1ንጉሡና፡ሐማም፡ከንግሥቲቱ፡ከአስቴር፡ጋራ፡ለመጠጣት፡መጡ።
2በኹለተኛውም፡ቀን፡ንጉሡ፡በወይኑ፡ጠጅ፡ግብዣ፡ሳለ፡አስቴርን፦ንግሥት፡አስቴር፡ ሆይ፥የምትለምኚኝ፡ምንድር፡ነው፧ይሰጥሻል፤የምትሺውስ፡ምንድር፡ነው፧እስከመንግሥቴ፡እኩሌታ፡እንኳ፡ ቢኾን፡ይደረግልሻል፡አላት።
3ንግሥቲቱም፡አስቴር፡መልሳ፦ንጉሥ፡ሆይ፥ባንተ፡ዘንድ፡ሞገስ፡አግኝቼ፡እንደ፡ኾነ፥ንጉሡንም፡ደስ፡ ቢያሠኘው፥ሕይወቴ፡በልመናዬ፡ሕዝቤም፡በመሻቴ፡ይሰጠኝ፤
4እኔና፡ሕዝቤ፡ለመጥፋትና፡ለመገደል፡ለመደምሰስም፡ተሸጠናልና፦ባሪያዎች፡ልንኾን፡ተሸጠን፡እንደ፡ ኾነ፡ዝም፡ባልኹ፡ነበር፤የኾነ፡ኾኖ፡ጠላቱ፡የንጉሡን፡ጕዳት፡ለማቅናት፡ባልቻለም፡ነበር፡አለች።
5ንጉሡም፡አርጤክስስ፡ንግሥቲቱን፡አስቴርን፦ይህን፡ያደርግ፡ዘንድ፡በልቡ፡የደፈረ፡ማን፡ነው፧ርሱስ፡ ወዴት፡ነው፧ብሎ፡ተናገራት።
6አስቴርም፦ያ፡ጠላትና፡ባለጋራ፡ሰው፡ክፉው፡ሐማ፡ነው፡አለች።ሐማም፡በንጉሡና፡በንግሥቲቱ፡ፊት፡ ደነገጠ።
7ንጉሡም፡ተቈጥቶ፡የወይን፡ጠጅ፡ከመጠጣቱ፡ተነሣ፥ወደንጉሡም፡ቤት፡አታክልት፡ውስጥ፡ ኼደ።ሐማም፡ከንጉሡ፡ዘንድ፡ክፉ፡ነገር፡እንደ፡ታሰበበት፡አይቷልና፥ከንግሥቲቱ፡ከአስቴር፡ሕይወቱን፡ ይለምን፡ዘንድ፡ቆመ።
8ንጉሡም፡ከቤቱ፡አታክልት፡ወደ፡ወይን፡ጠጁ፡ግብዣ፡ስፍራ፡ተመለሰ፤ሐማም፡አስቴር፡ባለችበት፡ ዐልጋ፡ላይ፡ወድቆ፡ነበር።ንጉሡም፦ደግሞ፡በቤቴ፡በእኔ፡ፊት፡ንግሥቲቱን፡ይጋፋታልን፧አለ።ይህም፡ ቃል፡ከንጉሡ፡አፍ፡በወጣ፡ጊዜ፡የሐማን፡ፊት፡ሸፈኑት።
9በንጉሡም፡ፊት፡ካሉት፡ጃን፡ደረባዎች፡አንዱ፡ሐርቦና፦እንሆ፥ሐማ፡ለንጉሡ፡በጎ፡ለተናገረው፡ ለመርዶክዮስ፡ያሠራው፡ርዝመቱ፡ዐምሳ፡ክንድ፡የኾነው፡ግንድ፡በሐማ፡ቤት፡ተተክሏል፡ አለ።ንጉሡም፦በርሱ፡ላይ፡ስቀሉት፡አለ።
10ሐማንም፡ለመርዶክዮስ፡ባዘጋጀው፡ግንድ፡ላይ፡ሰቀሉት፤በዚያም፡ጊዜ፡የንጉሡ፡ቍጣ፡በረደ።