1ነቢዩም፡ኤልሳዕ፡ከነቢያት፡ልጆች፡አንዱን፡ጠርቶ፡እንዲህ፡አለው፦ወገብኽን፡ታጥቀኽ፡ይህን፡የዘይት፡ ማሰሮ፡በእጅኽ፡ያዝ፥ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድም፡ኺድ።
2በዚያም፡በደረስኽ፡ጊዜ፡የናሜሲን፡ልጅ፡የኢዮሳፍጥን፡ልጅ፡ኢዩን፡ታገኘዋለኽ፤ገብተኽም፡ከወንድሞቹ፡ መካከል፡አስነሣው፥ወደ፡ጓዳም፡አግባው።
3የዘይቱንም፡ማሰሮ፡ይዘኽ፡በራሱ፡ላይ፡አፍሰ፟ውና፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእስራኤል፡ላይ፡ ንጉሥ፡ትኾን፡ዘንድ፡ቀባኹኽ፡በለው፤በሩንም፡ከፍተኽ፡ሽሽ፥አትዘግይም።
4እንዲሁም፡ጕልማሳው፡ነቢይ፡ወደ፡ሬማት፡ዘገለዓድ፡ኼደ።
5በገባም፡ጊዜ፥እንሆ፥የሰራዊት፡አለቃዎች፡ተቀምጠው፡ነበር፤ርሱም፦አለቃ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ነገር፡ አለኝ፡አለ።ኢዩም፦ከማንኛችን፡ጋራ፡ነው፧አለ።ርሱም፦አለቃ፡ሆይ፥ከአንተ፡ጋራ፡ነው፡አለ።
6ተነሥቶም፡ወደ፡ቤቱ፡ገባ፤ዘይቱንም፡በራሱ፡ላይ፡አፍሶ፟፡እንዲህ፡አለው፦የእስራኤል፡አምላክ፡ እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእግዚአብሔር፡ሕዝብ፡በእስራኤል፡ላይ፡ንጉሥ፡ትኾን፡ዘንድ፡ቀባኹኽ።
7የባሪያዎቼን፡የነቢያትን፡ደም፥የእግዚአብሔርንም፡ባሪያዎች፡ዅሉ፡ደም፡ከኤልዛቤል፡እጅ፡እበቀል፡ዘንድ፡ የጌታኽን፡የአክአብን፡ቤት፡ትመታለኽ።
8የአክአብም፡ቤት፡ዅሉ፡ይጠፋል፤በእስራኤልም፡ዘንድ፡የታሰረውንና፡የተለቀቀውን፡ወንድ፡ዅሉ፡ከአክአብ፡ አጠፋለኹ።
9የአክአብንም፡ቤት፡እንደ፡ናባጥ፡ልጅ፡እንደ፡ኢዮርብዓም፡ቤት፥እንደ፡አኪያም፡ልጅ፡እንደ፡ባኦስ፡ቤት፡ አደርገዋለኹ።
10ኤልዛቤልንም፡በኢይዝራኤል፡ዕርሻ፡ውሻዎች፡ይበሏታል፥የሚቀብራትም፡አታገኝም።በሩንም፡ከፍቶ፡ሸሸ።
11ኢዩም፡ወደጌታው፡ባሪያዎች፡ወጣ፤እነርሱም፦ደኅና፡ነውን፧ይህ፡እብድ፡ለምን፡ መጣብኽ፧አሉት።ርሱም፦ሰውዮውንና፡ነገሩን፡ታውቃላችኹ፡አላቸው።
12እነርሱም፦ሐሰት፡ነው፤ንገረን፡አሉት፤ርሱም፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእስራኤል፡ላይ፡ ንጉሥ፡ትኾን፡ዘንድ፡ቀባኹኽ፡ብሎ፡እንዲህ፡እንዲህ፡ነገረኝ፡አላቸው።
13ዅሉም፡ፈጥነው፡ልብሳቸውን፡ወሰዱ፥በሰገነቱ፡መሰላል፡ዕርከን፡ላይ፡ከእግሩ፡በታች፡አነጠፉት፥ቀንደ፡ መለከትም፡እየነፉ፦ኢዩ፡ነግሧል፡አሉ።
