1የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ለሕዝብኽ፡ልጆች፡ተናገር፥እንዲህም፡በላቸው፦ሰይፍን፡በምድር፡ላይ፡ባመጣኹ፡ ጊዜ፥የምድር፡ሕዝብ፡ከመካከላቸው፡ሰውን፡ወስደው፡ለራሳቸው፡ጕበኛ፡ቢያደርጉ፥
3ርሱም፡በምድር፡ላይ፡የመጣውን፡ሰይፍ፡ባየ፡ጊዜ፡መለከትን፡ቢነፋ፥ሕዝቡንም፡ቢያስጠነቅቅ፥
4የመለከቱን፡ድምፅ፡የሚሰማ፡ሰው፡ባይጠነቀቅ፥ሰይፍ፡መጥቶ፡ቢወስደው፥ደሙ፡በራሱ፡ላይ፡ይኾናል።
5የመለከቱን፡ድምፅ፡ሰምቶ፡ስላልተጠነቀቀ፡ደሙ፡በራሱ፡ላይ፡ይኾናል፤ቢጠነቀቅስ፡ኖሮ፡ነፍሱን፡ባዳነ፡ ነበር።
6ጕበኛው፡ግን፡ሰይፍ፡ሲመጣ፡ቢያይ፡መለከቱንም፡ባይነፋ፡ሕዝቡንም፡ባያስጠነቅቅ፡ሰይፍም፡መጥቶ፡ አንድ፡ሰው፡ከርሱ፡ቢወስድ፥ርሱ፡በኀጢአቱ፡ተወስዷል፥ደሙን፡ግን፡ከጕበኛው፡እጅ፡እፈልጋለኹ።
7አንተም፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ለእስራኤል፡ቤት፡ጕበኛ፡አድርጌኻለኹ፤ከአፌ፡ቃሌን፡ስማ፡ከእኔም፡ዘንድ፡ አስጠንቅቃቸው።
8ኀጢአተኛውን፦ኀጢአተኛ፡ሆይ፥በርግጥ፡ትሞታለኽ፡ባልኹ፡ጊዜ፥ኀጢአተኛውን፡ከመንገዱ፡ ታስጠነቅቅ፡ዘንድ፥ባትናገር፡ያ፡ኀጢአተኛ፡በኀጢአቱ፡ይሞታል፥ደሙን፡ግን፡ከእጅኽ፡እፈልጋለኹ።
9ነገር፡ግን፥ከመንገዱ፡ይመለስ፡ዘንድ፥ኀጢአተኛውን፡ብታስጠነቅቀው፡ርሱም፡ከመንገዱ፡ ባይመለስ፥በኀጢአቱ፡ይሞታል፡አንተ፡ግን፡ነፍስኽን፡አድነኻል።
10አንተም፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የእስራኤልን፡ቤት፦እናንተ፦በደላችንና፡ኀጢአታችን፡በላያችን፡ አሉ፥እኛም፡ሰልስለንባቸዋል፤እንዴትስ፡በሕይወት፡እንኖራለን፧ብላችኹ፡ተናግራችዃል፡በላቸው።
11እኔ፡ሕያው፡ነኝና፡ኀጢአተኛው፡ከመንገዱ፡ተመልሶ፡በሕይወት፡ይኖር፡ዘንድ፡እንጂ፥ኀጢአተኛው፡ ይሞት፡ዘንድ፡አልፈቅድም፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥ተመለሱ፥ከክፉ፡ መንገዳችኹ፡ተመለሱ፤ስለ፡ምንስ፡ትሞታላችኹ፧በላቸው።
12አንተም፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የሕዝብኽን፡ልጆች፡እንዲህ፡በላቸው፦በበደለበት፡ቀን፡የጻድቅ፡ጽድቁ፡ አያድነውም፥ኀጢአተኛም፡ከኀጢአቱ፡በተመለሰበት፡ቀን፡በኀጢአቱ፡አይሰናከልም፤ጻድቁም፡ኀጢአት፡ በሠራበት፡ቀን፡በጽድቁ፡በሕይወት፡አይኖርም።
13እኔ፡ጻድቁን፦በርግጥ፡በሕይወት፡ትኖራለኽ፡ባልኹ፡ጊዜ፥ርሱ፡በጽድቁ፡ታምኖ፡ኀጢአት፡ቢሠራ፡ በሠራው፡ኀጢአት፡ይሞታል፡እንጂ፡ጽድቁ፡አይታሰብለትም።
14እኔም፡ኀጢአተኛውን፦በርግጥ፡ትሞታለኽ፡ባልኹ፡ጊዜ፥ርሱ፡ከኀጢአቱ፡ተመልሶ፡ፍርድንና፡ቅን፡ ነገርን፡ቢያደርግ፥
15ኀጢአተኛውም፡መያዣን፡ቢመልስ፡የነጠቀውንም፡ቢመልስ፡በሕይወትም፡ትእዛዝ፡ቢኼድ፡ኀጢአትም፡ ባይሠራ፥በሕይወት፡ይኖራል፡እንጂ፡አይሞትም።
16የሠራው፡ኀጢአት፡ዅሉ፡አይታሰብበትም፤ፍርድንና፡ቅን፡ነገርን፡አድርጓል፤በርግጥ፡በሕይወት፡ይኖራል።
17ነገር፡ግን፥የሕዝብኽ፡ልጆች፦የጌታ፡መንገድ፡የቀና፡አይደለም፡ይላሉ፤ነገር፡ግን፥የእነርሱ፡መንገድ፡ የቀና፡አይደለም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
18ጻድቅ፡ከጽድቁ፡ተመልሶ፡ኀጢአትን፡ቢሠራ፡ይሞትባታል።
