1የጽሩያም፡ልጅ፡ኢዮአብ፡የንጉሡ፡ልብ፡ወደ፡አቤሴሎም፡እንዳዘነበለ፡ዐወቀ።
2ኢዮአብም፡ወደ፡ቴቁሔ፡ልኮ፡ከዚያ፡ብልኀተኛ፡ሴት፡አስመጣና፦አልቅሺ፥የሐዘንም፡ልብስ፡ ልበሺ፥ዘይትም፡አትቀቢ፥ስለ፡ሞተ፡ሰውም፡ብዙ፡ዘመን፡እንደምታለቅሺ፡ኹኚ፤
3ወደ፡ንጉሡም፡ገብተሽ፡እንዲህ፡ያለውን፡ቃል፡ንገሪው፡አላት፤ኢዮአብም፡ቃሉን፡በርሷ፡አፍ፡አደረገ።
4እንዲሁም፥የቴቁሔዪቱ፡ሴት፡ወደ፡ንጉሥ፡ገብታ፡በግንባሯ፡በምድር፡ላይ፡ወደቀች፥እጅ፡ ነሥታም፦ንጉሥ፡ሆይ፥አድነኝ፡አለች።
5ንጉሡም፦ምን፡ኾነሻል፧አላት።ርሷም፡መልሳ፡አለች፦በእውነት፡እኔ፡ባሌ፡የሞተብኝ፡ባልቴት፡ሴት፡ ነኝ።
6ለኔም፡ለባሪያኽ፡ኹለት፡ወንዶች፡ልጆች፡ነበሩኝ፥በሜዳም፡ተጣሉ፤የሚገላግላቸውም፡ አልነበረም፥አንዱም፡ሌላውን፡መቶ፟፡ገደለው።
7እንሆም፥ዘመዶች፡ዅሉ፡በባሪያኽ፡ላይ፡ተነሥተው፦ስለገደለው፡ስለወንድሙ፡ነፍስ፡እንገድለው፡ዘንድ፡ ወንድሙን፡የገደለውን፡አውጪ፡አሉኝ፤እንዲሁም፡ደግሞ፡ወራሹን፡የቀረውን፡መብራቴን፡ያጠፋሉ፥የባሌን፡ ስምና፡ዘርም፡ከምድር፡ላይ፡አያስቀሩም።
8ንጉሡም፡ሴቲቱን፦ወደ፡ቤትሽ፡ኺጂ፥እኔም፡ስለ፡አንቺ፡አዛ፟ለኹ፡አላት።
9የቴቁሔዪቱም፡ሴት፡ንጉሡን፦ጌታዬ፡ንጉሥ፡ሆይ፥ኀጢአቱ፡በእኔና፡በአባቴ፡ቤት፡ላይ፡ ይኹን፤ንጉሡና፡ዙፋኑ፡ንጹሕ፡ይኹን፡አለችው።
10ንጉሡም፦የሚናገርሽን፡አምጪልኝ፥ከዚያም፡በዃላ፡ደግሞ፡አይነካሽም፡አለ።
11ርሷም፦ደም፡ተበቃዮችም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡እንዳያጠፉ፡ልጄንም፡እንዳይገድሉ፥ንጉሡ፡አምላኩን፡ እግዚአብሔርን፡ያስብ፡አለች።ርሱም፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! ከልጅሽ፡አንድ፡ጠጕር፡በምድር፡ላይ፡ አይወድቅም፡አለ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
12ሴቲቱም፦እኔ፡ባሪያኽ፡ለጌታዬ፡ለንጉሥ፡አንድ፡ቃል፡ልናገር፡አለች፤ርሱም፦ተናገሪ፡አለ።
