1እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የኤዶምያስን፡ንጉሥ፡ዐጥንት፡ዐመድ፡እስኪኾን፡ድረስ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org አቃጥሎታልና፥ስለ፡ሦስት፡ወይም፡ስለ፡አራት፡የሞዐብ፡ኀጢአት፡መቅሠፍቴን፡ከማድረግ፡አልመለስም።
2በሞዐብ፡ላይ፡እሳትን፡እሰዳ፟ለኹ፥የቂርዮትንም፡አዳራሾች፡ትበላለች፤ሞዐብም፡በውካታና፡በጩኸት፡ በመለከትም፡ድምፅ፡ይሞታል፤
3ፈራጅንም፡ከመካከሏ፡አጠፋለኹ፥ከርሱም፡ጋራ፡አለቃዎቿን፡ዅሉ፡እገድላለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
4እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የእግዚአብሔርን፡ሕግ፡ጥለዋልና፥ትእዛዙንም፡ አልጠበቁምና፥አባቶቻቸውም፡የተከተሉት፡ሐሰታቸው፡አስቷቸዋልና፥ስለ፡ሦስት፡ወይም፡ስለ፡አራት፡የይሁዳ፡ ኀጢአት፡መቅሠፍቴን፡ከማድረግ፡አልመለስም።
5በይሁዳ፡ላይ፡እሳትን፡እሰዳ፟ለኹ፥የኢየሩሳሌምንም፡አዳራሾች፡ትበላለች።
6እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ጻድቁን፡ስለ፡ብር፥ችጋረኛውንም፡ስለ፡አንድ፡ጥንድ፡ጫማ፡ ሽጠውታልና፥ስለ፡ሦስት፡ወይም፡ስለ፡አራት፡የእስራኤል፡ኀጢአት፡መቅሠፍቴን፡ከማድረግ፡አልመለስም።
7የድኻዎችን፡ራስ፡በምድር፡ትቢያ፡ላይ፡ይረግጣሉ፥የትሑታንንም፡መንገድ፡ያጣምማሉ፤ቅዱሱንም፡ስሜን፡ ያረክሱ፡ዘንድ፡አባትና፡ልጁ፡ወደ፡አንዲት፡ሴት፡ይገባሉ፤
8በመሠዊያውም፡ዅሉ፡አጠገብ፡ለመያዣነት፡በተወሰደው፡ልብስ፡ላይ፡ይተኛሉ፤በአምላካቸውም፡ቤት፡ ውስጥ፡በካሣ፡የተወሰደውን፡ወይን፡ጠጅ፡ይጠጣሉ።
9እኔ፡ግን፡ቁመቱ፡እንደ፡ዝግባ፡ቁመት፥ብርታቱም፡እንደ፡ኮምበል፡ዛፍ፡የነበረውን፡አሞራዊውን፡ ከፊታቸው፡አጠፋኹ፤ፍሬውንም፡ከላዩ፥ሥሩንም፡ከታቹ፡አጠፋኹ።
10የአሞራዊውንም፡ምድር፡ትወርሱ፡ዘንድ፡ከግብጽ፡ምድር፡አወጣዃችኹ፥በምድረ፡በዳም፡አርባ፡ዓመት፡ መራዃችኹ።
11ከወንድ፡ልጆቻችኹም፡ነቢያትን፥ከጐበዛዝታችኹም፡ናዝራውያንን፡አስነሣኹ፤እናንተ፡የእስራኤል፡ልጆች፡ ሆይ፥ይህ፡እንደዚህ፡አይደለምን፧ይላል፡እግዚአብሔር።
12እናንተ፡ግን፡ናዝራውያኑን፡የወይን፡ጠጅ፡አጠጣችዃቸው፤ነቢያቱንም፦ትንቢትን፡አትናገሩ፡ብላችኹ፡ አዘዛችዃቸው።
13እንሆ፥ነዶ፡የተሞላች፡ሠረገላ፡እንደምትደቀድቅ፡እንዲሁ፡እደቀድቃችዃለኹ።
14ከሯጪም፡ሽሽት፡ይጠፋል፥ብርቱውም፡በብርታቱ፡አይበረታም፥ኀያሉም፡ነፍሱን፡አያድንም፤
15ቀስተኛውም፡አይቆምም፥ፈጣኑም፡አይድንም፥ፈረሰኛውም፡ነፍሱን፡አያድንም፤
16በኀያላኑም፡መካከል፡ልበ፡ሙሉው፡በዚያ፡ቀን፡ዕራቍቱን፡ኾኖ፡ይሸሻል፥ይላል፡እግዚአብሔር።