14እንዲሁም፡የናሜሲ፡ልጅ፡የኢዮሳፍጥ፡ልጅ፡ኢዩ፡በኢዮራም፡ላይ፡ተማማለ።ኢዮራምና፡የእስራኤል፡ ልጆች፡ዅሉ፡ከሶርያ፡ንጉሥ፡ከአዛሄል፡የተነሣ፡ሬማት፡ዘገለዓድን፡ይጠብቁ፡ነበር።
15ንጉሡ፡ኢዮራም፡ግን፡ከሶርያ፡ንጉሥ፡ከአዛሄል፡ጋራ፡በተዋጋ፡ጊዜ፡ሶርያውያን፡ያቈሰሉትን፡ቍስል፡ ይታከም፡ዘንድ፡ወደ፡ኢይዝራኤል፡ተመልሶ፡ነበር።ኢዩም፦ልባችኹስ፡ከእኔ፡ጋራ፡ከኾነ፡በኢይዝራኤል፡ እንዳያወራ፡ማንም፡ከከተማ፡ኰብሎ፟፡አይውጣ፡አለ።
16ኢዮራምም፡በዚያ፡ታሞ፟፡ተኝቶ፡ነበርና፥ኢዩ፡በሠረገላው፡ላይ፡ተቀምጦ፡ወደ፡ኢይዝራኤል፡ ኼደ።የይሁዳም፡ንጉሥ፡አካዝያስ፡ኢዮራምን፡ለማየት፡ወርዶ፡ነበር።
17በኢይዝራኤልም፡ግንብ፡ላይ፡የቆመው፡ሰላይ፡የኢዩ፡ጭፍራ፡ሲመታ፡አይቶ፦ጭፍራ፡አያለኹ፡ አለ።ኢዮራምም፦የሚገናኘው፡ፈረሰኛ፡ላክ፥ርሱም፦ሰላም፡ነውን፧ይበለው፡አለ።
18ፈረሰኛውም፡ሊገናኘው፡ኼዶ፦ንጉሡ፡እንዲህ፡ይላል፦ሰላም፡ነውን፧አለ።ኢዩም፦አንተ፡ከሰላም፡ ጋራ፡ምን፡አለኽ፧ወደ፡ዃላዬ፡ዐልፈኽ፡ተከተለኝ፡አለ።ሰላዩም፦መልእክተኛው፡ደረሰባቸው፥ነገር፡ ግን፥አልተመለሰም፡ብሎ፡ነገረው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19ኹለተኛም፡ፈረሰኛ፡ሰደደ፥ወደ፡እነርሱም፡ደርሶ፦ንጉሡ፡እንዲህ፡ይላል፦ሰላም፡ ነውን፧አለ።ኢዩም፦አንተ፡ከሰላም፡ጋራ፡ምን፡አለኽ፧ወደ፡ዃላዬ፡ዐልፈኽ፡ተከተለኝ፡አለ።
20ሰላዩም፦ደረሰባቸው፥ነገር፡ግን፥አልተመለሰም፤በችኰላ፡ይኼዳልና፥አካኼዱ፡እንደ፡ናሜሲ፡ልጅ፡ እንደ፡ኢዩ፡አካኼድ፡ነው፡ብሎ፡ነገረው።
21ኢዮራምም፦ሠረገላ፡አዘጋጁ፡አለ፤ሠረገላውንም፡አዘጋጁለት።የእስራኤልም፡ንጉሥ፡ኢዮራም፡ የይሁዳም፡ንጉሥ፡አካዝያስ፡በሠረገላዎቻቸው፡ተቀምጠው፡ወጡ፥ኢዩንም፡ሊገናኙት፡ ኼዱ፤በኢይዝራኤላዊው፡በናቡቴ፡ዕርሻ፡ውስጥ፡አገኙት።
22ኢዮራምም፡ኢዩን፡ባየ፡ጊዜ፦ኢዩ፡ሆይ፥ሰላም፡ነውን፧አለ።ርሱም፦የእናትኽ፡የኤልዛቤል፡ ግልሙትናዋና፡መተቷ፡ሲበዛ፡ምን፡ሰላም፡አለ፧ብሎ፡መለሰ።
23ኢዮራምም፡መልሶ፡ነዳና፡ሸሸ፥አካዝያስንም፦አካዝያስ፡ሆይ፥ዐመፅ፡ነው፡አለው።
24ኢዩም፡በእጁ፡ቀስቱን፡ለጠጠ፥ኢዮራምንም፡በጫንቃው፡መካከል፡ወጋው፤ፍላጻውም፡በልቡ፡ ዐለፈ፥ወደ፡ሠረገላውም፡ውስጥ፡ወደቀ።
