1ከንጉሡ፡ከናቡከደነጾር፡በምድር፡ዅሉ፡ወደሚቀመጡ፡ወገኖችና፡አሕዛብ፡በልዩ፡ልዩ፡ቋንቋም፡ ወደሚናገሩ፡ዅሉ፥ሰላም፡ይብዛላችኹ።
2ልዑል፡አምላክ፡በፊቴ፡ያደረገውን፡ተኣምራቱንና፡ድንቁን፡አሳያችኹ፡ዘንድ፡ወድጃለኹ።
3ተኣምራቱ፡እንዴት፡ታላቅ፡ነው! ድንቁም፡እንዴት፡ጽኑ፡ነው! መንግሥቱም፡የዘለዓለም፡መንግሥት፡ ነው፥ግዛቱም፡ለልጅ፡ልጅ፡ነው።
4እኔ፡ናቡከደነጾር፡በቤቴ፡ደስ፡ብሎኝ፡በአዳራሼም፡ተመችቶኝ፡ነበር።
5ሕልም፡ዐለምኹ፤ርሷም፡አስፈራችኝ፤በዐልጋዬም፡ላይ፡የነበረው፡ዐሳቤና፡የራሴ፡ራእይ፡አስጨነቁኝ።
6ስለዚህ፥የሕልሙን፡ፍቺ፡እንዲያስታውቁኝ፡የባቢሎን፡ጠቢባን፡ዅሉ፡ወደ፡እኔ፡ይገቡ፡ዘንድ፡አዘዝኹ።
7የዚያን፡ጊዜም፡የሕልም፡ተርጓሚዎቹና፡አስማተኛዎቹ፡ከለዳውያኑና፡ቃላ፟ተኛዎቹ፡ገቡ፤ሕልሙንም፡ በፊታቸው፡ተናገርኹ፥ፍቺውን፡ግን፡አላስታወቁኝም።
8በመጨረሻም፡የቅዱሳን፡አማልክት፡መንፈስ፡ያለበት፡እንደ፡አምላኬ፡ስም፡ብልጣሶር፡የሚባለው፡ዳንኤል፡ በፊቴ፡ገባ፤እኔም፡ሕልሙን፡ነገርኹት፡እንዲህም፡አልኹት።
9የሕልም፡ተርጓሚዎች፡አለቃ፡ብልጣሶር፡ሆይ፥የቅዱሳን፡አማልክት፡መንፈስ፡ባንተ፡ውስጥ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እንዳለ፥ከምስጢርም፡ዅሉ፡የሚያስቸግርኽ፡እንደሌለ፡ዐውቄያለኹና፡ያለምኹትን፡የሕልሜን፡ራእይ፡ ፍቺውንም፡ንገረኝ።
10የራሴ፡ራእይ፡በዐልጋዬ፡ላይ፡ይህ፡ነበረ፤እንሆ፥በምድር፡መካከል፡ዛፍ፡አየኹ፥ቁመቱም፡እጅግ፡ ረዥም፡ነበረ።
11ዛፉም፡ትልቅ፡ኾነ፥በረታም፥ቁመቱም፡እስከ፡ሰማይ፡ደረሰ፥መልኩም፡እስከምድር፡ዅሉ፡ዳርቻ፡ድረስ፡ ታየ።
12ቅጠሉም፦የተዋበ፡ነበረ፡ፍሬውም፡ብዙ፡ነበረ፥ለዅሉም፡መብል፡ነበረበት፤ከጥላውም፡በታች፡የምድር፡ አራዊት፡ያርፉበት፡ነበር፥በቅርንጫፎቹም፡ውስጥ፡የሰማይ፡ወፎች፡ይቀመጡ፡ነበር፥ሥጋ፡ለባሹም፡ዅሉ፡ ከርሱ፡ይበላ፡ነበር።
13በዐልጋዬም፡ላይ፡በራሴ፡ራእይ፡አየኹ፤እንሆም፥አንድ፡ቅዱስ፡ጠባቂ፡ከሰማይ፡ወረደ።
14በታላቅ፡ድምፅም፡እየጮኸ፡እንዲህ፡አለ፦ዛፉን፡ቍረጡ፥ቅርንጫፎቹንም፡ጨፍጭፉ፥ቅጠሎቹንም፡ አራግፉ፥ፍሬውንም፡በትኑ፤አራዊትም፡ከበታቹ፡ወፎቹም፡ከቅርንጫፉ፡ይሽሹ።
15ነገር፡ግን፥ጕቶውን፡በምድር፡ውስጥ፡ተዉት፥በመስክም፡ውስጥ፡በብረትና፡በናስ፡ማሰሪያ፡ታስሮ፡ ይቈይ፤በሰማይም፡ጠል፡ይረስርስ፡ዕድል፡ፈንታውም፡በምድር፡ሣር፡ውስጥ፡ከአራዊት፡ጋራ፡ይኹን።
