1ከዚህም፡በዃላ፡እንዲህ፡ኾነ፤ለዳዊት፡ልጅ፡ለአቤሴሎም፡አንዲት፡የተዋበች፡እኅት፡ነበረችው፥ስሟም፡ ትዕማር፡ነበረ፤የዳዊትም፡ልጅ፡አምኖን፡ወደዳት።
2አምኖንም፡ከእኅቱ፡ከትዕማር፡የተነሣ፡እጅግ፡ስለ፡ተከዘ፡ታመመ፤ድንግልም፡ነበረችና፡አንዳች፡ ያደርጋት፡ዘንድ፡በዐይኑ፡ፊት፡ጭንቅ፡ኾኖበት፡ነበር።
3ለአምኖንም፡የዳዊት፡ወንድም፡የሳምዓ፡ልጅ፡ኢዮናዳብ፡የሚባል፡ወዳጅ፡ነበረው፤ኢዮናዳብም፡እጅግ፡ ብልኅ፡ሰው፡ነበረ።
4ርሱም፦የንጉሥ፡ልጅ፡ሆይ፥ስለ፡ምን፡ቀን፡በቀን፡እንዲህ፡ ከሳኽ፧አትነግረኝምን፧አለው።አምኖንም፦የወንድሜን፡የአቤሴሎምን፡እኅት፡ትዕማርን፡እወዳ፟ታለኹ፡አለው።
5ኢዮናዳብም፦ታምሜያለኹ፡ብለኽ፡በዐልጋኽ፡ላይ፡ተኛ፤አባትኽም፡ሊያይኽ፡በመጣ፡ጊዜ፦እኅቴ፡ ትዕማር፡እንድትመጣና፡እኔ፡የምበላውን፡እንጀራ፡እንድትሰጠኝ፥መብሉንም፡እኔ፡እያየኹ፡ እንድታዘጋጅልኝ፥ከእጇም፡እንድበላው፡እለምንኻለኹ፡በል፡አለው።
6እንዲሁም፡አምኖን፦ታምሜያለኹ፡ብሎ፡ተኛ፤ንጉሡም፡ሊያየው፡በመጣ፡ጊዜ፡አምኖን፡ ንጉሡን፦እኅቴ፡ትዕማር፡እንድትመጣና፡እኔ፡እያየኹ፡ኹለት፡ዕንጐቻ፡እንድታደርግልኝ፥ከእጇም፡እንድበላ፡ እለምንኻለኹ፡አለው።
7ዳዊትም፦መብልን፡ታዘጋጂለት፡ዘንድ፡ወደወንድምሽ፡ወደአምኖን፡ቤት፡ኺጂ፡ብሎ፡መልእክተኛዎችን፡ ወደትዕማር፡ቤት፡ላከ።
8ትዕማርም፡ወደወንድሟ፡ወደአምኖን፡ቤት፡ኼደች፥ተኝቶም፡ነበር፤ዱቄትም፡ወስዳ፡ለወሰች፥እያየም፡ ዕንጐቻ፡አደረገች፥ጋገረችም።
9ምጣዱንም፡ወስዳ፡በፊቱ፡ገለበጠች፡ርሱ፡ግን፡ይበላ፡ዘንድ፡እንቢ፡አለ።አምኖንም፦ሰውን፡ዅሉ፡ ከእኔ፡ዘንድ፡አስወጡ፡አለ፤ሰውም፡ዅሉ፡ከርሱ፡ዘንድ፡ወጣ።
10አምኖንም፡ትዕማርን፦ከእጅሽ፡እበላ፡ዘንድ፡መብሉን፡ወደ፡ዕልፍኙ፡አግቢው፡አላት፤ትዕማርም፡ የሠራችውን፡ዕንጐቻ፡ወስዳ፡ወንድሟ፡አምኖን፡ወዳለበት፡ዕልፍኝ፡አገባችው።
11መብሉንም፡ባቀረበች፡ጊዜ፡ያዛትና፦እኅቴ፡ሆይ፥ነዪ፥ከእኔም፡ጋራ፡ተኚ፡አላት። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
12ርሷ፡መልሳ፦ወንድሜ፡ሆይ፥አይኾንም፤እንዲህ፡ያለ፡ነገር፡በእስራኤል፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ምና፡ አታሳፍረኝ፤ይህንም፡ነውረኛ፡ሥራ፡አታድርግ።