25ኢዩም፡አለቃውን፡ቢድቃርን፡እንዲህ፡አለው፦አንሥተኽ፡በኢይዝራኤላዊው፡በናቡቴ፡ዕርሻ፡ ጣለው፥አንተና፡እኔ፡ጐን፡ለጐን፡በፈረስ፡ተቀምጠን፡አባቱን፡አክአብን፡በተከተልን፡ጊዜ፡እግዚአብሔር፡ እንዲህ፡ብሎ፡ይህን፡መከራ፡እንደ፡ተናገረበት፡ዐስብ።
26በእውነት፡የናቡቴንና፡የልጆቹን፡ደም፡ትናንትና፡አይቻለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር፥በዚህም፡ዕርሻ፡ እመልስብኻለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።ስለዚህ፡እግዚአብሔር፡እንደተናገረው፡ቃል፡ወስደኽ፡በዕርሻው፡ ውስጥ፡ጣለው።
27የይሁዳ፡ንጉሥ፡አካዝያስ፡ያንን፡ባየ፡ጊዜ፡በአትክልት፡ቤት፡መንገድ፡ሸሸ።ኢዩም፦ይህን፡ደግሞ፡ በሠረገላው፡ላይ፡ውጉት፡እያለ፡ተከተለው፤በይብለዓምም፡አቅራቢያ፡ባለችው፡በጉር፡ዐቀበት፡ላይ፡ ወጉት።ወደ፡መጊዶም፡ሸሸ፥በዚያም፡ሞተ።
28ባሪያዎቹም፡በሠረገላው፡ጭነው፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወሰዱት፥በዳዊትም፡ከተማ፡በመቃብሩ፡ከአባቶቹ፡ ጋራ፡ቀበሩት።
29በአክአብም፡ልጅ፡በኢዮራም፡በዐሥራ፡አንደኛው፡ዓመት፡አካዝያስ፡በይሁዳ፡ላይ፡ነገሠ።
30ኢዩም፡ወደ፡ኢይዝራኤል፡መጣ፤ኤልዛቤልም፡በሰማች፡ጊዜ፡ዐይኗን፡ተኳለች፥ራሷንም፡ አስጌጠች፥በመስኮትም፡ዘልቃ፡ትመለከት፡ነበር።
31ኢዩም፡በበሩ፡ሲገባ፦ጌታውን፡የገደለ፡ዘምሪ፡ሆይ፥ሰላም፡ነውን፧አለችው።
32ፊቱንም፡ወደ፡መስኮቱ፡አንሥቶ፦ከእኔ፡ጋራ፡ማን፡ነው፧አለ።ኹለት፡ሦስትም፡ጃን፡ደረባዎች፡ወደ፡ ርሱ፡ተመለከቱ።
33ርሱም፦ወደ፡ታች፡ወርውሯት፡አለ፤ወረወሯትም፥ደሟም፡በግንቡና፡በፈረሶቹ፡ላይ፡ ተረጨ፥ረገጧትም።
34በገባም፡ጊዜ፡በላ፡ጠጣም፤ከዚያም፡በዃላ፦ይህችን፡የተረገመች፡እዩ፤የንጉሥ፡ልጅ፡ናትና፥ቅበሯት፡ አለ።
35ሊቀብሯትም፡በኼዱ፡ጊዜ፥ከዐናቷና፡ከእግሯ፣ከመዳፍም፡በቀር፡ምንም፡አላገኙም።
36ተመልሰውም፡ነገሩት፤ርሱም፦በባሪያው፡በቴስብያዊ፡ኤልያስ፦በኢይዝራኤል፡ዕርሻ፡የኤልዛቤልን፡ሥጋ፡ ውሻዎች፡ይበላሉ፤
37የኤልዛቤልም፡ሬሳ፡በኢይዝራኤል፡ዕርሻ፡መሬት፡ላይ፡እንደ፡ፍግ፡ይኾናልና፥ማንም፦ይህች፡ ኤልዛቤል፡ናት፡ይል፡ዘንድ፡አይችልም፡ብሎ፡የተናገረው፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይህ፡ነው፡አለ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org