1በከለዳውያን፡መንግሥት፡ላይ፡በነገሠ፥ከሜዶን፡ዘር፡በነበረ፡በአሕሻዊሮስ፡ልጅ፡በዳርዮስ፡በመዠመሪያ፡ ዓመት፥
2በነገሠ፡በመዠመሪያው፡ዓመት፡እኔ፡ዳንኤል፡የኢየሩሳሌም፡መፍረስ፡የሚፈጸምበትን፡ሰባውን፡ ዓመት፥እግዚአብሔር፡በቃሉ፡ለነቢዩ፡ለኤርምያስ፡የተናገረውን፡የዓመቱን፡ቍጥር፡በመጽሐፍ፡አስተዋልኹ።
3ማቅ፡ለብሼ፡በዐመድም፡ላይ፡ኾኜ፡ስጾም፡እጸልይና፡እለምን፡ዘንድ፡ፊቴን፡ወደ፡ጌታ፡ወደ፡አምላክ፡ አቀናኹ።
4ወደ፡አምላኬም፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ጸለይኹ፥ተናዝዤም፡እንዲህ፡አልኹ፦ጌታ፡ሆይ፥ከሚወዱኽና፡ ትእዛዝኽን፡ከሚፈጽሙ፡ጋራ፡ቃል፡ኪዳንንና፡ምሕረትን፡የምትጠብቅ፡ታላቅና፡የምታስፈራ፡አምላክ፡ሆይ፥
5ኀጢአትን፡ሠርተናል፥በድለንማል፥ክፋትንም፡አድርገናል፥ዐምፀንማል፥ከትእዛዝኽና፡ከፍርድኽም፡ፈቀቅ፡ ብለናል፤
6በስምኽም፡ለነገሥታታችንና፡ለአለቃዎቻችን፡ለአባቶቻችንም፡ለአገሩም፡ሕዝብ፡ዅሉ፡የተናገሩትን፡ ባሪያዎችኽን፡ነቢያትን፡አልሰማንም።
7ጌታ፡ሆይ፥ጽድቅ፡ለአንተ፡ነው፤እንደ፡ዛሬም፡ለእኛ፡ለይሁዳ፡ሰዎችና፡በኢየሩሳሌም፡ለሚቀመጡ፡ ለእስራኤልም፡ዅሉ፡በቅርብና፡በሩቅም፡ላሉት፡አንተን፡በበደሉበት፡በበደላቸው፡ምክንያት፡በበተንኽበት፡አገር፡ ዅሉ፡የፊት፡ዕፍረት፡ነው።
8ጌታ፡ሆይ፥ባንተ፡ላይ፡ኀጢአት፡ስለ፡ሠራን፡ለእኛና፡ለነገሥታታችን፡ለአለቃዎቻችንና፡ለአባቶቻችንም፡ የፊት፡ዕፍረት፡ነው።
10በርሱ፡ላይ፡ምንም፡እንኳ፡ያመፅን፡ብንኾን፥በባሪያዎቹም፡በነቢያት፡እጅ፡በፊታችን፡ባኖረው፡በሕጉ፡ እንኼድ፡ዘንድ፡የአምላካችንን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ምንም፡እንኳ፡ባንሰማ፥ለጌታ፡ለአምላካችን፡ምሕረትና፡ ይቅርታ፡ነው።
11እስራኤልም፡ዅሉ፡ሕግኽን፡ተላልፈዋል፥ቃልኽንም፡እንዳይሰሙ፡ፈቀቅ፡ብለዋል፤በርሱ፡ላይ፡ኀጢአት፡ ሠርተናልና፥በእግዚአብሔር፡ባሪያ፡በሙሴ፡ሕግ፡የተጻፈው፡መሐላና፡ርግማን፡ፈሰሰብን።
12እጅግ፡ክፉ፡ነገርንም፡በእኛ፡ላይ፡በማምጣቱ፡በላያችንና፡በእኛ፡ዘንድ፡በተሾሙት፡ፈራጆቻችን፡ላይ፡ የተናገረውን፡ቃል፡አጸና፤በኢየሩሳሌምም፡ላይ፡እንደተደረገው፡ያለ፡ነገር፡ከቶ፡ከሰማይ፡ዅሉ፡በታች፡ አልተደረገም።
13በሙሴም፡ሕግ፡እንደ፡ተጻፈ፡ይህ፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡መጣብን፤ከኀጢአታችንም፡እንመለስ፡ እውነትኽንም፡እናስብ፡ዘንድ፡ወደአምላካችን፡ወደእግዚአብሔር፡ፊት፡አልለመንንም።
14ስለዚህም፡እግዚአብሔር፡ክፉ፡ነገሩን፡ጠብቆ፡በእኛ፡ላይ፡አመጣ፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፡ በሚሠራው፡ሥራ፡ዅሉ፡ጻድቅ፡ነውና፥እኛም፡ቃሉን፡አልሰማንምና።
