1እንዲህም፡ኾነ፤በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ዓመት፡በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ወር፡ከወሩም፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ስለግብጽ፡ንጉሥ፡ስለ፡ፈርዖን፡ሙሾ፡አሙሽ፥እንዲህም፡በለው፦የአሕዛብን፡ አንበሳ፡መስለኽ፡ነበር፥ነገር፡ግን፥እንደ፡ባሕር፡ዘንዶ፡ኾነኻል፤በወንዞችኽም፡ወጥተኻል፥ውሃውንም፡ በእግርኽ፡አደፍርሰኻል፥ወንዞችኽንም፡አሳድፈኻል።
3ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በብዙ፡አሕዛብ፡ጉባኤ፡መረቤን፡እዘረጋብኻለኹ፥እነርሱም፡ በመረቤ፡ያወጡኻል።
4በምድርም፡ላይ፡እተውኻለኹ፥በምድረ፡በዳም፡ፊት፡እጥልኻለኹ፥የሰማይንም፡ወፎች፡ዅሉ፡ አሳርፍብኻለኹ፥የምድርንም፡አራዊት፡ዅሉ፡ከአንተ፡አጠግባቸዋለኹ።
5ሥጋኽን፡በተራራዎች፡ላይ፡አደርጋለኹ፡ሸለቆዎቹንም፡በሬሳኽ፡ክምር፡እሞላለኹ።
6የምትዋኝባትንም፡ምድር፡እስከ፡ተራራዎች፡ድረስ፡በደምኽ፡አጠጣለኹ፥መስኖችም፡ከአንተ፡ይሞላሉ።
7ባጠፋኹኽም፡ጊዜ፡ሰማዮችን፡እሸፍናለኹ፥ከዋክብትንም፡አጨልማለኹ፤ፀሓዩንም፡በደመና፡ እሸፍናለኹ፥ጨረቃም፡ብርሃኑን፡አይሰጥም።
8የሰማይን፡ብርሃኖች፡ዅሉ፡በላይኽ፡አጨልማለኹ፥በምድርኽም፡ላይ፡ጨለማ፡አደርጋለኹ፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።
9በማታውቃቸውም፡አገሮች፡ባሉ፡በአሕዛብ፡ዘንድ፡ጥፋትኽን፡ባመጣኹ፡ጊዜ፡የብዙ፡ሕዝብን፡ልብ፡ አስጨንቃለኹ።
10ብዙም፡አሕዛብን፡አስደንቅብኻለኹ፡ሰይፌንም፡በፊታቸው፡ባወዛወዝኹ፡ጊዜ፡ነገሥታታቸው፡ስለ፡አንተ፡ እጅግ፡አድርገው፡ይፈራሉ፤በወደቅኽበትም፡ቀን፡እያንዳንዱ፡ስለ፡ነፍሱ፡በየጊዜው፡ዅሉ፡ይንቀጠቀጣል።
11ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦የባቢሎን፡ንጉሥ፡ሰይፍ፡ይመጣብኻል።
12በኀያላን፡ሰይፍ፡የሕዝብኽን፡ብዛት፡እጥላለኹ፤ዅሉ፡የአሕዛብ፡ጨካኞች፡ናቸው፤የግብጽንም፡ትዕቢት፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ያጠፋሉ፥ብዛቷም፡ዅሉ፡ይጠፋል።
13በብዙም፡ውሃ፡አጠገብ፡ያሉትን፡እንስሳዎች፡ዅሉ፡አጠፋለኹ፤ከእንግዲህም፡ወዲያ፡የሰው፡እግር፡ አያደፈርሰውም፡የእንስሳም፡ኰቴ፡አይረግጠውም።
14በዚያን፡ጊዜ፡ውሃቸውን፡አጠራለኹ፥ወንዞቻቸውም፡እንደ፡ዘይት፡እንዲፈሱ፟፡አደርጋለኹ፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።
15የግብጽንም፡ምድር፡ባድማና፡ውድማ፡ባደረግኹ፡ጊዜ፥ሞላዋንም፡ያጣች፡ምድር፡ባደረግዃት፡ ጊዜ፥የሚኖሩባትንም፡ዅሉ፡በቀሠፍኹ፡ጊዜ፥እኔ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ።
16የሚያለቅሱበት፡ልቅሶ፡ይህ፡ነው፤የአሕዛብ፡ቈነዣዥት፡ያለቅሱበታል፤ስለ፡ግብጽና፡ስለ፡ብዛቷ፡ዅሉ፡ ያለቅሱበታል፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
