቤቴ፡አንዳች፡የለኝም፡አለች። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
3ርሱም፦ኼደሽ፡ከጎረቤቶችሽ፡ዅሉ፡ከሜዳ፡ባዶ፡ማድጋዎችን፡ተዋሺ፤አታሳንሻቸውም፡አላት።
4ገብተሽም፡ከአንቺና፡ከልጆችሽ፡በዃላ፡በሩን፡ዝጊ፥ወደ፡እነዚህም፡ማድጋዎች፡ዅሉ፡ዘይቱን፡ ገልብጪ፤የሞላውንም፡ፈቀቅ፡አድርጊ፡አለ።
5እንዲሁም፡ከርሱ፡ኼዳ፡በሩን፡ከርሷና፡ከልጆቿ፡በዃላ፡ዘጋች፤እነርሱም፡ማድጋዎቹን፡ወደ፡ርሷ፡ ያመጡ፡ነበር፥ርሷም፡ትገለብጥ፡ነበር።
6ማድጋዎቹም፡በሞሉ፡ጊዜ፡ልጇን፦ደግሞም፡ማድጋ፡አምጣልኝ፡አለችው፤ርሱም፦ሌላ፡ማድጋ፡የለም፡ አላት፤ዘይቱም፡ቆመ።
7መጥታም፡ለእግዚአብሔር፡ሰው፡ነገረችው፤ርሱም፦ኼደሽ፡ዘይቱን፡ሽጪ፡ለባለዕዳውም፡ክፈዪ፤አንቺና፡ ልጆችሽም፡ከተረፈው፡ተመገቡ፡አለ።
8አንድ፡ቀንም፡እንዲህ፡ኾነ፤ኤልሳዕ፡ወደ፡ሱነም፡ዐለፈ፥በዚያም፡ታላቅ፡ሴት፡ነበረች፤እንጀራ፡ይበላ፡ ዘንድ፡የግድ፡አለችው፤በዚያም፡ባለፈ፡ቍጥር፡እንጀራ፡ሊበላ፡ወደዚያ፡ይገባ፡ነበር።
9ለባሏም፦ይህ፡በእኛ፡ዘንድ፡ዅልጊዜ፡የሚያልፈው፡ቅዱስ፡የእግዚአብሔር፡ሰው፡እንደ፡ኾነ፡ዐውቃለኹ።
10ትንሽ፡ቤት፡በሰገነቱ፡ላይ፡እንሥራ፤በዚያም፡ዐልጋ፡ጠረጴዛ፡ወንበርና፡መቅረዝ፡እናኑርለት፤ወደ፡ እኛም፡ሲመጣ፡ወደዚያ፡ይገባል፡አለችው።
11አንድ፡ቀንም፡ወደዚያ፡በመጣ፡ጊዜ፡ወደ፡ቤቱ፡ገብቶ፡በዚያ፡ዐረፈ።
12ሎሌውንም፡ግያዝን፦ይህችን፡ሱነማዊት፡ጥራ፡አለው።
13በጠራትም፡ጊዜ፡በፊቱ፡ቆመች።ርሱም፦እንሆ፥ይህን፡ዅሉ፡ዐሳብ፡ዐሰብሺልኝ፤አኹንስ፡ምን፡ ላድርግልሽ፧ለንጉሥ፡ወይስ፡ለሰራዊት፡አለቃ፡ልንገርልሽን፧በላት፡አለው፤ርሷም፦እኔ፡በወገኔ፡መካከል፡ ተቀምጫለኹ፡ብላ፡መለሰች።
14ርሱም፦እንግዲህ፡ምን፡እናድርግላት፧አለ።ግያዝም፦ልጅ፡የላትም፤ባሏም፡ሸምግሏል፡ብሎ፡መለሰ።
15ርሱም፦ጥራት፡አለ።በጠራትም፡ጊዜ፡በደጃፉ፡ቆመች።
16ርሱም፦በሚመጣው፡ዓመት፡በዚህ፡ወራት፡ወንድ፡ልጅ፡ትታቀፊያለሽ፡አለ፤ርሷም፦አይደለም፡ ጌታዬ፥የእግዚአብሔር፡ሰው፡ሆይ፥ባሪያኽን፡እንዳትዋሻት፡እለምንኻለኹ፡አለች።