13እኔም፡ነውሬን፡ወዴት፡ልሸከም፧አንተም፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ከምናምንቴዎች፡እንደ፡አንዱ፡ ትኾናለኽ፤እንግዲህስ፡ለንጉሡ፡ንገረው፥እኔንም፡አይነሣኽም፡አለችው።
14ቃሏን፡ግን፡አልሰማም፤ከርሷም፡ይልቅ፡ብርቱ፡ነበረና፡በግድ፡አስነወራት፥ከርሷም፡ጋራ፡ተኛ።
15ከዚያም፡በዃላ፡አምኖን፡ፈጽሞ፡ጠላት፤አስቀድሞም፡ከወደዳት፡ውድ፡ይልቅ፡በዃላ፡የጠላት፡ጥል፡ በለጠ።አምኖንም፦ተነሥተሽ፡ኺጂ፡አላት።
16ርሷም፦አይኾንም፤ቀድሞ፡ከሠራኸው፡ክፋት፡ይልቅ፡እኔን፡በማውጣትኽ፡የበለጠ፡ክፋት፡ትሠራለኽ፡ አለችው፤ርሱ፡ግን፡አልሰማትም።
17የሚያገለግለውንም፡ብላቴና፡ጠርቶ፦ይህችን፡ሴት፡ከፊቴ፡አስወጥተኽ፡በሩን፡ዝጋባት፡አለው።
18ብዙ፡ሕብር፡ያለውንም፡ልብስ፡ለብሳ፡ነበር፥እንዲህ፡ያለውን፡ልብስ፡የንጉሡ፡ልጆች፡ደናግሉ፡ ይለብሱ፡ነበርና፤አገልጋዩም፡አስወጥቶ፡በሩን፡ዘጋባት።
19ትዕማርም፡በራሷ፡ላይ፡ዐመድ፡ነስንሳ፥ብዙ፡ሕብርም፡ያለውን፡ልብሷን፡ተርትራ፥እጇንም፡በራሷ፡ላይ፡ ጭና፡እየጮኸች፡ኼደች።
20ወንድሟም፡አቤሴሎም፦ወንድምሽ፡አምኖን፡ከአንቺ፡ጋራ፡ነበረን፧እኅቴ፡ሆይ፥አኹን፡ግን፡ዝም፡ በዪ፤ወንድምሽ፡ነው፤ይህን፡ነገር፡በልብሽ፡አትያዢው፡አላት።ትዕማርም፡በወንድሟ፡በአቤሴሎም፡ቤት፡ ብቻዋን፡ተቀመጠች።
21ንጉሡም፡ዳዊት፡ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡በሰማ፡ጊዜ፡እጅግ፡ተቈጣ፤ነገር፡ግን፥የበኵር፡ልጁ፡ነበረና፡ስለ፡ ወደደው፡የልጁን፡የአምኖን፡ነፍስ፡አላሳዘነም።
22አቤሴሎምም፡እኅቱን፡ትዕማርን፡ስላሳፈራት፡አምኖንን፡ጠልቶታልና፡አቤሴሎም፡አምኖንን፡ክፉም፡ኾነ፡ መልካምም፡አልተናገረውም።
23ከኹለት፡ዓመትም፡በዃላ፡አቤሴሎም፡በኤፍሬም፡አቅራቢያ፡ባለችው፡በቤላሶር፡በጎቹን፡ አሸለተ፤አቤሴሎምም፡የንጉሡን፡ልጆች፡ዅሉ፡ጠራ።
24አቤሴሎምም፡ወደ፡ንጉሡ፡መጥቶ፦እንሆ፥ባሪያኽ፡በጎቹን፡ያሸልታል፤ንጉሡና፡ሎሌዎቹ፡ከባሪያኽ፡ ጋራ፡ይኺዱ፡አለው።
25ንጉሡም፡አቤሴሎምን፦ልጄ፡ሆይ፥እንከብድብኻለንና፡ዅላችን፡እንመጣ፡ዘንድ፡አይኾንም፡ አለው።የግድም፡አለው፥ርሱ፡ግን፡መረቀው፡እንጂ፡ለመኼድ፡እንቢ፡አለ።
