Skip to content
← 2 Samuel

Chapter 4 · Amharic

2 Samuel

1የሳኦልም፡ልጅ፡ኢያቡስቴ፡አበኔር፡በኬብሮን፡እንደ፡ሞተ፡በሰማ፡ጊዜ፡እጁ፡ደከመች፥እስራኤላውያንም፡ ዅሉ፡ደነገጡ።

2ለሳኦልም፡ልጅ፡ለኢያቡስቴ፡የጭፍራ፡አለቃዎች፡የኾኑ፡ኹለት፡ሰዎች፡ነበሩት፤የአንዱም፡ስም፡ በዓና፥የኹለተኛውም፡ስም፡ሬካብ፡ነበረ፥ከብንያምም፡ልጆች፡የብኤሮታዊው፡የሬሞን፡ልጆች፡ ነበሩ፤ብኤሮትም፡ለብንያም፡ተቈጥራ፡ነበር።

3ብኤሮታውያንም፡ወደ፡ጌቴም፡ሸሽተው፡ነበር፥እስከ፡ዛሬም፡ድረስ፡በዚያ፡ተጠግተው፡ነበር።

4ለሳኦልም፡ልጅ፡ለዮናታን፡አንድ፡ሽባ፡የኾነ፡ልጅ፡ነበረው።የሳኦልና፡የዮናታን፡ወሬ፡ከኢይዝራኤል፡ በመጣ፡ጊዜ፡የዐምስት፡ዓመት፡ልጅ፡ነበረ፥ሞግዚቱም፡ዐዝላው፡ሸሸች፤ፈጥናም፡ስትሸሽ፡ወድቆ፡ሽባ፡ ኾነ።ስሙም፡ሜምፊቦስቴ፡ነበር።

5የብኤሮታዊውም፡የሬሞን፡ልጆች፡ሬካብና፡በዓና፡ቀኑ፡ሲሞቅ፡ወደኢያቡስቴ፡ቤት፡መጡ፤ርሱም፡በቀትር፡ ጊዜ፡በምንጣፍ፡ላይ፡ተኝቶ፡ነበር።

6በረኛዪቱም፡ስንዴ፡ታበጥር፡ነበር፥አንቀላፍታም፡ተኝታ፡ነበር፤ሬካብና፡ወንድሙ፡በዓናም፡በቀስታ፡ገቡ።

7ወደ፡ቤትም፡በገቡ፡ጊዜ፡ርሱ፡በዕልፍኙ፡በምንጣፉ፡ላይ፡ተኝቶ፡ሳለ፡መቱት፥ገደሉትም፤ራሱንም፡ ቈርጠው፡ወሰዱት፥በዐረባም፡መንገድ፡ሌሊቱን፡ዅሉ፡ኼዱ።

8የኢያቡስቴንም፡ራስ፡ይዘው፡ወደ፡ዳዊት፡ወደ፡ኬብሮን፡መጡ፥ንጉሡንም፦ነፍስኽን፡ይሻ፡የነበረው፡ የጠላትኽ፡የሳኦል፡ልጅ፡የኢያቡስቴ፡ራስ፡እንሆ፤እግዚአብሔርም፡ዛሬ፡ከሳኦልና፡ከዘሩ፡ለጌታችን፡ለንጉሥ፡ ተበቀለለት፡አሉት።

9ዳዊትም፡ለብኤሮታዊው፡ለሬሞት፡ልጆች፡ለሬካብና፡ለወንድሙ፡ለበዓና፡እንዲህ፡ብሎ፡ መለሰላቸው።ነፍሴን፡ከመከራ፡ዅሉ፡ያዳነ፡ሕያው፡እግዚአብሔርን!

10መልካም፡ወሬ፡የያዘ፡መስሎት፦እንሆ፥ሳኦል፡ሞተ፡ብሎ፡የነገረኝን፡የምሥራቹ፡ዋጋ፡እንዲኾን፡ ይዤ፡በጺቅላግ፡ገደልኹት።

11ይልቁንስ፡በቤቱ፡ውስጥ፡በምንጣፉ፡ላይ፡ንጹሑን፡ሰው፡የገደላችኹትን፡እናንተን፡ኀጢአተኛዎችንማ፡ እንዴት፡ነዋ፧ደሙን፡ከእጃችኹ፡አልሻውምን፧ከምድርም፡አላጠፋችኹምን፧

12ዳዊትም፡ጕልማሳዎቹን፡አዘዘ፥ገደሏቸውም፤እጃቸውንና፡እግራቸውን፡ቈርጠው፡በኬብሮን፡በውሃ፡ መቆሚያ፡አጠገብ፡አንጠለጠሏቸው።የኢያቡስቴንም፡ራስ፡ወስደው፡በአበኔር፡መቃብር፡በኬብሮን፡ቀበሩት።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source