17ሴቲቱም፡ፀነሰች፥በዚያም፡ወራት፡በዐዲሱ፡ዓመት፡ኤልሳዕ፡እንዳላት፡ወንድ፡ልጅ፡ወለደች።
18ሕፃኑም፡አደገ፥አንድ፡ቀንም፡እኽል፡ዐጫጆች፡ወዳሉበት፡ወደ፡አባቱ፡ወጣ።
19አባቱንም፦ራሴን፡ራሴን፡አለው፤ርሱም፡ሎሌውን፦ተሸክመኽ፡ወደ፡እናቱ፡ውሰደው፡አለው።
20አንሥቶም፡ወደ፡እናቱ፡ወሰደው፤በጕልበቷም፡ላይ፡እስከ፡ቀትር፡ድረስ፡ተቀመጠ፥ሞተም።
21ወጥታም፡በእግዚአብሔር፡ሰው፡ዐልጋ፡ላይ፡አጋደመችው፥በሩንም፡ዘግታበት፡ወጣች።
22ባሏንም፡ጠርታ፦ወደእግዚአብሔር፡ሰው፡በፍጥነት፡ደርሼ፡እመለስ፡ዘንድ፡አንድ፡ሎሌና፡አንድ፡አህያ፡ ላክልኝ፡አለችው።
23ርሱም፦መባቻ፡ወይም፡ሰንበት፡ያይደለ፡ዛሬ፡ለምን፡ትኼጂበታለሽ፧አለ።ርሷም፦ደኅና፡ነው፡አለች።
24አህያውንም፡አስጭና፡ሎሌዋን፦ንዳ፥ኺድ፤እኔ፡ሳላዝ፟ኽ፡አታዘግየኝ፡አለችው።
25እንዲሁም፡ኼደች፥ወደእግዚአብሔርም፡ሰው፡ወደቀርሜሎስ፡ተራራ፡መጣች።የእግዚአብሔርም፡ሰው፡ ከሩቅ፡ባያት፡ጊዜ፡ሎሌውን፡ግያዝን፥እንሇት፡ሱነማዊቲቱ፡መጣች፤
26ትቀበላትም፡ዘንድ፡ሩጥና፦በደኅናሽ፡ነውን፧ባልሽ፡ደኅና፡ነውን፧ልጅሽስ፡ደኅና፡ነውን፧በላት፡ አለው።ርሷም፦ደኅና፡ነው፡አለች። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
27ወደ፡ተራራው፡ወደእግዚአብሔር፡ሰው፡በመጣች፡ጊዜ፡እግሮቹን፡ጨበጠች፤ግያዝም፡ሊያርቃት፡ ቀረበ፤የእግዚአብሔርም፡ሰው፦ነፍሷ፡ዐዝናለችና፡ተዋት፤እግዚአብሔርም፡ያንን፡ከእኔ፡ሰውሮታል፡ አልነገረኝምም፡አለ።
28ርሷም፦በእውኑ፡ከጌታዬ፡ልጅን፡ለመንኹን፧እኔም፡አታታለ፟ኝ፡አላልኹኽምን፧አለች።
29ግያዝንም፦ወገብኽን፡ታጠቅ፥በትሬንም፡በእጅኽ፡ይዘኽ፡ኺድ፤ሰውም፡ብታገኝ፡ሰላም፡ አትበል፥ርሱም፡ሰላም፡ቢልኽ፡አትመልስለት፤በትሬንም፡በሕፃኑ፡ፊት፡ላይ፡አኑር፡አለው።
30የሕፃኑም፡እናት፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! በሕያው፡ነፍስኽም፡እምላለኹ! አልተውኽም፡ አለች፤ተነሥቶም፡ተከተላት።