19ኀጢአተኛውም፡ከኀጢአቱ፡ተመልሶ፡ፍርድንና፡ቅን፡ነገርን፡ቢያደርግ፡በሕይወት፡ይኖርበታል።
20እናንተ፡ግን፦የጌታ፡መንገድ፡የቀና፡አይደለም፡ትላላችኹ።የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥በያንዳንዳችኹ፡ላይ፡ እንደ፡መንገዳችኹ፡እፈርድባችዃለኹ።
21እንዲህም፡ኾነ፤በተማረክን፡በዐሥራ፡ኹለተኛው፡ዓመት፡በዐሥረኛው፡ወር፡ከወሩም፡በዐምስተኛው፡ቀን፡ ከኢየሩሳሌም፡ያመለጠ፡አንድ፡ሰው፡ወደ፡እኔ፡መጥቶ፦ከተማዪቱ፡ተመታች፡አለኝ።
22ያመለጠውም፡ሳይመጣ፡በመሸ፡ጊዜ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡በእኔ፡ላይ፡ነበረች፥በነጋውም፡ወደ፡እኔ፡ እስኪመጣ፡ድረስ፡አፌን፡ከፈተ፤አፌም፡ተከፈተች፡ከዚያም፡በዃላ፡እኔ፡ዲዳ፡አልኾንኹም።
23የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
24የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥በእስራኤል፡ምድር፡ባሉ፡በባድማ፡ስፍራዎች፡የተቀመጡ፦አብርሃም፡ብቻውን፡ሳለ፡ ምድሪቱን፡ወረሰ፤እኛም፡ብዙዎች፡ነን፡ምድሪቱም፡ርስት፡ኾና፡ለእኛ፡ተሰጥታለች፡ይላሉ።
25ስለዚህ፥እንዲህ፡በላቸው፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ከደም፡ጋራ፡ ትበላላችኹ፥ዐይናችኹንም፡ወደ፡ጣዖቶቻችኹ፡ታነሣላችኹ፥ደምንም፡ታፈሳ፟ላችኹ፤በእውኑ፡ምድሪቱን፡ ትወርሳላችኹን፧
26ሰይፋችኹን፡ይዛችኹ፡ቆማችዃል፥ርኩስ፡ነገርን፡ታደርጋላችኹ፥የባልንጀራዎቻችኹንም፡ሚስቶች፡ ታስነውራላችኹ፤በእውኑ፡ምድሪቱን፡ትወርሳላችኹን፧
27እንዲህም፡በላቸው፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እኔ፡ሕያው፡ነኝና፡በባድማ፡ስፍራዎች፡ያሉ፡ በሰይፍ፡ይወድቃሉ፥በምድረ፡በዳ፡ያለውን፡ለአራዊት፡መብል፡አድርጌ፡እሰጣለኹ፥በዐምባዎችና፡በዋሾች፡ ያሉ፡በቸነፈር፡ይሞታሉ።
28ምድሪቱንም፡ባድማና፡ውድማ፡አደርጋታለኹ፡የኀይሏም፡ትዕቢት፡ይቀራል፥የእስራኤልም፡ተራራዎች፡ ባድማ፡ይኾናሉ፥ማንም፡አያልፍባቸውም።
29ስላደረጉትም፡ርኵሰት፡ዅሉ፡ምድሪቱን፡ባድማና፡ውድማ፡ባደርግኹ፡ጊዜ፥እኔ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ ኾንኹ፡ያውቃሉ።
30አንተም፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የሕዝብኽ፡ልጆች፡በቅጥር፡አጠገብና፡በቤት፡ደጆች፡ውስጥ፡ስለ፡አንተ፡ ይናገራሉ፥ርስ፡በርሳቸውም፥አንዱ፡ከአንዱ፡ጋራ፦እንኺድና፡እግዚአብሔር፡ያለው፡ቃል፡ምን፡እንደ፡ኾነ፡ እንስማ፡ብለው፡ይናገራሉ።
31ሕዝብ፡እንደሚመጣ፡ወዳንተ፡ይመጣሉ፥እንደ፡ሕዝቤም፡በፊትኽ፡ይቀመጣሉ፥ቃልኽንም፡ ይሰማሉ፥ነገር፡ግን፥አያደርጉትም፤በአፋቸው፡ብዙ፡ፍቅር፡ይገልጣሉ፥ልባቸው፡ግን፡ሥሥታቸውን፡ ትከተላለች።
32እንሆ፥አንተ፡መልካም፡ድምፅ፡እንዳለው፡እንደሚወደድ፡መዝሙር፡ማለፊያም፡አድርጎ፡በገና፡ እንደሚጫወት፡ሰው፡ኾነኽላቸዋል፤ቃልኽንም፡ይሰማሉ፥ነገር፡ግን፥አያደርጉትም።
33እንሆ፥ይህ፡ይመጣል፤በመጣም፡ጊዜ፡እነርሱ፡ነቢይ፡በመካከላቸው፡እንደ፡ነበረ፡ያውቃሉ።