1የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2አንተ፡የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ስለ፡ጢሮስ፡ሙሾ፡አድርግ፥
3በባሕር፡መግቢያ፡የምትኖር፡በብዙም፡ደሴቶች፡ላይ፡ከሚኖሩ፡አሕዛብ፡ጋራ፡ንግድን፡የምታደርግ፡ ጢሮስንም፡እንዲህ፡በላት፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ጢሮስ፡ሆይ፥አንቺ።በውበት፡ፍጹም፡ነኝ፡ ብለሻል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
4ዳርቻሽ፡በባሕር፡ውስጥ፡ነው፤ሠሪዎችሽ፡ውበትሽን፡ፈጽመዋል።
5ሳንቃዎችሽን፡ዅሉ፡ከሳኔር፡ጥድ፡ሠርተዋል፥ደቀልንም፡ይሠሩልሽ፡ዘንድ፥ከሊባኖስ፡ዝግባ፡ወስደዋል።
6ከባሳን፡ኮምቦል፡መቅዘፊያሽን፡ሠርተዋል፥በዝኆን፡ጥርስ፡ከታሻበ፡ከኪቲም፡ደሴቶች፡ዛፍ፡ መቀመጫዎችሽን፡ሠርተዋል።
7ዐላማ፡እንዲኾንልሽ፡ሸራሽ፡ከግብጽ፡በፍታና፡ከወርቅ፡ዘቦ፡ተሠርቷል፥መደረቢያሽም፡ከኤሊሳ፡ደሴቶች፡ ሰማያዊና፡ቀይ፡ሐር፡ተሠርቷል።
8የሲዶናና፡የአራድ፡ሰዎች፡ቀዛፎችሽ፡ነበሩ፤ጢሮስ፡ሆይ፥ጥበበኛዎችሽ፡ባንቺ፡ዘንድ፡ነበሩ፡ የመርከቦችሽም፡መሪዎች፡ነበሩ።
9ባንቺ፡ውስጥ፡የነበሩ፡የጌባል፡ሽማግሌዎችና፡ጥበበኛዎቿ፡ስብራትሽን፡ይጠግኑ፡ነበር፤ከአንቺም፡ጋራ፡ ይነግዱ፡ዘንድ፥የባሕር፡መርከቦች፡ዅሉና፡መርከበኛዎቻቸው፡በመካከልሽ፡ነበሩ።
10ፋርስና፡ሉድ፡ፉጥም፡በሰራዊትሽ፡ሰልፈኛዎችሽ፡ነበሩ፤ጋሻና፡ራስ፡ቍርም፡ባንቺ፡ውስጥ፡ያንጠለጥሉ፡ ነበር፤እነርሱም፡ውበትሽን፡ሰጡ።
11የአራድ፡ሰዎችና፡ሰራዊቶችሽ፡በቅጥሮችሽ፡ላይ፡በዙሪያ፡ነበሩ፥ገማዳውያንም፡በግንቦችሽ፡ውስጥ፡ ነበሩ፤ጋሻቸውንም፡በዙሪያ፡በቅጥርሽ፡ላይ፡አንጠለጠሉ፥ውበትሽንም፡ፈጽመዋል።
12ከብልጥግናሽ፡ዅሉ፡ብዛት፡የተነሣ፡ተርሴስ፡ነጋዴሽ፡ነበረች፤በብርና፡በብረት፡በቈርቈሮና፡በርሳስ፡ስለ፡ አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ነበር።
13ያዋንና፡ቶቤል፡ሞሳሕም፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ፤የሰዎችን፡ነፍሳትና፡የናሱን፡ዕቃ፡ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ ይነግዱ፡ነበር።
14ከቴርጋማ፡ቤትም፡የነበሩት፡ሰዎች፡በፈረሶችና፡በፈረሰኛዎች፡በበቅሎዎችም፡ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ ነበር።
15የድዳን፡ሰዎች፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ።ብዙ፡ደሴቶች፡የእጅሽ፡ገበያዎች፡ነበሩ፤ይለውጡ፡ዘንድ፥የዝኆን፡ ጥርስና፡ዞጲ፡አመጡልሽ።
16ከሥራሽ፡ብዛት፡የተነሣ፡ሶርያ፡ነጋዴሽ፡ነበረች፡በበሉርና፡በቀይ፡ሐር፡በወርቀ፡ዘቦም፡በጥሩ፡በፍታም፡ በዛጐልም፡በቀይ፡ዕንቍም፡ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ነበር።
