Skip to content
← Amos

Chapter 4 · Amharic

Amos

1በሰማርያ፡ተራራ፡የምትኖሩ፥ድኻዎችንም፡የምትበድሉ፥ችጋረኛዎችንም፡ የምታሰጨንቁ፥ጌታዎቻቸውንም፦አምጡ፡እንጠጣ፡የምትሉ፡እናንተ፡የባሳን፡ላሞች፡ሆይ፥ይህን፡ቃል፡ስሙ።

2ጌታ፡እግዚአብሔር፦እናንተን፡በሰልፍ፡ዕቃ፥ቅሬታችኹንም፡በመቃጥን፡የሚወስዱበት፡ ቀን፥እንሆ፥በላያችኹ፡ይመጣል፡ብሎ፡በቅዱስነቱ፡ምሏል።

3እያንዳንዳችኹ፡በየፊታችኹ፡በተነደለ፡ስፍራ፡ትወጣላችኹ፤በሬማንም፡ትጣላላችኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።

4የእስራኤል፡ልጆች፡ሆይ፥ይህን፡ወዳ፟ችዃልና፥ወደ፡ቤቴል፡ኑና፡ኀጢአትን፡ሥሩ፤ወደ፡ገልገላ፡ኑና፡ ኀጢአትን፡አብዙ፤በየማለዳውም፡መሥዋዕታችኹን፥በየሦስተኛውም፡ቀን፡ዐሥራታችኹን፡አቅርቡ፤

5ርሾ፡ካለበትም፡የምስጋናውን፡መሥዋዕት፡አቅርቡ፥በፈቃዳችኹም፡የምታቀርቡትን፡ዐውጁና፡አውሩ፥ይላል፡ ጌታ፡እግዚአብሔር።

6በከተማችኹ፡ዅሉ፡ጥርስን፡ማጥራት፥በስፍራችኹም፡ዅሉ፡እንጀራን፡ማጣት፡ሰጠዃችኹ፤እናንተ፡ግን፡ ወደ፡እኔ፡አልተመለሳችኹም፥ይላል፡እግዚአብሔር።

7መከር፡ሳይደርስ፡ገና፡ከሦስት፡ወር፡በፊት፡ዝናብ፡ከለከልዃችኹ፤በአንድም፡ከተማ፡ላይ፡ አዘነብኹ፥በሌላውም፡ከተማ፡ላይ፡እንዳይዘንብ፡አደረግኹ፤ባንድ፡ወገን፡ዘነበ፥ያልዘነበበትም፡ወገን፡ደረቀ።

8የኹለት፡ወይም፡የሦስት፡ከተማዎች፡ሰዎች፡ወደ፡አንዲት፡ከተማ፡ውሃ፡ይጠጡ፡ዘንድ፡ኼዱ፥ነገር፡ ግን፥አልረኩም፤እናንተ፡ግን፡ወደ፡እኔ፡አልተመለሳችኹም፥ይላል፡እግዚአብሔር።

9በዋግና፡በዐረማሞ፡መታዃችኹ፤የአታክልታችኹንም፡ብዛት፡ወይኖቻችኹንም፡በለሶቻችኹንም፡ ወይራዎቻችኹንም፡ተምች፡በልቷል፤እናንተ፡ግን፡ወደ፡እኔ፡አልተመለሳችኹም፥ይላል፡እግዚአብሔር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

10በግብጽ፡እንደ፡ነበረው፡ቸነፈርን፡ሰደድኹባችኹ፤ጐበዛዝታችኹን፡በሰይፍ፡ገደልኹ፥ፈረሶቻችኹንም፡ አስማረክኹ፤የሰፈራችኹንም፡ግማት፡ወደ፡አፍንጫችኹ፡አወጣኹ፤እናንተ፡ግን፡ወደ፡እኔ፡ አልተመለሳችኹም፥ይላል፡እግዚአብሔር።

11ሰዶምንና፡ገሞራን፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ገለበጣቸው፥እንዲሁ፡ገለበጥዃችኹ፥እናንተም፡ከእሳት፡ውስጥ፡ እንደ፡ተነጠቀ፡ትንታግ፡ኾናችኹ፤ነገር፡ግን፥ወደ፡እኔ፡አልተመለሳችኹም፥ይላል፡እግዚአብሔር።

12ስለዚህ፥እስራኤል፡ሆይ፥እንደዚህ፡አደርግብኻለኹ፤እስራኤልም፡ሆይ፥እንደዚህ፡ስለማደርግብኽ፡ አምላክኽን፡ለመገናኘት፡ተዘጋጅ።

13እንሆ፥ተራራዎችን፡የሠራ፥ነፋስንም፡የፈጠረ፥የልቡንም፡ዐሳብ፡ለሰው፡የሚነግር፥ንጋትን፡ጨለማ፡ የሚያደርግ፥በምድርም፡ከፍታዎች፡ላይ፡የሚረግጥ፥ስሙ፡የሰራዊት፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ነው።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source