1ከዚህም፡በዃላ፡አቤሴሎም፡ሠረገላና፡ፈረሶች፥በፊቱም፡የሚሮጡ፡ዐምሳ፡ሰዎች፡አዘጋጀ።
2አቤሴሎምም፡በማለዳ፡ተነሥቶ፡በበሩ፡አደባባይ፡ይቆም፡ነበር፤አቤሴሎምም፡ከንጉሥ፡ለማስፈረድ፡ጕዳይ፡ የነበረውን፡ዅሉ፡ወደ፡ርሱ፡እየጠራ፦አንተ፡ከወዴት፡ከተማ፡ነኽ፧ብሎ፡ይጠይቅ፡ነበር።ርሱም፦እኔ፡ ባሪያኽ፡ከእስራኤል፡ነገድ፡ከአንዲቱ፡ነኝ፡ብሎ፡ይመልስ፡ነበር።
3አቤሴሎምም፦ነገርኽ፡እውነትና፡ቅን፡ነው፤ነገር፡ግን፥ከንጉሥ፡ታዞ፟፡የሚሰማኽ፡የለም፡ይለው፡ነበር።
4አቤሴሎምም፦ነገርና፡ክርክር፡ያለው፡ዅሉ፡ወደ፡እኔ፡ይመጣ፡ዘንድ፡ቅንም፡ፍርድ፡እፈርድለት፡ዘንድ፡ በአገር፡ላይ፡ፈራጅ፡አድርጎ፡ማን፡በሾመኝ፧ይል፡ነበር።
5ሰውም፡እጅ፡ሊነሣው፡ወደ፡ርሱ፡በቀረበ፡ጊዜ፡እጁን፡ዘርግቶ፡ይይዝና፡ይስመው፡ነበር።
6እንዲሁም፡አቤሴሎም፡ከንጉሥ፡ፍርድ፡ሊሰማ፡ከእስራኤል፡ዘንድ፡በሚመጣ፡ዅሉ፡ያደርግ፡ ነበር፤አቤሴሎምም፡የእስራኤልን፡ሰዎች፡ልብ፡ሰረቀ።
7እንዲህም፡ኾነ፤ከአራት፡ዓመት፡በዃላ፡አቤሴሎም፡ንጉሡን፦ለእግዚአብሔር፡የተሳልኹትን፡ስእለት፡ ለመስጠት፡ወደ፡ኬብሮን፥እባክኽ፥ልኺድ።
8እኔ፡ባሪያኽ፡በሶርያ፡ጌሹር፡ሳለኹ፦እግዚአብሔር፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ቢመልሰኝ፡ለእግዚአብሔር፡ መሥዋዕት፡አቀርባለኹ፡ብዬ፡ስእለት፡ተስዬ፡ነበር፡አለው።
9ንጉሡም፦በደኅና፡ኺድ፡አለው፤ተነሥቶም፡ወደ፡ኬብሮን፡ኼደ።
10አቤሴሎምም፡በእስራኤል፡ነገድ፡ዅሉ፦የቀንደ፡መለከት፡ድምፅ፡በሰማችኹ፡ጊዜ፦አቤሴሎም፡ በኬብሮን፡ነገሠ፡በሉ፡የሚሉ፡ጕበኛዎች፡ላከ።
11የተጠሩትም፡ኹለት፡መቶ፡ሰዎች፡ከአቤሴሎም፡ጋራ፡በየዋህነት፡ከኢየሩሳሌም፡ኼዱ፤የሚኾነውንም፡ ነገር፡ከቶ፡አያውቁም፡ነበር።
12አቤሴሎምም፡የዳዊት፡መካር፡የነበረውን፡የጊሎ፡ሰው፡አኪጦፌልን፡ከከተማው፡ከጊሎ፡መሥዋዕት፡ በሚያቀርብበት፡ጊዜ፡አስጠራው።ሤራውም፡ጽኑ፡ኾነ፤ከአቤሴሎምም፡ጋራ፡ያለ፡ሕዝብ፡እየበዛ፡ኼደ።
13ለዳዊትም፦የእስራኤል፡ሰዎች፡ልብ፡ከአቤሴሎም፡ጋራ፡ኾኗል፡የሚል፡ወሬኛ፡መጣለት።
14ዳዊትም፡ከርሱ፡ጋራ፡በኢየሩሳሌም፡ያሉትን፡ባሪያዎቹን፡ዅሉ፦ተነሡ፥እንሽሽ፡ያለዚያ፡ከአቤሴሎም፡ እጅ፡የሚድን፡ከእኛ፡የለምና፤መጥቶም፡እንዳይዘን፥ክፉም፡እንዳያመጣብን፡ከተማዪቱንም፡በሰይፍ፡ስለት፡ እንዳይመታ፡ፈጥናችኹ፡እንኺድ፡አላቸው።