17ይሁዳና፡የእስራኤል፡ምድር፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ፤የሚኒትን፡ስንዴ፡ጣፋጭም፡ዕንጐቻ፥ማር፡ዘይትም፡ በለሳንም፡ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ነበር።
18ከሥራሽ፡ብዛትና፡ከብልጥግናሽ፡ዅሉ፡ብዛት፡የተነሣ፡ደማስቆ፡ነጋዴሽ፡ነበረች፤በኬልቦን፡የወይን፡ ጠጅ፡በነጭም፡በግ፡ጠጕር፡ይነግዱ፡ነበር።
19ዌንዳንና፡ያዋን፡ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ነበር፤ከኦሴል፡የተሠራ፡ብረትና፡ብርጕድ፣ቀረፋም፡ ሸቀጥሽ፡ነበረ።
20ድዳን፡በከብት፡ላይ፡ለመቀመጥ፡በመረሻት፡ነጋዴሽ፡ነበረች።
21ዐረብና፡የቄዳር፡አለቃዎች፡ዅሉ፡የእጅሽ፡ነጋዴዎች፡ነበሩ፤በጠቦቶችና፡በአውራ፡በጎች፡በፍየሎችም፡ በእነዚህ፡ከአንቺ፡ጋራ፡ይነግዱ፡ነበር።
22የሳባና፡የራዕማ፡ነጋዴዎች፡እነዚህ፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ፤በጥሩ፡ሽቶና፡በክብር፡ድንጋይ፡ዅሉ፡በወርቅም፡ ስለ፡አንቺ፡ሸቀጥ፡ይነግዱ፡ነበር።
23ካራንና፡ካኔ፡ዔዴንም፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ፤አሶርና፡ኪልማድ፡ነጋዴዎችሽ፡ነበሩ።
24እነዚህ፡ባማረ፡ልብስ፡በሰማያዊ፡ካባ፡በወርቀ፡ዘቦም፥በዝግባ፡በተሠራች፡በገመድም፡በታሰረች፡ በግምጃም፡በተሞላች፡ሳጥን፡በገበያሽ፡ይነግዱ፡ነበር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
25የተርሴስ፡መርከቦች፡ሸቀጥሽን፡የሚሸከሙ፡ነበሩ፤አንቺም፡ተሞልተሽ፡ነበር፡በባሕርም፡ውስጥ፡እጅግ፡ ከበርሽ።
26ቀዛፊዎችሽ፡ወደ፡ትልቁ፡ውሃ፡አመጡሽ፤የምሥራቅ፡ነፋስ፡በባሕር፡ውስጥ፡ሰበረሽ።
27ብልጥግናሽና፡ሸቀጥሽ፡ንግድሽም፡መርከበኛዎችሽም፡መርከብ፡መሪዎችሽም፡ሰባራሽንም፡የሚጠግኑ፡ ነጋዴዎችሽም፡ባንቺም፡ዘንድ፡ያሉ፡ሰልፈኛዎችሽ፡ዅሉ፡በውስጥሽ፡ካሉት፡ጉባኤ፡ዅሉ፡ጋራ፡በወደቅሽበት፡ ቀን፡በባሕር፡ውስጥ፡ይወድቃሉ።
28ከመርከብ፡መሪዎች፡ጩኸት፡ድምፅ፡የተነሣ፡በዙሪያሽ፡ያሉ፡ዅሉ፡ይንቀጠቀጣሉ።
29ቀዛፊዎችም፡ዅሉ፡መርከበኛዎችም፡መርከብ፡መሪዎችም፡ዅሉ፡ከመርከቦቻቸው፡ይወርዳሉ፡በመሬትም፡ ላይ፡ይቆማሉ፤
30ድምፃቸውንም፡ባንቺ፡ላይ፡ያሰማሉ፥ምርር፡ብለውም፡ይጮኻሉ፥በራሳቸውም፡ላይ፡ትቢያ፡ ይነሰንሳሉ፥በዐመድም፡ውስጥ፡ይንከባለላሉ፤
31ስለ፡አንቺም፡የራሳቸውን፡ጠጕር፡ይላጫሉ፡ማቅም፡ያሸርጣሉ፡በነፍስ፡ምሬትም፡ስለ፡አንቺ፡መራራ፡ ልቅሶ፡ያለቅሳሉ።
32በትካዜያቸውም፡ልቅሶ፡ያነሡልሻል፥ስለ፡አንቺም፡ሙሾ፡ያሞሻሉ፡እንዲህም፡ይላሉ፦በባሕር፡መካከል፡ ጠፍቶ፡እንደ፡ቀረ፡እንደ፡ጢሮስ፡ያለ፡ማን፡ነው፧
33ሸቀጥሽ፡ከባሕር፡በወጣ፡ጊዜ፡ብዙ፡አሕዛብን፡አጥግበሻል፤በብልጥግናሽና፡በንግድሽ፡ብዛት፡የምድርን፡ ነገሥታት፡ባለጠጋዎች፡አድርገሻል።
34አኹን፡ግን፡በጥልቅ፡ውሃ፡ውስጥ፡በባሕር፡ተሰብረሻል፡ንግድሽና፡ጉባኤሽ፡ዅሉ፡በመካከልሽ፡ ወድቀዋል።
35በደሴቶች፡የሚኖሩ፡ዅሉ፡ተደንቀውብሻል፥ነገሥታታቸውም፡እጅግ፡ፈርተዋል፡ፊታቸውም፡ተለውጧል።
36የአሕዛብ፡ነጋዴዎች፡አፏጩብሽ፤አንቺ፡ለድንጋጤ፡ኾነሻል፥እስከ፡ዘለዓለምም፡አትገኚም።