13ሴቲቱም፡አለች፦በእግዚአብሔር፡ሕዝብ፡ላይ፡እንዲህ፡ያለ፡ነገር፡ስለ፡ምን፡ዐሰብኽ፧ንጉሡ፡ይህን፡ ነገር፡ተናግሯልና፡ያሳደደውን፡ስላላስመለሰ፡በደለኛ፡ነው።
14ዅላችን፡እንሞታለን፥በምድርም፡ላይ፡እንደ፡ፈሰሰና፡እንደማይመለስ፡ውሃ፡ነን፤እግዚአብሔርም፡ የነፍስን፡ጥፋት፡አይወድ፟ም፥ነገር፡ግን፥የተጣለ፡ሰው፡ፈጽሞ፡እንዳይጠፋ፡በምክሩ፡ያስባል።
15አኹንም፡ሕዝቡ፡ስለሚያስፈራኝ፡ይህን፡ነገር፡ለጌታዬ፡ለንጉሥ፡እነግረው፡ዘንድ፡መጥቻለኹ፤እኔም፡ ባሪያኽ፦ምናልባት፡የእኔን፡የባሪያውን፡ልመና፡ንጉሡ፡ያደርግልኝ፡እንደ፡ኾነ፡ለንጉሡ፡ልናገር፤
16ርሷንና፡ልጇን፡ከእግዚአብሔር፡ርስት፡ያጠፋቸው፡ዘንድ፡ከሚሻ፡ሰው፡እጅ፡ያድን፡ዘንድ፡ንጉሡ፡ ባሪያውን፡ይሰማል፡አልኹ።
17እኔም፡ባሪያኽ፦መልካሙንና፡ክፉውን፡ነገር፡ለመስማት፡ንጉሡ፡ጌታዬ፡እንደእግዚአብሔር፡መልአክ፡ ነውና፥የጌታዬ፡የንጉሡ፡ቃል፡ያጽናናኛል፤አምላክኽም፡እግዚአብሔር፡ከአንተ፡ጋራ፡ይኹን፡አልኹ።
18ንጉሡም፡ለሴቲቱ፡መልሶ፦የምጠይቅሽን፡ነገር፡አትሰውሪኝ፡አላት።ሴቲቱም፦ጌታዬ፡ንጉሥ፡ይናገር፡ አለች።
19ንጉሡም፦በዚህ፡ዅሉ፡የኢዮአብ፡እጅ፡ከአንቺ፡ጋራ፡ነውን፧አላት።ሴቲቱም፡መልሳ፦ጌታዬ፡ንጉሥ፡ ሆይ፥በሕያው፡ነፍስኽ፡እምላለኹ! ጌታዬ፡ንጉሥ፡ከተናገረው፡ነገር፡ዅሉ፡ወደ፡ቀኝም፡ወደ፡ግራም፡ሊል፡ የሚችል፡የለም፤ባሪያኽ፡ኢዮአብ፡አዞ፟ኛል፥ይህንም፡ቃል፡ዅሉ፡በባሪያኽ፡አፍ፡አደረገው።
20ባሪያኽ፡ኢዮአብ፡የዚህ፡ነገር፡መልክ፡እንዲለወጥ፡አደረገ፤ነገር፡ግን፥የእግዚአብሔር፡መልአክ፡ ጠቢብ፡እንደ፡ኾነ፥አንተም፡ጌታዬ፡በምድር፡ላይ፡ያለውን፡ነገር፡ዅሉ፡ታውቅ፡ዘንድ፡ጠቢብ፡ነኽ፡አለች።
21ንጉሡም፡ኢዮአብን፦እንሆ፥ይህን፡ነገር፡አድርጌያለኹ፤እንግዲህ፡ኺድና፡ብላቴናውን፡አቤሴሎምን፡ መልሰው፡አለው።
22ኢዮአብም፡በምድር፡ላይ፡በግንባሩ፡ወድቆ፡እጅ፡ነሣ፥ንጉሡንም፡ባረከ፤ኢዮአብም፦ጌታዬ፡ንጉሥ፡ ሆይ፥የባሪያኽን፡ነገር፡አድርገኻልና፡በዐይንኽ፡ፊት፡ሞገስ፡እንዳገኘ፡ባሪያኽ፡ዛሬ፡ዐወቀ፡አለ።