31ግያዝም፡ቀደማቸው፥በትሩንም፡በሕፃኑ፡ፊት፡ላይ፡አኖረው፤ነገር፡ግን፥ድምፅ፡ወይም፡መስማት፡ አልነበረም፤ርሱንም፡ሊገናኘው፡ተመልሶ፦ሕፃኑ፡አልነቃም፡ብሎ፡ነገረው።
32ኤልሳዕም፡ወደ፡ቤት፡በገባ፡ጊዜ፥እንሆ፥ሕፃኑ፡ሞቶ፡በዐልጋው፡ላይ፡ተጋድሞ፡ነበር።
33ገብቶም፡በሩን፡ከኹለቱ፡በዃላ፡ዘጋ፥ወደ፡እግዚአብሔርም፡ጸለየ።
34መጥቶም፡በሕፃኑ፡ላይ፡ተኛ፤አፉንም፡በአፉ፥ዐይኑንም፡በዐይኑ፥እጁንም፡በእጁ፡ላይ፡አድርጎ፡ ተጋደመበት፤የሕፃኑም፡ገላ፡ሞቀ።
35ተመልሶም፡በቤቱ፡ውስጥ፡አንድ፡ጊዜ፡ወዲህና፡ወዲያ፡ተመላለሰ፤ደግሞም፡ወጥቶ፡ሰባት፡ጊዜ፡ በሕፃኑ፡ላይ፡ተጋደመ፤ሕፃኑም፡ዐይኖቹን፡ከፈተ።
36ግያዝንም፡ጠርቶ፦ይህችን፡ሱነማዊት፡ጥራ፡አለው።ጠራትም፥ወደ፡ርሱም፡በገባች፡ጊዜ፦ልጅሽን፡ አንሥተሽ፡ውሰጂ፡አላት።
37ገብታም፡በእግሩ፡አጠገብ፡ወደቀች፡በምድርም፡ላይ፡ተደፋች፤ልጇንም፡አንሥታ፡ወጣች።
38ኤልሳዕም፡ዳግመኛ፡ወደ፡ገልገላ፡መጣ፥በምድርም፡ላይ፡ራብ፡ነበረ፤የነቢያትም፡ልጆች፡በፊቱ፡ ተቀምጠው፡ነበር፥ሎሌውንም፦ታላቁን፡ምንቸት፡ጣድ፥ለነቢያት፡ልጆችም፡ወጥ፡ሥራ፡አለው።
39አንዱም፡ቅጠላቅጠል፡ያመጣ፡ዘንድ፡ወደ፡ሜዳ፡ወጣ፥የምድረ፡በዳውንም፡ሐረግ፡አገኘ፡ከዚያም፡ የበረሓ፡ቅል፡ሰበሰበ፥ልብሱንም፡ሞልቶ፡ተመለሰ፥መትሮም፡በወጡ፡ምንቸት፡ውስጥ፡ጨመረው፤ምን፡ እንደ፡ኾነ፡ግን፡አላወቁም።
40ሰዎቹም፡ይበሉ፡ዘንድ፡ቀዱ፤ወጡንም፡በቀመሱ፡ጊዜ፥የእግዚአብሔር፡ሰው፡ሆይ፥በምንቸቱ፡ውስጥ፡ ሞት፡አለ፡ብለው፡ጮኹ፤ይበሉም፡ዘንድ፡አልቻሉም።
41ርሱም፦ዱቄት፡አምጡልኝ፡አለ፤በምንቸቱም፡ውስጥ፡ጥሎ፦ይበሉ፡ዘንድ፡ለሕዝቡ፡ቅዱ፡ አለ።በምንቸቱም፡ውስጥ፡ክፉ፡ነገር፡አልተገኘም።
42አንድ፡ሰውም፡ከበዓልሻሊሻ፡የበኵራቱን፡እንጀራ፥ኻያ፡የገብስ፡እንጀራ፥የእኽልም፡እሸት፡በአቍማዳ፡ ይዞ፡ወደእግዚአብሔር፡ሰው፡መጣ፤ርሱም፦ይበሉ፡ዘንድ፡ለሕዝቡ፡ስጣቸው፡አለ።
43ሎሌውም፦ይህን፡እንዴት፡አድርጌ፡ለመቶ፡ሰው፡እሰጣለኹ፧አለ።ርሱም፦ይበላሉ፡ያተርፋሉም፡ ብሎ፡እግዚአብሔር፡ተናግሯልና፥ይበሉ፡ዘንድ፡ለሕዝቡ፡ስጣቸው፡አለ።
44እንዲሁም፡በፊታቸው፡አኖረው፥እንደእግዚአብሔርም፡ቃል፡በሉ፥አተረፉም።