16ልቡም፡ከሰው፡ልብ፡ይለወጥ፥የአውሬም፡ልብ፡ይሰጠው፤ሰባት፡ዘመናትም፡ይለፉበት።
17ልዑሉ፡በሰዎች፡መንግሥት፡ላይ፡እንዲሠለጥን፥ለወደደውም፡እንዲሰጠው፥ከሰውም፡የተዋረደውን፡ እንዲሾምበት፡ሕያዋን፡ያውቁ፡ዘንድ፥ይህ፡ነገር፡የጠባቂዎች፡ትእዛዝ፥ይህም፡ፍርድ፡የቅዱሳን፡ቃል፡ነው።
18እኔ፡ንጉሡ፡ናቡከደነጾር፡ይህን፡ሕልም፡ዐልሜያለኹ፤አንተም፥ብልጣሶር፥ፍቺውን፡ አስታውቀኝ፥የመንግሥቴ፡ጠቢባን፡ዅሉ፡ፍቺውን፡ያስታውቁኝ፡ዘንድ፡አይችሉምና፤ነገር፡ግን፥የቅዱሳን፡ አማልክት፡መንፈስ፡ባንተ፡ውስጥ፡አለና፡አንተ፡ትችላለኽ።
19የዚያን፡ጊዜ፡ብልጣሶር፡የተባለው፡ዳንኤል፡አንድ፡ሰዓት፡ያኽል፡ዐሰበ፥ልቡም፡ታወከ።ንጉሡም፡ መልሶ፦ብልጣሶር፡ሆይ፥ሕልሙና፡ፍቺው፡አያስቸግርኽ፡አለው።ብልጣሶርም፡መልሶ፡አለ፦ጌታዬ፡ ሆይ፥ሕልሙ፡ለሚጠሉኽ፥ፍቺውም፡ለጠላቶችኽ፡ይኹን።
20ትልቅ፡የነበረው፡የበረታውም፥ቁመቱም፡እስከ፡ሰማይ፡የደረሰው፥መልኩም፡እስከ፡ምድር፡ዅሉ፡ድረስ፡ የታየው፥
21ቅጠሉም፡አምሮ፡የነበረው፥ፍሬውም፡የበዛው፥ለዅሉም፡መብል፡የነበረበት፤በበታቹም፡የምድር፡አራዊት፡ የተቀመጡ፥በቅርንጫፎቹም፡የሰማይ፡ወፎች፡ያደሩበት፡ያየኸው፡ዛፍ፤
22ንጉሥ፡ሆይ፥ርሱ፡ታላቅና፡ብርቱ፡የኾንኽ፡አንተ፡ነኽ፤ታላቅነትኽ፡በዝቷል፥እስከ፡ሰማይም፡ ደርሷል፥ግዛትኽም፡እስከምድር፡ዳርቻ፡ድረስ፡ነው።
23ንጉሡም፡ከሰማይ፡የወረደውንና፦ዛፉን፡ቍረጡ፥አጥፉትም፤ነገር፡ግን፥ጕቶውን፡በምድር፡ውስጥ፡ ተዉት፤በብረትና፡በናስ፡ማሰሪያ፡ታስሮ፡በመስክ፡ውስጥ፡ይቈይ፤በሰማይም፡ጠል፡ይረስርስ፥ሰባት፡ ዘመናትም፡እስኪያልፉበት፡ድረስ፡ዕድል፡ፈንታው፡ከምድር፡አራዊት፡ጋራ፡ይኹን፡ያለውን፡ቅዱስ፡ጠባቂ፡ ማየቱ፤ንጉሥ፡ሆይ፥ፍቺው፡ይህ፡ነው፤
24በጌታዬ፡በንጉሥ፡ላይ፡የወረደው፡የልዑሉ፡ትእዛዝ፡ነው፤
25ልዑሉም፡በሰዎች፡መንግሥት፡ላይ፡እንዲሠለጥን፥ለሚወደ፟ውም፡እንዲሰጠው፡እስክታውቅ፡ድረስ፡ ከሰዎች፡ተለይተኽ፡ትሰደዳለኽ፥መኖሪያኽም፡ከምድር፡አራዊት፡ጋራ፡ይኾናል፥እንደ፡በሬም፡ሣር፡ትበላ፡ ዘንድ፡ትገደዳለኽ፥በሰማይም፡ጠል፡ትረሰርሳለኽ፥ሰባት፡ዘመናትም፡ያልፉብኻል።
26የዛፉንም፡ጕቶ፡ይተዉት፡ዘንድ፡ማዘዙ፥ሥልጣን፡ከሰማያት፡እንደ፡ኾነ፡ካወቅኽ፡በዃላ፡መንግሥትኽ፡ ይቈይልኻል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