15የንጉሡም፡ባሪያዎች፡ንጉሡን፦እንሆ፥ጌታችን፡ንጉሡ፡የመረጠውን፡ዅሉ፡እኛ፡ባሪያዎችኽ፡ዕሺ፡ ብለን፡እናደርጋለን፡አሉት።
16ንጉሡም፡ከርሱም፡በዃላ፡ቤተ፡ሰቡ፡ዅሉ፡ወጡ፤ንጉሡም፡ዐሥሩን፡ሴቶች፡ቁባቶቹን፡ቤቱን፡ ይጠብቁ፡ዘንድ፡ተወ።
17ንጉሡም፡ከርሱም፡በዃላ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ወጡ፥በቤትሜርሐቅም፡ቆሙ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
18ባሪያዎቹም፡ዅሉ፡በፊቱ፡ዐለፉ፤ከሊታውያንና፡ፈሊታውያንም፡ዅሉ፥ከርሱም፡በዃላ፡ከጌት፡የመጡት፡ ስድስት፡መቶው፡ጌትያውን፡ዅሉ፡በንጉሡ፡ፊት፡ዐለፉ።
19ንጉሡም፡የጌት፡ሰው፡ኢታይን፦ከእኛ፡ጋራ፡ለምን፡መጣኽ፧አንተ፡ከስፍራኽ፡የመጣኽ፡እንግዳና፡ ስደተኛ፡ነኽና፥ተመለስ፥ከንጉሡም፡ጋራ፡ተቀመጥ።
20የመጣኸው፡ትናንት፡ነው፤ዛሬ፡ከእኛ፡ጋራ፡ላዙርኽን፧እኔ፡ወደምኼድበት፡እኼዳለኹ፤አንተ፡ግን፡ ተመለስ፥ወንድሞችኽንም፡ከአንተ፡ጋራ፡ውሰድ፥እግዚአብሔርም፡ምሕረቱንና፡እውነቱን፡ያድርግልኽ፡አለው።
21ኢታይም፡ለንጉሡ፡መልሶ፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! በጌታዬም፡በንጉሡ፡ሕይወት፡እምላለኹ! በእውነት፡ ጌታዬ፡ባለበት፡ስፍራ፡ዅሉ፥በሞትም፡ቢኾን፡በሕይወትም፥በዚያ፡ደግሞ፡እኔ፡ባሪያኽ፡እኾናለኹ፡አለው።
22ዳዊትም፡ኢታይን፦ኺድ፡ተሻገር፡አለው፤የጌት፡ሰው፡ኢታይና፡ሰዎቹም፡ዅሉ፥ከርሱም፡ጋራ፡ የነበሩት፡ሕፃናት፡ዅሉ፡ተሻገሩ።
23በአገርም፡የነበሩት፡ዅሉ፡በታላቅ፡ድምፅ፡አለቀሱ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ተሻገሩ፥ንጉሡም፡ደግሞ፡ የቄድሮንን፡ፈፋ፡ተሻገረ፤ሕዝቡም፡ዅሉ፡ወደምድረ፡በዳ፡መንገድ፡ተሻገሩ።
24እንሆም፥ደግሞ፡ሳዶቅ፡ከርሱም፡ጋራ፡ሌዋውያን፡ዅሉ፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ኪዳን፡ታቦት፡ ተሸክመው፡መጡ፤የእግዚአብሔርንም፡ታቦት፡አስቀመጡ፥ሕዝቡም፡ዅሉ፡ከከተማዪቱ፡ፈጽሞ፡እስኪያልፍ፡ ድረስ፡አብያታር፡ወጣ።
