1በባቢሎን፡ንጉሥ፡በብልጣሶር፡በመዠመሪያው፡ዓመት፡ዳንኤል፡በዐልጋው፡ላይ፡ሕልምንና፡የራሱን፡ራእይ፡ አየ፤ከዚያም፡በዃላ፡ሕልሙን፡ጻፈ፥ዋነኛውንም፡ነገር፡ተናገረ።
2ዳንኤልም፡ተናገረ፡እንዲህም፡አለ፦በሌሊት፡በራእይ፡አየኹ፤እንሆም፥አራቱ፡የሰማይ፡ነፋሳት፡በታላቁ፡ ባሕር፡ላይ፡ይጋጩ፡ነበር።
3አራትም፡ታላላቅ፡አራዊት፡ከባሕር፡ወጡ፥እያንዳንዲቱም፡ልዩ፡ልዩ፡ነበረች።
4መዠመሪያዪቱ፡አንበሳ፡ትመስል፡ነበር፥የንስርም፡ክንፍ፡ነበራት፤ክንፎቿም፡ከርሷ፡እስኪነቀሉ፡ድረስ፡ አይ፡ነበር፥ከምድርም፡ከፍ፡ከፍ፡ተደረገች፥እንደ፡ሰውም፡በኹለት፡እግር፡እንድትቆም፡ተደረገች፥የሰውም፡ ልብ፡ተሰጣት።
5እንሆም፥ኹለተኛዪቱ፡ድብ፡የምትመስል፡ሌላ፡አውሬ፡ነበረች፥ባንድ፡ወገንም፡ቆመች፥ሦስትም፡ የጐድን፡ዐጥንቶች፡በአፏ፡ውስጥ፡በጥርሷ፡መካከል፡ነበሩ፤እንደዚህም፦ተነሥተሽ፡እጅግ፡ሥጋ፡ብዪ፡ ተባለላት።
6ከዚህም፡በዃላ፥እንሆ፥ነብር፡የምትመስል፡በዠርባዋም፡ላይ፡አራት፡የወፍ፡ክንፎች፡የነበሯት፡ሌላ፡ አውሬ፡አየኹ፤ለአውሬዪቱም፡አራት፡ራሶች፡ነበሯት፥ግዛትም፡ተሰጣት።
7ከዚህም፡በዃላ፡በሌሊት፡ራእይ፡አየኹ፤እንሆም፥የምታስፈራና፡የምታስደነግጥ፡እጅግም፡ የበረታች፥ታላላቅም፡የብረት፡ጥርሶች፡የነበሯት፡አራተኛ፡አውሬ፡ነበረች፤ትበላና፡ታደቅ፟፡ነበር፥የቀረውንም፡ በእግሯ፡ትረግጥ፡ነበር፤ከርሷም፡በፊት፡ከነበሩት፡አራዊት፡ዅሉ፡የተለየች፡ነበረች፤ዐሥር፡ቀንዶችም፡ ነበሯት።
8ቀንዶችንም፡ተመለከትኹ፤እንሆም፥በመካከላቸው፡ሌላ፡ትንሽ፡ቀንድ፡ወጣ፥በፊቱም፡ከቀደሙት፡ ቀንዶች፡ሦስት፡ተነቃቀሉ፤እንሆም፥በዚያ፡ቀንድ፡እንደ፡ሰው፡ዐይኖች፡የነበሩ፡ዐይኖች፡በትዕቢትም፡ የሚናገር፡አፍ፡ነበሩበት።
9ዙፋኖችም፡እስኪዘረጉ፡ድረስ፡አየኹ፥በዘመናት፡የሸመገለውም፡ተቀመጠ፤ልብሱም፡እንደ፡በረዶ፡ ነጭ፥የራሱም፡ጠጕር፡እንደ፡ጥሩ፡ጥጥ፡ነበረ፤ዙፋኑም፡የእሳት፡ነበልባል፡ነበረ፥መንኰራኵሮቹም፡የሚነድ፟፡ እሳት፡ነበሩ።
10የእሳትም፡ፈሳሽ፡ከፊቱ፡ይፈልቅና፡ይወጣ፡ነበር፤ሺሕ፡ጊዜ፡ሺሕ፡ያገለግሉት፡ነበር፥እልፍ፡አእላፋትም፡ በፊቱ፡ቆመው፡ነበር፤ፍርድም፡ኾነ፥መጻሕፍትም፡ተገለጡ።
11የዚያን፡ጊዜም፡ቀንዱ፡ይናገረው፡ከነበረው፡ከታላቁ፡ቃል፡ድምፅ፡የተነሣ፡አየኹ፤አውሬዪቱም፡ እስክትገደል፥አካሏም፡እስኪጠፋ፡ድረስ፥በእሳትም፡ለመቃጠል፡እስክትሰጥ፡ድረስ፡አየኹ።
12ከቀሩትም፡አራዊት፡ግዛታቸው፡ተወሰደ፤የሕይወታቸው፡ዕድሜ፡ግን፡እስከ፡ዘመንና፡እስከ፡ጊዜ፡ድረስ፡ ረዘመ።
13በሌሊት፡ራእይ፡አየኹ፤እንሆም፥የሰው፡ልጅ፡የሚመስል፡ከሰማይ፡ደመናት፡ጋራ፡መጣ፡በዘመናት፡ ወደሸመገለውም፡ደረሰ፤ወደ፡ፊቱም፡አቀረቡት።