23ኢዮአብም፡ተነሥቶ፡ወደ፡ጌሹር፡ኼደ፥አቤሴሎምንም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ይዞ፡መጣ።
24ንጉሡም፦ወደ፡ቤቱ፡ይኺድ፡እንጂ፡ፊቴን፡እንዳያይ፡አለ፤አቤሴሎምም፡ወደ፡ቤቱ፡ ኼደ፥የንጉሡንም፡ፊት፡አላየም።
25በእስራኤልም፡ዅሉ፡ዘንድ፡እንደ፡አቤሴሎም፡በውበቱ፡የተመሰገነ፡ሰው፡አልነበረም፤ከእግሩ፡እስከ፡ ራሱ፡ድረስ፡ነውር፡አልነበረበትም።
26ጠጕሩም፡ይከብደው፡ነበርና፥በዓመት፡አንድ፡ጊዜ፡ይቈርጠው፡ነበር፤ሲቈረጥም፡የራሱ፡ጠጕር፡ በንጉሥ፡ሚዛን፡ኹለት፡መቶ፡ሰቅል፡ያኽል፡ይመዘን፡ነበር።
27ለአቤሴሎምም፡ሦስት፡ወንዶች፡ልጆችና፡አንዲት፡ሴት፡ልጅ፡ተወለዱለት፤የሴቲቱም፡ልጅ፡ስም፡ ትዕማር፡ነበረ፥ርሷም፡የተዋበች፡ሴት፡ነበረች።
28አቤሴሎምም፡በኢየሩሳሌም፡ኹለት፡ዓመት፡ሙሉ፡የንጉሡን፡ፊት፡ሳያይ፡ተቀመጠ።
29አቤሴሎምም፡ወደ፡ንጉሡ፡ይልከው፡ዘንድ፡ወደ፡ኢዮአብ፡ላከ፥ወደ፡ርሱም፡ሊመጣ፡ አልወደደም፤ኹለተኛም፡ላከበት፥ሊመጣ፡ግን፡አልወደደም።
30ባሪያዎቹንም፦በዕርሻዬ፡አጠገብ፡ያለውን፡የኢዮአብን፡ዕርሻ፡እዩ፥በዚያም፡ገብስ፡አለው፤ኺዳችኹ፡ በእሳት፡አቃጥሉት፡አላቸው።የአቤሴሎምም፡ባሪያዎች፡ዕርሻውን፡አቃጠሉት።
31ኢዮአብም፡ተነሥቶ፡ወደ፡አቤሴሎም፡ወደ፡ቤቱ፡መጣና፦ባሪያዎችኽ፡ዕርሻዬን፡ስለ፡ምን፡ አቃጠሉት፧አለው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
32አቤሴሎምም፡ኢዮአብን፡መልሶ፦ከጌሹር፡ለምን፡መጣኹ፧በዚያም፡ተቀምጬ፡ብኾን፡ይሻለኝ፡ነበር፡ ብለኽ፡እንድትነግረው፡ወደ፡ንጉሡ፡እልክኽ፡ዘንድ፡ወደ፡እኔ፡ጠራኹኽ፤አኹንም፡የንጉሡን፡ፊት፡ ልይ፥ኀጢአት፡ቢኾንብኝ፡ይግደለኝ፡አለው።
33ኢዮአብም፡ወደ፡ንጉሥ፡መጥቶ፡ነገረው፤አቤሴሎምንም፡ጠራው፥ወደ፡ንጉሡም፡ገብቶ፡በንጉሥ፡ ፊት፡ወደ፡ምድር፡በግንባሩ፡ተደፋ፤ንጉሡም፡አቤሴሎምን፡ሳመው።