1እንዲህም፡ኾነ፤አንድ፡ብንያማዊ፡የቢክሪ፡ልጅ፡ስሙ፡ሳቤዔ፡የሚባል፡ምናምንቴ፡ሰው፡ ነበረ፤ርሱም፦ከዳዊት፡ዘንድ፡ዕድል፡ፈንታ፡የለንም፥ከእሴይም፡ልጅ፡ዘንድ፡ርስት፡የለንም፤እስራኤል፡ ሆይ፥እያንዳንድኽ፡ወደ፡ድንኳንኽ፡ተመለስ፡ብሎ፡ቀንደ፡መለከት፡ነፋ።
2የእስራኤልም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ከዳዊት፡ተለይተው፡የቢክሪን፡ልጅ፡ሳቤዔን፡ተከተሉ፤የይሁዳ፡ሰዎች፡ግን፡ ከዮርዳኖስ፡ዠምረው፡ኢየሩሳሌም፡እስኪደርሱ፡ንጉሣቸውን፡ተከተሉ።
3ዳዊትም፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወደ፡ቤቱ፡መጣ፤ንጉሡም፡ቤቱን፡ሊጠብቁ፡የተዋቸውን፡ዐሥሩን፡ቁባቶች፡ ወስዶ፡ለጠባቂ፡ሰጣቸው፥ቀለብም፡ሰጣቸው፥ነገር፡ግን፥ወደ፡እነርሱ፡አልገባም፤በቤት፡ተዘግተው፡ እስኪሞቱም፡ድረስ፡ባልቴቶች፡ኾነው፡ተቀመጡ።
4ንጉሡም፡ዐማሳይን፦የይሁዳን፡ሰዎች፡ዅሉ፡በሦስት፡ቀን፡ውስጥ፡ጥራልኝ፥አንተም፡ዐብረኽ፡በዚህ፡ ኹን፡አለው።
5ዐማሳይም፡የይሁዳን፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይጠራ፡ዘንድ፡ኼደ፤ነገር፡ግን፥ርሱ፡የተቀጠረውን፡ቀን፡አሳልፎ፡ ዘገየ።
6ዳዊትም፡አቢሳን፦አኹን፡ከአቤሴሎም፡ይልቅ፡የሚጐዳን፡የቢክሪ፡ልጅ፡ሳቤዔ፡ነው፤ርሱ፡የተመሸጉትን፡ ከተማዎች፡አግኝቶ፡ከዐይናችን፡እንዳያመልጥ፥አንተ፡የጌታኽን፡ባሪያዎች፡ወስደኽ፡አሳደ፟ው፡አለው።
7አቢሳንም፡ተከትለው፡የኢዮአብ፡ሰዎች፡ከሊታውያንም፡ፈሊታውያንም፡ኀያላንም፡ዅሉ፡ኼዱ፤የቢክሪንም፡ ልጅ፡ሳቤዔን፡ለማሳደድ፡ከኢየሩሳሌም፡ወጡ።
8በገባዖንም፡ወዳለው፡ወደ፡ታላቁ፡ድንጋይ፡በደረሱ፡ጊዜ፡ዐማሳይ፡ሊገናኛቸው፡መጣ፤ኢዮአብም፡ የሰልፍ፡ልብስ፡ለብሶ፡ነበር፥በላዩም፡መታጠቂያ፡ነበረ፥በወገቡም፡ላይ፡ሰገባ፡ያለው፡ሰይፍ፡ታጥቆ፡ ነበር፤ርሱም፡ሲራመድ፡ሰይፉ፡ወደቀ።
9ኢዮአብም፡ዐማሳይን፦ወንድሜ፡ሆይ፥ደኅና፡ነኽን፧አለው፡ኢዮአብም፡ዐማሳይን፡የሚስም፡መስሎ፡ በቀን፡እጁ፡ጢሙን፡ያዘው።
10ዐማሳይ፡ግን፡በኢዮአብ፡እጅ፡ከነበረው፡ሰይፍ፡አልተጠነቀቀም፡ነበር፤ኢዮአብም፡ሆዱን፡ ወጋው፥አንዠቱንም፡በምድር፡ላይ፡ዘረገፈው፤ኹለተኛም፡አልወጋውም፥ሞተም።ኢዮአብና፡ወንድሙ፡አቢሳ፡ የቢክሪን፡ልጅ፡ሳቤዔን፡አሳደዱ።
11ከኢዮአብም፡ብላቴናዎች፡አንዱ፡በዐማሳይ፡ሬሳ፡አጠገብ፡ቆሞ፦ለኢዮአብ፡ወዳጅ፡የሚኾን፡ለዳዊትም፡ የኾነ፡ዅሉ፡ኢዮአብን፡ይከተል፡ይል፡ነበር።
12ዐማሳይም፡በመንገድ፡መካከል፡ወድቆ፡በደሙ፡ላይ፡ይንከባለል፡ነበር፤ያም፡ሰው፡ወደ፡ርሱ፡የሚመጣ፡ ዅሉ፡ሲቆም፡አይቷልና፥ሕዝቡ፡ዅሉ፡እንደ፡ቆመ፡ባየ፡ጊዜ፡ዐማሳይን፡ከመንገድ፡ላይ፡ወደ፡ዕርሻ፡ ውስጥ፡ፈቀቅ፡አደረገው፥በልብስም፡ከደነው።