15አኹንም፡ሕዝብኽን፡ከግብጽ፡ምድር፡በበረታች፡እጅ፡ያወጣኽ፥እንደ፡ዛሬም፡ቀን፡ዝና፡ለአንተ፡ ያገኘኽ፡ጌታ፡አምላካችን፡ሆይ፥ኀጢአትን፡ሠርተናል፥ክፋትንም፡አድርገናል።
16ጌታ፡ሆይ፥ስለ፡ኀጢአታችንና፡ስላባቶቻችን፡በደል፡ኢየሩሳሌምና፡ሕዝብኽ፡በዙሪያችን፡ላሉት፡ዅሉ፡ መሰደቢያ፡ኾነዋልና፥እንደ፡ጽድቅኽ፡ዅሉ፡ቍጣኽና፡መዓትኽ፡ከከተማኽ፡ከኢየሩሳሌም፡ከቅዱስ፡ተራራኽ፡ እንዲመለስ፡እለምንኻለኹ።
17አኹንም፥አምላካችን፡ሆይ፥የባሪያኽን፡ጸሎትና፡ልመናውን፡ስማ፤ጌታ፡ሆይ፥በፈረሰው፡በመቅደስኽ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ላይ፡ስለ፡አንተ፡ስትል፡ፊትኽን፡አብራ።
18አምላኬ፡ሆይ፥በፊትኽ፡የምንለምን፡ስለ፡ብዙ፡ምሕረትኽ፡ነው፡እንጂ፡ስለ፡ጽድቃችን፡አይደለምና፡ ዦሮኽን፡አዘንብለኽ፡ስማ፤ዐይንኽን፡ገልጠኽ፡ጥፋታችንና፡ስምኽ፡የተጠራባትን፡ከተማ፡ተመልከት።
19አቤቱ፥ስማ፤አቤቱ፥ይቅር፡በል፤አቤቱ፥አድምጥና፡አድርግ፤አምላኬ፡ሆይ፥ስምኽ፡በከተማኽና፡ በሕዝብኽ፡ላይ፡ተጠርቷልና፥ስለ፡ራስኽ፡አትዘግይ።
20እኔም፡ገና፡ስናገር፡ስጸልይ፥በኀጢአቴና፡በሕዝቤም፡በእስራኤል፡ኀጢአት፡ስናዘዝ፥በአምላኬም፡ በእግዚአብሔር፡ፊት፡ስለተቀደሰው፡ስለአምላኬ፡ተራራ፡ስለምን፥
21ገናም፡በጸሎት፡ስናገር፡አስቀድሜ፡በራእይ፡አይቼው፡የነበረው፡ሰው፡ገብርኤል፥እንሆ፥እየበረረ፡ መጣ፤በማታም፡መሥዋዕት፡ጊዜ፡ዳሰሰኝ።
22አስተማረኝም፥ተናገረኝም፡እንዲህም፡አለ፦ዳንኤል፡ሆይ፥ጥበብንና፡ማስተዋልን፡እሰጥኽ፡ዘንድ፡ አኹን፡መጥቻለኹ።
23አንተ፡እጅግ፡የተወደድኽ፡ነኽና፥በልመናኽ፡መዠመሪያ፡ላይ፡ትእዛዝ፡ወጥቷል፥እኔም፡እነግርኽ፡ ዘንድ፡መጥቻለኹ፤አኹንም፡ነገሩን፡መርምር፥ራእዩንም፡አስተውል።
24ዐመፃን፡ይጨርስ፥ኀጢአትንም፡ይፈጽም፥በደልንም፡ያስተሰርይ፥የዘለዓለምን፡ጽድቅ፡ያገባ፥ራእይንና፡ ትንቢትን፡ያትም፥ቅዱሰ፡ቅዱሳኑንም፡ይቀባ፡ዘንድ፡በሕዝብኽና፡በቅድስት፡ከተማኽ፡ላይ፡ሰባ፡ሱባዔ፡ ተቀጥሯል።
25ስለዚህ፥ዕወቅ፡አስተውልም፤ኢየሩሳሌምን፡መጠገንና፡መሥራት፡ትእዛዙ፡ከሚወጣበት፡ዠምሮ፡እስከ፡ አለቃው፡እስከ፡መሲሕ፡ድረስ፡ሰባት፡ሱባዔና፡ስድሳ፡ኹለት፡ሱባዔ፡ይኾናል፤ርሷም፡በጭንቀት፡ዘመን፡ ከጐዳናና፡ከቅጥር፡ጋራ፡ትሠራለች።
26ከስድሳ፡ኹለት፡ጊዜ፡ሰባትም፡በዃላ፡መሲሕ፡ይገደላል፥በርሱም፡ዘንድ፡ምንም፡የለም፤የሚመጣውም፡ አለቃ፡ሕዝብ፡ከተማዪቱንና፡መቅደሱን፡ያጠፋሉ፤ፍጻሜውም፡በጐርፍ፡ይኾናል፥እስከ፡መጨረሻም፡ድረስ፡ ጦርነት፡ይኾናል፤ጥፋትም፡ተቀጥሯል።
27ርሱም፡ከብዙ፡ሰዎች፡ጋራ፡ጽኑ፡ቃል፡ኪዳን፡ላንድ፡ሱባዔ፡ያደርጋል፤በሱባዔውም፡እኩሌታ፡ መሥዋዕቱንና፡ቍርባኑን፡ያስቀራል፤በርኵሰትም፡ጫፍ፡ላይ፡አጥፊው፡ይመጣል፤እስከተቈረጠውም፡ፍጻሜ፡ ድረስ፡መቅሠፍት፡በአጥፊው፡ላይ፡ይፈሳ፟ል።