17እንዲህም፡ኾነ፤በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ዓመት፡ከወሩም፡በዐሥራ፡ዐምስተኛው፡ቀን፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
18የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ስለግብጽ፡ብዛት፡ዋይ፡በል፥ርሷንና፡የብርቱዎችን፡አሕዛብ፡ሴቶች፡ልጆች፡ወደ፡ ጕድጓድ፡ከሚወርዱ፡ጋራ፡ወደ፡ታችኛው፡ምድር፡ጣላቸው።
19በውበት፡የምትበልጪው፡ማን፡ነው፧ውረጂ፡ካልተገረዙትም፡ጋራ፡ተኚ።
20በሰይፍ፡በተገደሉት፡መካከል፡ይወድቃሉ፤ለሰይፍ፡ተሰጥታለች፤ርሷንና፡ብዛቷን፡ዅሉ፡ጐትቱ።
21የኀያላን፡አለቃዎች፡በሲኦል፡ውስጥ፡ኾነው፡ከረዳቶቹ፡ጋራ፡ይናገሩታል፤በሰይፍም፡የተገደሉት፡ ያልተገረዙ፡ወርደው፡ተኝተዋል።
22አሶርና፡ጉባኤዋ፡ዅሉ፡በዚያ፡አሉ፤መቃብራቸው፡በዙሪያቸው፡ነው፤ዅሉም፡በሰይፍ፡ወድቀው፡ ተገደሉ።
23መቃብራቸው፡በጕድጓዱ፡በውስጠኛው፡ክፍል፡ነው፥ጉባኤዋም፡በመቃብሯ፡ዙሪያ፡ነው፤በሕያዋን፡ ምድር፡ያስፈሩ፡ዅሉ፡በሰይፍ፡ወድቀው፡ተገድለዋል።
24ዔላምም፡በዚያ፡አለች፡ብዛቷም፡ዅሉ፡በመቃብሯ፡ዙሪያ፡ነው፤በሕያዋን፡ምድር፡ያስፈሩ፡ዅሉ፡ በሰይፍ፡ወድቀው፡ተገድለዋል፡ሳይገረዙም፡ወደ፡ታችኛው፡ምድር፡ወርደዋል፥ወደ፡ጕድጓድም፡ከሚወርዱ፡ ጋራ፡ዕፍረታቸውን፡ተሸክመዋል።
25በተገደሉት፡መካከል፡ከብዛቷ፡ዅሉ፡ጋራ፡መኝታን፡አድርገውላታል፤መቃብሯ፡በዙሪያዋ፡ነው፥ዅሉም፡ ያልተገረዙና፡በሰይፍ፡የተገደሉ፡ናቸው፤በሕያዋንም፡ምድር፡ያስፈሩ፡ነበር፡ወደ፡ጕድጓድም፡ከሚወርዱ፡ጋራ፡ ዕፍረታቸውን፡ተሸክመዋል፥በተገደሉትም፡መካከል፡ተሰጥተዋል።
26ሞሳሕና፡ቶቤል፡ብዛታቸውም፡ዅሉ፡በዚያ፡አሉ፡መቃብራቸውም፡በዙሪያቸው፡ነው፤ዅሉም፡ሳይገረዙ፡ በሰይፍ፡ተገድለዋል፤በሕያዋን፡ምድር፡ያስፈሩ፡ነበርና።
27በሕያዋንም፡ምድር፡ኀያላኑን፡ያስፈሩ፡ነበርና፥መሣሪያቸውን፡ይዘው፡ወደ፡ሲኦል፡ ከወረዱ፥ሰይፋቸውንም፡ከራሳቸው፡በታች፡ካደረጉ፥ኀጢአታቸውም፡በዐጥንታቸው፡ላይ፡ከኾነ፡ጋራ፡ከወደቁ፡ ካልተገረዙ፡ኀያላን፡ጋራ፡ይተኛሉ።
28አንተም፡ባልተገረዙት፡መካከል፡ትሰበራለኽ፥በሰይፍም፡ከተገደሉት፡ጋራ፡ትተኛለኽ።
29ኤዶምያስና፡ነገሥታቷ፡አለቃዎቿም፡ዅሉ፡በዚያ፡አሉ፤በሰይፍ፡ከተገደሉት፡ጋራ፡በኀይላቸው፡ ተኝተዋል፤ካልተገረዙትና፡ወደ፡ጕድጓድ፡ከሚወርዱ፡ጋራ፡ይተኛሉ።
30የሰሜን፡አለቃዎች፡ዅሉ፡ሲዶናውያንም፡ዅሉ፡ከተገደሉት፡ጋራ፡ወርደው፡በዚያ፡አሉ፤በኀይላቸውም፡ ያስፈሩ፡በነበረው፡ፍርሀት፡ዐፍረዋል፥በሰይፍም፡ከተገደሉት፡ጋራ፡ሳይገረዙ፡ተኝተዋል፥ወደ፡ጕድጓድም፡ ከሚወርዱት፡ጋራ፡ዕፍረታቸውን፡ተሸክመዋል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
31በሰይፍ፡የተገደሉ፡ፈርዖንና፡ሰራዊቱ፡ዅሉ፡ያይዋቸዋል፥ፈርዖንም፡ስለ፡ብዛቱ፡ዅሉ፡ይጽናናል፥ይላል፡ ጌታ፡እግዚአብሔር።
32መፈራቱን፡በሕያዋን፡ምድር፡አድርጌያለኹ፥ፈርዖንና፡ብዛቱም፡ዅሉ፡በሰይፍ፡በተገደሉት፡ባልተገረዙት፡ መካከል፡ይተኛሉ፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።