1ዳዊትም፡ከተራራው፡ራስ፡ጥቂት፡ፈቀቅ፡ባለ፡ጊዜ፡የሜምፊቦስቴ፡ባሪያ፡ሲባ፡ኹለት፡መቶ፡ እንጀራ፥አንድ፡መቶም፡ዘለላ፡ዘቢብ፥አንድ፡መቶም፡በለስ፥አንድ፡አቍማዳም፡ወይን፡ጠጅ፡የተጫኑ፡ ኹለት፡አህያዎች፡እየነዳ፡ተገናኘው።
2ንጉሡም፡ሲባን፦ይህ፡ምንድር፡ነው፧አለው።ሲባም፦አህያዎቹ፡የንጉሥ፡ቤተ፡ሰቦች፡ይቀመጡባቸው፡ ዘንድ፥እንጀራውና፡በለሱ፡ብላቴናዎቹ፡ይበሉት፡ዘንድ፥የወይን፡ጠጁም፡በበረሓ፡የሚደክሙት፡ይጠጡት፡ ዘንድ፡ነው፡አለ።
3ንጉሡም፦የጌታኽ፡ልጅ፡ወዴት፡ነው፧አለ።ሲባም፡ንጉሡን፦እንሆ፦የእስራኤል፡ቤት፡ዛሬ፡የአባቴን፡ መንግሥት፡ይመልስልኛል፡ብሎ፡በኢየሩሳሌም፡ተቀምጧል፡አለው።
4ንጉሡም፡ሲባን፦እንሆ፥ለሜምፊቦስቴ፡የነበረው፡ዅሉ፡ለአንተ፡ይኹን፡አለው።ሲባም፦እጅ፡ እነሣለኹ፤ጌታዬ፡ንጉሥ፡ሆይ፥በፊትኽ፡ሞገስ፡ላግኝ፡አለ።
5ንጉሡ፡ዳዊትም፡ወደ፡ብራቂም፡መጣ፤እንሆም፥ሳሚ፡የሚባል፡የጌራ፡ልጅ፡ከሳኦል፡ቤተ፡ዘመድ፡ የኾነ፡አንድ፡ሰው፡ከዚያ፡ወጣ፥እየኼደም፡ይረግመው፡ነበር።
6ወደ፡ዳዊትና፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደዳዊት፡ባሪያዎችም፡ድንጋይ፡ይወረውር፡ነበር፤በንጉሡም፡ቀኝና፡ግራ፡ ሕዝቡ፡ዅሉና፡ኀያላኑ፡ዅሉ፡ነበሩ።
7ሳሚም፡ሲረግም፦ኺድ፥አንተ፡የደም፡ሰው፥ምናምንቴ፥ኺድ።
8በፋንታው፡ነግሠኻልና፡እግዚአብሔር፡የሳኦልን፡ቤት፡ደም፡ዅሉ፡መለሰብኽ፤እግዚአብሔርም፡ መንግሥትን፡ለልጅኽ፡ለአቤሴሎም፡እጅ፡አሳልፎ፡ሰጥቶታል፤እንሆም፥አንተ፡የደም፡ሰው፡ነኽና፥በመከራ፡ ተይዘኻል፡አለ።
9የጽሩያም፡ልጅ፡አቢሳ፡ንጉሡን፦ይህ፡የሞተ፡ውሻ፡ጌታዬን፡ንጉሡን፡ስለ፡ምን፡ይረግማል፧ልኺድና፡ ራሱን፡ልቍረጠው፡አለው።
10ንጉሡም፦እናንተ፡የጽሩም፡ልጆች፥እኔ፡ከእናንተ፡ጋራ፡ምን፡አለኝ፧እግዚአብሔር፦ዳዊትን፡ስደበው፡ ብሎ፡አዞ፟ታልና፥ይርገመኝ፤ለምንስ፡እንዲህ፡ታደርጋለኽ፧የሚለው፡ማን፡ነው፧አለ።
11ዳዊትም፡አቢሳንና፡ባሪያዎቹን፡ዅሉ፦እንሆ፥ከወገቤ፡የወጣው፡ልጄ፡ነፍሴን፡ይሻል፤ይልቁንስ፡ይህ፡ የብንያም፡ልጅ፡እንዴት፡ነዋ፧እግዚአብሔር፡አዞ፟ታልና፥ተዉት፥ይርገመኝ።
12ምናልባት፡በዚህ፡ቀን፡መከራዬን፡አይቶ፡ስለ፡ርግማኑ፡መልካም፡ይመልስልኛል፡አላቸው።
13ዳዊትና፡ሰዎቹም፡በመንገድ፡ይኼዱ፡ነበር፤ሳሚም፡በተራራው፡አጠገብ፡በርሱ፡ትይዩ፡እየኼደ፡ ይራገም፤ድንጋይም፡ይወረውር፥ትቢያም፡ይበትን፡ነበር።
14ንጉሡና፡ከርሱም፡ጋራ፡የነበረው፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ደክመው፡ነበር፥በዚያም፡ዐረፉ።
15አቤሴሎምና፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡የእስራኤልም፡ሰዎች፡አኪጦፌልም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡መጡ።
16የዳዊትም፡ወዳጅ፡አርካዊው፡ኩሲ፡ወደ፡አቤሴሎም፡በመጣ፡ጊዜ፥ኩሲ፦ሺሕ፡ዓመት፡ያንግሥኽ፡ አለው።
17አቤሴሎምም፡ኩሲን፦ስለ፡ወዳጅኽ፡ያደረግኸው፡ቸርነት፡ይህ፡ነውን፧ከወዳጅኽ፡ጋራ፡ያልኼድኽ፡ ስለ፡ምንድር፡ነው፧አለው።
18ኩሲም፡አቤሴሎምን፦እንዲህ፡አይደለም፤ከእግዚአብሔር፡ከዚህም፡ሕዝብ፡ከእስራኤልም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ ለተመረጠው፡ለርሱ፡እኾናለኹ፡ከርሱም፡ጋራ፡እቀመጣለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19ዳግምም፡የማገለግል፡ለማን፡ነው፧በንጉሥ፡ልጅ፡ፊት፡አይደለምን፧በአባትኽ፡ፊት፡እንዳገለገልኹ፡ እንዲሁ፡ባንተ፡ፊት፡እኾናለኹ፡አለው።
20አቤሴሎምም፡አኪጦፌልን፦ምከሩ፡ምን፡እናድርግ፧አለው።
21አኪጦፌልም፡አቤሴሎምን፦ቤት፡ሊጠብቁ፡ወደተዋቸው፡ወዳባትኽ፡ቁባቶች፡ግባ፤እስራኤልም፡ዅሉ፡ አባትኽን፡እንዳሳፈርኸው፡ይሰማሉ፤ከአንተም፡ጋራ፡ያሉት፡ዅሉ፡እጃቸው፡ይበረታል፡አለው።
22ለአቤሴሎምም፡በሰገነት፡ላይ፡ድንኳን፡ተከሉለት፤አቤሴሎምም፡በእስራኤል፡ዅሉ፡ፊት፡ወዳባቱ፡ቁባቶች፡ ገባ።
23በዚያም፡ወራት፡የመከራት፡የአኪጦፌል፡ምክር፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡እንደ፡መጠየቅ፡ ነበረች፤የአኪጦፌልም፡ምክር፡ዅሉ፡ከዳዊትና፡ከአቤሴሎም፡ጋራ፡እንዲህ፡ነበረች።