13ከመንገድ፡ራቅ፡ባለ፡ጊዜ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡የቢክሪን፡ልጅ፡ሳቤዔን፡ለማሳደድ፡ኢዮአብን፡ተከትሎ፡ያልፍ፡ ነበር።
14ርሱ፡ግን፡ከእስራኤል፡ነገድ፡ዅሉ፡ወደ፡አቤል፥ወደ፡ቤትመዓካ፥ወደ፡ቤሪም፡ዅሉ፡ዐለፈ፤ሰዎችም፡ ደግሞ፡ተሰብስበው፡ተከተሉት።
15በቤትመዓካ፡ባለ፡በአቤልም፡መጥተው፡ከበቡት፥በከተማዪቱም፡ላይ፡እስከ፡ቅጥሯ፡ድረስ፡የዐፈርን፡ ድልድል፡ደለደሉ፤ቅጥሩንም፡ያፈርሱ፡ዘንድ፡ከኢዮአብ፡ጋራ፡የነበሩ፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ይደባደቡ፡ነበር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
16ከከተማዪቱም፡አንዲት፡ብልኀተኛ፡ሴት።ስሙ፥ስሙ፤ኢዮአብንም፦እነግርኽ፡ዘንድ፡ወደዚህ፡ቅረብ፡ በሉት፡ስትል፡ጮኸች።
17ወደ፡ርሷም፡ቀረበ፤ሴቲቱም፦ኢዮአብ፡አንተ፡ነኽን፧አለች።ርሱም፦እኔ፡ነኝ፡ብሎ፡ መለሰላት።ርሷም፦የባሪያኽን፡ቃል፡ስማ፡አለችው።ርሱም፦እሰማለኹ፡አላት።
18ርሷም፦ቀድሞ፦የሚጠይቅ፡በአቤል፡ዘንድ፡ይጠይቅ፡ይባል፡ነበር፤እንዲሁም፡ነገሩ፡ይፈጸም፡ነበር።
19በእስራኤል፡ዘንድ፡ሰላምንና፡እውነትን፡ከሚወዱ፡እኔ፡ነኝ፤አንተ፡በእስራኤል፡ያለችውን፡ከተማና፡እናት፡ ለማፍረስ፡ትሻለኽ፤ስለ፡ምንስ፡የእግዚአብሔርን፡ርስት፡ትውጣለኽ፧ብላ፡ተናገረች።
20ኢዮአብም፡መልሶ፦ይህ፡መዋጥና፡ማጥፋት፡ከእኔ፡ይራቅ፤
21ነገሩ፡እንዲህ፡አይደለም፤ከተራራማው፡ከኤፍሬም፡አገር፡የሚኾን፡የቢክሪ፡ልጅ፡ሳቤዔ፡የሚባል፡አንድ፡ ሰው፡ግን፡በንጉሡ፡በዳዊት፡ላይ፡እጁን፡አነሣ፤ርሱን፡ብቻውን፡ስጡኝ፥እኔም፡ከከተማዪቱ፡እርቃለኹ፡ አላት።ሴቲቱም፡ኢዮአብን፦እንሆ፥ራሱ፡ከቅጥር፡ላይ፡ይጣልልኻል፡አለችው።
22ሴቲቱም፡በብልኀቷ፡ወደ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ኼደች፤እነርሱም፡የቢክሪን፡ልጅ፡የሳቤዔን፡ራስ፡ቈርጠው፡ ወደ፡ኢዮአብ፡ጣሉት።ርሱም፡ቀንደ፡መለከቱን፡ነፋ፥ሰውም፡ዅሉ፡ከከተማዪቱ፡ርቆ፡እያንዳንዱ፡ወደ፡ ድንኳኑ፡ኼደ።ኢዮአብም፡ወደ፡ንጉሡ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተመለሰ።
23ኢዮአብም፡በእስራኤል፡ሰራዊት፡ዅሉ፡ላይ፡አለቃ፡ነበረ፤የዩዳሄም፡ልጅ፡በናያስ፡በከሊታውያንና፡ በፈሊታውያን፡ላይ፡ነበረ፤
24አዶኒራምም፡ግብር፡አስገባሪ፡ነበረ፤የአኂሉድም፡ልጅ፡ኢዮሳፍጥ፡ታሪክ፡ጸሓፊ፡ነበረ፤
25ሱሳም፡ጸሓፊ፡ነበረ፤ሳዶቅና፡አብያታርም፡ካህናት፡ነበሩ፤
26የኢያዕር፡ሰውም፡ዒራስ ፡ለዳዊት፡አማካሪ፡ነበረ።