14ወገኖችና፡አሕዛብ፡በልዩ፡ልዩ፡ቋንቋም፡የሚናገሩ፡ዅሉ፡ይገዙለት፡ዘንድ፡ግዛትና፡ክብር፡መንግሥትም፡ ተሰጠው፤ግዛቱም፡የማያልፍ፡የዘለዓለም፡ግዛት፡ነው፥መንግሥቱም፡የማይጠፋ፡ነው።
15በእኔም፡በዳንኤል፡በሥጋዬ፡ውስጥ፡መንፈሴ፡ደነገጠች፥የራሴም፡ራእይ፡አስቸገረኝ።
16በዚያም፡ከቆሙት፡ወደ፡አንዱ፡ቀርቤ፡ስለዚህ፡ዅሉ፡እውነቱን፡ጠየቅኹት፤ርሱም፡ነገረኝ፥የነገሩንም፡ ፍቺ፡አስታወቀኝ።
17እነዚህ፡አራቱ፡ታላላቅ፡አራዊት፡ከምድር፡የሚነሡ፡አራት፡ነገሥታት፡ናቸው።
18ነገር፡ግን፥የልዑሉ፡ቅዱሳን፡መንግሥቱን፡ይወስዳሉ፥እስከ፡ዘለዓለም፡ዓለምም፡መንግሥቱን፡ይወርሳሉ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19ከዚህም፡በዃላ፡ከቀሩት፡ዅሉ፡ተለይታ፡እጅግ፡ስለምታስፈራው፥ጥርሶቿም፡የብረት፡ጥፍራዎቿም፡የናስ፡ ስለኾኑት፥ስለምትበላውና፡ስለምታደቀ፟ው፡የቀረውንም፡በእግሯ፡ስለምትረግጠው፡ስለ፡አራተኛዪቱ፡አውሬ፥
20በራሷም፡ላይ፡ስለነበሩ፡ስለ፡ዐሥር፡ቀንዶች፥በዃላም፡ስለ፡ወጣው፥በፊቱም፡ሦስቱ፡ስለ፡ ወደቁ፥ዐይኖችና፡ትዕቢት፡የተናገረ፡አፍ፡ስለ፡ነበሩት፥መልኩም፡ከሌላዎች፡ስለ፡በለጠ፡ስለ፡ሌላው፡ቀንድ፡ እውነቱን፡ለማወቅ፡ፈቀድኹ።
21እንሆም፥ያ፡ቀንድ፡ከቅዱሳን፡ጋራ፡ሲዋጋ፡አየኹ፥
22በዘመናት፡የሸመገለው፡እስኪመጣ፡ድረስ፥ፍርድም፡ለልዑሉ፡ቅዱሳን፡እስኪሰጥ፡ድረስ፥ቅዱሳኑም፡ መንግሥቱን፡የሚወስዱበት፡ዘመን፡እስኪመጣ፡ድረስ፡አሸነፋቸውም።
23እንዲህም፡አለ፦አራተኛዪቱ፡አውሬ፡በምድር፡ላይ፡አራተኛ፡መንግሥት፡ትኾናለች፤ርሱም፡ ከመንግሥታት፡ዅሉ፡የተለየ፡ይኾናል፥ምድሪቱንም፡ዅሉ፡ይበላል፥ይረግጣታል፡ያደቃ፟ትማል።
24ዐሥሩም፡ቀንዶች፡ከዚያ፡መንግሥት፡የሚነሡ፡ዐሥር፡ነገሥታት፡ናቸው፤ከነርሱም፡በዃላ፡ሌላ፡ ይነሣል፥ርሱም፡ከፊተኛዎች፡የተለየ፡ይኾናል፥ሦስቱንም፡ነገሥታት፡ያዋርዳል።
25በልዑሉም፡ላይ፡ቃልን፡ይናገራል፥የልዑልንም፡ቅዱሳን፡ይሰባብራል፥ዘመናትንና፡ሕግን፡ይለውጥ፡ዘንድ፡ ያስባል፤እስከ፡ዘመንና፡እስከ፡ዘመናት፡እስከ፡እኩሌታ፡ዘመንም፡በእጁ፡ይሰጣሉ።
26ነገር፡ግን፥ፍርድ፡ይኾናል፥እስከ፡ፍጻሜም፡ድረስ፡ያፈርሱትና፡ያጠፉት፡ዘንድ፡ግዛቱን፡ያስወግዱታል።
27መንግሥትም፡ግዛትም፡ከሰማይም፡ዅሉ፡በታች፡ያሉ፡የመንግሥታት፡ታላቅነት፡ለልዑሉ፡ቅዱሳን፡ሕዝብ፡ ይሰጣል፤መንግሥቱ፡የዘለዓለም፡መንግሥት፡ነው፥ግዛቶችም፡ዅሉ፡ይገዙለታል፡ይታዘዙለትማል።
28የነገሩም፡ፍጻሜ፡እስከዚህ፡ድረስ፡ነው።እኔም፡ዳንኤል፡በዐሳቤ፡እጅግ፡ተቸገርኹ፥ፊቴም፡ ተለወጠብኝ፤ዳሩ፡ግን፡ነገሩን፡በልቤ፡ጠብቄያለኹ።