26አቤሴሎምም፦አንተ፡እንቢ፡ካልኽ፡ወንድሜ፡አምኖን፡ከእኛ፡ጋራ፡እንዲኼድ፡እለምንኻለኹ፡ አለ።ንጉሡም፦ከአንተ፡ጋራ፡ለምን፡ይኼዳል፧አለው።
27አቤሴሎምም፡የግድ፡አለው፥አምኖንንና፡የንጉሡንም፡ልጆች፡ዅሉ፡ከርሱ፡ጋራ፡ሰደደ።
28አቤሴሎምም፡እንደ፡ንጉሥ፡ግብዣ፡ያለ፡ግብዣ፡አደረገ፤አቤሴሎምም፡አገልጋዮቹን፦አምኖን፡የወይን፡ ጠጅ፡ጠጥቶ፡ልቡን፡ደስ፡ባለው፡ጊዜ፡እዩ።አምኖንን፡ግደሉ፡ባልዃችኹም፡ጊዜ፡ ግደሉት፥አትፍሩም፤ያዘዝዃችኹም፡እኔ፡ነኝና፡በርቱ፡ጽኑም፡ብሎ፡አዘዛቸው።
29የአቤሴሎም፡አገልጋዮች፡አቤሴሎም፡እንዳዘዛቸው፡በአምኖን፡ላይ፡አደረጉበት።የንጉሡም፡ልጆች፡ዅሉ፡ ተነሥተው፡በየበቅሎዎቻቸው፡ተቀምጠው፡ሸሹ።
30ገናም፡በመንገድ፡ሲኼዱ፡ለዳዊት፦አቤሴሎም፡የንጉሡን፡ልጆች፡ዅሉ፡ገድሏል፥ከነርሱም፡አንድ፡ አልቀረም፡የሚል፡ወሬ፡መጣለት።
31ንጉሡም፡ተነሥቶ፡ልብሱን፡ቀደደ፥በምድር፡ላይም፡ወደቀ፤ባሪያዎቹም፡ዅሉ፡ልብሳቸውን፡ቀደ፟ው፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org በአጠገቡ፡ቆሙ።
32የዳዊትም፡ወንድም፡የሳምዓ፡ልጅ፡ኢዮናዳብ፦ጌታዬ፡ጕልማሳዎቹ፡የንጉሡ፡ልጆች፡ዅሉ፡እንደ፡ሞቱ፡ አያስብ፤እኅቱን፡ትዕማርን፡በግድ፡ካስነወራት፡ዠምሮ፡በአቤሴሎም፡ዘንድ፡የተቈረጠ፡ነገር፡ነበረና፡የሞተ፡ አምኖን፡ብቻ፡ነው።
33አኹንም፡የሞተ፡አምኖን፡ብቻ፡ነው፡እንጂ፡የንጉሥ፡ልጆች፡ዅሉ፡ሞቱ፡ብሎ፡ጌታዬ፡ንጉሡ፡ይህን፡ ነገር፡በልቡ፡አያኑር፡አለው።
34አቤሴሎምም፡ኰበለለ።ጕበኛውም፡ጕልማሳ፡ዐይኑን፡ከፍ፡አደረገ፥እንሆም፥ብዙ፡ሰዎች፡በዃላው፡ በተራራው፡አጠገብ፡በመንገድ፡ሲመጡ፡አየ።
35ኢዮናዳብም፡ንጉሡን፦እንሆ፥የንጉሡ፡ልጆች፡መጥተዋል፤ባሪያኽ፡እንዳለው፡እንዲሁ፡ኾኗል፡አለው።
36ተናግሮም፡በጨረሰ፡ጊዜ፥እንሆ፥ወዲያው፡የንጉሥ፡ልጆች፡ገቡ፥ድምፃቸውንም፡ከፍ፡አድርገው፡ አለቀሱ፤ደግሞ፡ንጉሡና፡ባሪያዎቹ፡ዅሉ፡እጅግ፡ታላቅ፡ልቅሶ፡አለቀሱ።
37አቤሴሎም፡ግን፡ኰብሎ፟፡ወደጌሹር፡ንጉሥ፡ወደዐሚሁድ፡ልጅ፡ወደ፡ተልማይ፡ኼደ።ዳዊትም፡ ዅልጊዜ፡ለልጁ፡ያለቅስ፡ነበር።
38አቤሴሎም፡ኰብሎ፟፡ወደ፡ጌሹር፡ኼደ፥በዚያም፡ሦስት፡ዓመት፡ያኽል፡ተቀመጠ።
39ንጉሡም፡ዳዊት፡ስለ፡አምኖን፡ሞት፡ተጽናንቶ፡ወደ፡አቤሴሎም፡ይኼድ፡ዘንድ፡እጅግ፡ናፈቀ።