Skip to content
← Amos

Chapter 8 · Amharic

Amos

1ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡አሳየኝ፡እንሆም፥የቃርሚያ፡ፍሬ፡የሞላበት፡እንቅብ፡ነበረ።

2ርሱም፦ዓሞጽ፡ሆይ፥የምታየው፡ምንድር፡ነው፧አለኝ።እኔም፦የቃርሚያ፡ፍሬ፡የሞላበት፡እንቅብ፡ ነው፡አልኹት።እግዚአብሔርም፡አለኝ፦ፍጻሜ፡በሕዝቤ፡በእስራኤል፡ላይ፡መጥቷል፤ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ ደግሞ፡አላልፋቸውም።

3የመቅደሱ፡ዝማሬ፡በዚያ፡ቀን፡ዋይታ፡ይኾናል፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤የሰዎችም፡ሬሳ፡ ይበዛል፥በስፍራውም፡ዅሉ፡በዝምታ፡ይጣላል።

4ችጋረኛውን፡የምትውጡ፥የአገሩንም፡ድኻ፡የምታጠፉ፡እናንተ፡ሆይ፦

5እኽልን፡እንሸጥ፡ዘንድ፡መባቻው፡መቼ፡ያልፋል፧የኢፍ፡መስፈሪያውንም፡እያሳነስን፥ሰቅሉንም፡ እያበዛን፥በሐሰተኛም፡ሚዛን፡እያታለልን፥

6ድኻውን፡በብር፡ችጋረኛውንም፡ባንድ፡ጥንድ፡ጫማ፡እንገዛ፡ዘንድ፥የስንዴውን፡ግርድ፡እንሸጥ፡ዘንድ፡ ስንዴውን፡እንድንሸምት፡ሰንበት፡መቼ፡ያልፋል፧የምትሉ፡እናንተ፡ሆይ፥ይህን፡ስሙ።

7እግዚአብሔር፡በያዕቆብ፡ክብር፡እንዲህ፡ብሎ፡ምሏል።ሥራቸውን፡ዅሉ፡ለዘለዓለም፡ምንም፡አልረሳም።

8በእውኑ፡ምድሪቱ፡ስለዚህ፡ነገር፡አትናወጥምን፧በርሷም፡የሚኖር፡ዅሉ፡አያለቅስምን፧መላ፟ዋም፡እንደ፡ ወንዙ፡ትነሣለች፤እንደ፡ግብጽም፡ወንዝ፡ትነሣለች፡ደግሞም፡ትወርዳለች።

9በዚያም፡ቀን፡ፀሓይ፡በቀትር፡እንድትገባ፡አደርጋለኹ፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤በብርሃንም፡ቀን፡ ምድሩን፡አጨልማለኹ።

10ዓመት፡በዓላችኹንም፡ወደ፡ልቅሶ፥ዝማሬያችኹንም፡ወደ፡ዋይታ፡እለውጣለኹ፤ማቅንም፡በወገብ፡ ዅሉ፥ራስ፡መንጨትንም፡በዅሉ፡ላይ፡አመጣለኹ፤እንደ፡አንድያ፡ልጅም፡ልቅሶ፥ፍጻሜውንም፡እንደ፡ መራራ፡ቀን፡አደርገዋለኹ።

11እንሆ፥በምድር፡ላይ፡ራብን፡የምሰድ፟በት፡ዘመን፡ይመጣል፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤ርሱም፡ የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ከመስማት፡እንጂ፡እንጀራን፡ከመራብና፡ውሃን፡ከመጠማት፡አይደለም።

12ከባሕርም፡እስከ፡ባሕር፡ድረስ፥ከሰሜንም፡እስከ፡ምሥራቅ፡ድረስ፡ይቅበዘበዛሉ፤የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ ለመሻት፡ይሯሯጣሉ፥አያገኙትምም።

13በዚያ፡ቀን፡መልካካሞች፡ደናግል፡ጐበዛዝትም፡በጥም፡ይዝላሉ።

14በሰማርያ፡ኀጢአት፡የሚምሉና፦ዳን፡ሆይ፥ሕያው፡አምላክኽን! ደግሞ፦ሕያው፡የቤርሳቤሕን፡መንገድ! ብለው፡የሚሉ፥እነርሱ፡ይወድቃሉ፥ደግሞም፡አይነሡም።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source