25ንጉሡም፡ሳዶቅን፦የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ወደ፡ከተማ፡መልስ፤በእግዚአብሔር፡ዐይን፡ሞገስ፡አግኝቼ፡ እንደ፡ኾንኹ፥መልሶ፡ርሱንና፡ማደሪያውን፡ያሳየኛል፤
26ነገር፡ግን፦አልወድ፟ኽም፡ቢለኝ፥እንሆኝ፥ደስ፡የሚያሠኘውን፡ያድርግብኝ፡አለው።
27ንጉሡም፡ደግሞ፡ካህኑን፡ሳዶቅን፦እንሆ፥አንተና፡ልጅኽ፡አኪማዐስ፡የአብያታርም፡ልጅ፡ዮናታን፡ ኹለቱ፡ልጆቻችኹ፡በደኅና፡ወደ፡ከተማ፡ተመለሱ።
28እኔም፥እንሆ፥ከእናንተ፡ዘንድ፡ወሬ፡እስኪመጣልኝ፡ድረስ፡በምድረ፡በዳው፡መሻገሪያ፡እቈያለኹ፡ አለው።
29ሳዶቅም፡አብያታርም፡የእግዚአብሔርን፡ታቦት፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መለሱት፥በዚያም፡ተቀመጡ።
30ዳዊትም፡ተከናንቦ፡ያለጫማ፡እያለቀሰ፡ወደደብረ፡ዘይት፡ዐቀበት፡ወጣ፤ከርሱም፡ጋራ፡የነበሩት፡ሕዝብ፡ ዅሉ፡ተከናንበው፡እያለቀሱ፡ወጡ፦
31አኪጦፌል፡ከአቤሴሎም፡ጋራ፡በሤራ፡አንድ፡ነው፡ብለው፡ለዳዊት፡ ነገሩት፤ዳዊትም፦አቤቱ፥የአኪጦፌልን፡ምክር፡ስንፍና፡አድርገኽ፡እንድትለውጥ፡እለምንኻለኹ፡አለ።
32ዳዊትም፡ለእግዚአብሔር፡ወደሰገደበት፡ወደተራራው፡ራስ፡በመጣ፡ጊዜ፥አርካዊው፡ኩሲ ፡ልብሱን፡ ቀዶ፟፡በራሱም፡ላይ፡ትቢያ፡ነስንሶ፡ሊገናኘው፡መጣ።
33ዳዊትም፡አለው፦ከእኔ፡ጋራ፡ብትመጣ፡ትከብደኛለኽ፤
34ወደ፡ከተማ፡ግን፡ተመልሰኽ፡ለአቤሴሎም፦ንጉሥ፡ሆይ፥ባሪያ፡እኾንኻለኹ፤አስቀድሞ፡ለአባትኽ፡ ባሪያ፡እንደ፡ነበርኹ፡እንዲሁ፡አኹን፡ለአንተ፡ባሪያ፡እኾንኻለኹ፡ብትለው፡የአኪጦፌልን፡ምክር፡ከንቱ፡ ታደርግልኛለኽ።
35ካህናቱ፡ሳዶቅና፡አብያታርም፡በዚያ፡ከአንተ፡ጋራ፡አይደሉምን፧ከንጉሡ፡ቤትም፡የምትሰማውን፡ነገር፡ ዅሉ፡ለካህናቱ፡ለሳዶቅና፡ለአብያታር፡ንገራቸው።
36እንሆ፥የሳዶቅ፡ልጅ፡አኪማዐስና፡የአብያታር፡ልጅ፡ዮናታን፡ልጆቻቸው፡በዚያ፡ከነርሱ፡ጋራ፡ አሉ፤የምትሰሙትን፡ዅሉ፡በእነርሱ፡እጅ፡ላኩልኝ። 153 ዕብ.፥ሑሲ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
37የዳዊትም፡ወዳጅ፡ኩሲ፡ወደ፡ከተማ፡መጣ፤አቤሴሎምም፡ደግሞ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ገባ።