27ንጉሥ፡ሆይ፥ስለዚህ፡ምናልባት፡የደኅንነትኽ፡ዘመን፡ይረዝም፡እንደ፡ኾነ፡ምክሬ፡ደስ፡ ያሠኝኽ፤ኀጢአትኽንም፡በጽድቅ፥በደልኽንም፡ለድኻዎች፡በመመጽወት፡አስቀር።
28ይህ፡ዅሉ፡በንጉሡ፡በናቡከደነጾር፡ላይ፡ደረሰ።
29ከዐሥራ፡ኹለት፡ወር፡በዃላ፡በባቢሎን፡ቤተ፡መንግሥት፡ሰገነት፡ላይ፡ይመላለስ፡ነበር።
30ንጉሡም፦ይህች፡እኔ፡በጕልበቴ፡ብርታት፡ለግርማዬ፡ክብር፡የመንግሥት፡መኖሪያ፡እንድትኾን፡ ያሠራዃት፡ታላቂቱ፡ባቢሎን፡አይደለችምን፧ብሎ፡ተናገረ።
31ቃሉም፡ገና፡በንጉሡ፡አፍ፡ሳለ፡ድምፅ፡ከሰማይ፡ወደቀና፦ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡ሆይ፦መንግሥት፡ ከአንተ፡ዘንድ፡ዐለፈች፡ተብሎ፡ለአንተ፡ተነግሯል፤
32ልዑሉም፡በሰዎች፡መንግሥት፡ላይ፡እንዲሠለጥን፥ለሚወደ፟ውም፡እንዲሰጠው፡እስክታውቅ፡ድረስ፡ ከሰዎች፡ተለይተኽ፡ትሰደዳለኽ፥መኖሪያኽም፡ከምድር፡አራዊት፡ጋራ፡ይኾናል፤እንደ፡በሬም፡ሣር፡ትበላ፡ ዘንድ፡ትገደዳለኽ፥ሰባት፡ዘመናትም፡ያልፉብኻል፡አለው።
33በዚያም፡ሰዓት፡ነገሩ፡በናቡከደነጾር፡ላይ፡ደረሰ፤ጠጕሩም፡እንደ፡ንስር፥ጥፍሩም፡እንደ፡ወፎች፡ እስኪረዝም፡ድረስ፡ከሰዎች፡ተለይቶ፡ተሰደደ፥እንደ፡በሬም፡ሣር፡በላ፥አካሉም፡በሰማይ፡ጠል፡ረሰረሰ።
34ዘመኑም፡ከተፈጸመ፡በዃላ፡እኔ፡ናቡከደነጾር፡ዐይኔን፡ወደ፡ሰማይ፡አነሣኹ፥አእምሮዬም፡ ተመለሰልኝ፤ልዑሉንም፡ባረክኹ፥ለዘለዓለምም፡የሚኖረውን፡አመሰገንኹ፡አከበርኹትም፤ግዛቱ፡የዘለዓለም፡ ግዛት፡ነውና፥መንግሥቱም፡ለልጅ፡ልጅ፡ነውና።
35በምድርም፡የሚኖሩ፡ዅሉ፡እንደ፡ምናምን፡ይቈጠራሉ፤በሰማይም፡ሰራዊት፡በምድርም፡ላይ፡በሚኖሩ፡ መካከል፡እንደ፡ፈቃዱ፡ያደርጋል፤እጁንም፡የሚከለክላት፡ወይም፦ምን፡ታደርጋለኽ፧የሚለው፡የለም።
36በዚያን፡ጊዜም፡አእምሮዬ፡ተመለሰልኝ፥ለመንግሥቴም፡ክብር፡ግርማዬና፡ውበቴ፡ወደ፡እኔ፡ ተመለሰ፤አማካሪዎቼና፡መኳንንቶቼም፡ፈለጉኝ፥በመንግሥቴም፡ውስጥ፡ጸናኹ፥ብዙም፡ክብር፡ተጨመረልኝ።
37አኹንም፡እኔ፡ናቡከደነጾር፡የሰማይን፡ንጉሥ፡አመሰግናለኹ፥ታላቅም፡ አደርገዋለኹ፥አከብረውማለኹ።ሥራው፡ዅሉ፡እውነት፥መንገዱም፡ፍርድ፡ነውና፥በትዕቢትም፡የሚኼዱትን፡ ያዋርድ፡ዘንድ፡ይችላልና።