1የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ትንቢት፡ተናገር፥በእስራኤል፡እረኛዎች፡ላይ፡ትንቢት፡ተናገር፥እረኛዎችንም፡እንዲህ፡ በላቸው፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ራሳቸውን፡ለሚያሰማሩ፡ለእስራኤል፡እረኛዎች፡ወዮላቸው! እረኛዎች፡በጎችን፡ያሰማሩ፡ዘንድ፡አይገ፟ባ፟ቸውምን፧ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
3ጮማውን፡ትበላላችኹ፡ጠጕሩንም፡ትለብሳላችኹ፥የወፈሩትን፡ታርዳላችኹ፤በጎቹን፡ግን፡አታሰማሩም።
4የደከመውን፡አላጸናችኹትም፡የታመመውንም፡አላከማችኹትም፡የተሰበረውንም፡አልጠገናችኹትም፡ የባዘነውንም፡አልመለሳችኹትም፡የጠፋውንም፡አልፈለጋችኹትም፡በኀይልና፡በጭቈናም፡ገዛችዃቸው።
5እረኛንም፡በማጣት፡ተበተኑ፥ለምድርም፡አራዊት፡ዅሉ፡መብል፡ኾኑ፥ተበተኑም።
6በጎቼ፡በተራራዎች፡ዅሉና፡በረዘሙ፡ኰረብታዎች፡ዅሉ፡ላይ፡ተቅበዝብዘዋል፥በጎቼም፡በምድር፡ፊት፡ ዅሉ፡ላይ፡ተበትነዋል፤የሚሻም፡የሚፈልግም፡አልነበረም።
7ስለዚህ፥እረኛዎች፡ሆይ፥የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፤
8ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እኔ፡ሕያው፡ነኝና፡እረኛ፡ስለሌለ፡እረኛዎቼም፡በጎቼን፡ስላልፈለጉ፡ እረኛዎችም፡ራሳቸውን፡እንጂ፡በጎቼን፡ስላላሰማሩ፥በጎቼ፡ንጥቂያ፡ኾነዋልና፥በጎቼም፡ለምድር፡አራዊት፡ ዅሉ፡መብል፡ኾነዋልና፥
9ስለዚህ፥እረኛዎች፡ሆይ፥የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፤
10ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥በእረኛዎች፡ላይ፡ነኝ፥በጎቼንም፡ከእጃቸው፡ እፈልጋለኹ፥በጎቼንም፡ከማሰማራት፡አስተዋቸዋለኹ።ከዚያም፡ወዲያ፡እረኛዎች፡ራሳቸውን፡ አያሰማሩም፤በጎቼንም፡ከአፋቸው፡አድናለኹ፥መብልም፡አይኾኑላቸውም።
11ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦እንሆ፥እኔ፡ራሴ፡በጎቼን፡እሻለኹ፡እፈልግማለኹ።
12እረኛ፡በተበተኑት፡በጎች፡መካከል፡ባለ፡ጊዜ፡መንጋውን፡እንደሚፈልግ፥እንዲሁ፡በጎቼን፡ እፈልጋለኹ፤በደመናና፡በጨለማ፡ቀን፡ከተበተኑት፡ስፍራ፡ዅሉ፡አድናቸዋለኹ።
13ከአሕዛብም፡ዘንድ፡አወጣቸዋለኹ፡ከአገሮችም፡እሰበስባቸዋለኹ፥ወደ፡ገዛ፡አገራቸውም፡ አመጣቸዋለኹ፤በእስራኤልም፡ተራራዎች፡ላይ፡በፈሳሾችም፡አጠገብ፡በምድርም፡ላይ፡ሰዎች፡በሚኖሩበት፡ ስፍራ፡ዅሉ፡አሰማራቸዋለኹ።
14በመልካም፡ማሰማሪያ፡አሰማራቸዋለኹ፥ጕረኗቸውም፡በረዥሞቹ፡በእስራኤል፡ተራራዎች፡ላይ፡ ይኾናል፤በዚያ፡በመልካም፡ጕረኖ፡ውስጥ፡ይመሰጋሉ፥በእስራኤልም፡ተራራዎች፡ላይ፡በለመለመ፡ማሰማሪያ፡ ይሰማራሉ።
15እኔ፡ራሴ፡በጎቼን፡አሰማራለኹ፡አስመስጋቸውማለኹ፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
16የጠፋውንም፡እፈልጋለኹ፡የባዘነውንም፡እመልሳለኹ፡የተሰበረውንም፡እጠግናለኹ፡የደከመውንም፡ አጸናለኹ፤የወፈረውንና፡የበረታውንም፡አጠፋለኹ፤በፍርድም፡እጠብቃቸዋለኹ።
17ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እናንተም፡መንጋዬ፡ሆይ፥እንሆ፥በበግና፡በበግ፡ መካከል፥በአውራ፡በግና፡በአውራ፡ፍየልም፡መካከል፥እፈርዳለኹ።
18የቀረውን፡ማሰማሪያችኹን፡በእግራችኹ፡የረገጣችኹት፥በመልካሙ፡ማሰማሪያ፡መሰማራታችኹ፡ ባይበቃችኹ፡ነውን፧የቀረውንስ፡ውሃ፡በእግራችኹ፡ያደፈረሳችኹት፥ጥሩውን፡ውሃ፡መጠጣታችኹ፡ ባይበቃችኹ፡ነውን፧
19በጎቼም፡በእግራችኹ፡በረገጣችኹት፡ይሰማራሉ፡በእግራችኹም፡ያደፈረሳችኹትን፡ይጠጣሉ።
20ስለዚህ፥ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላቸዋል፦እንሆ፥እኔ፡በወፈሩት፡በጎችና፡በከሱት፡በጎች፡ መካከል፡እፈርዳለኹ።
21እስክትበትኗቸው፡ድረስ፡በእንቢያና፡በትከሻ፡ስለምትገፏቸው፡የደከሙትንም፡ዅሉ፡በቀንዳችኹ፡ ስለምትወጓቸው፥
22ስለዚህ፥መንጋዬን፡አድናለኹ፥ከእንግዲህ፡ወዲህም፡ንጥቂያ፡አይኾኑም፤በበግና፡በበግ፡መካከልም፡ እፈርዳለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
23በላያቸውም፡አንድ፡እረኛ፡አቆማለኹ፡ርሱም፡ያሰማራቸዋል፥ርሱም፡ባሪያዬ፡ዳዊት፡ነው፤ያሰማራቸዋል፡ እረኛም፡ይኾናቸዋል።
24እኔም፡እግዚአብሔር፡አምላክ፡እኾናቸዋለኹ፡ባሪያዬም፡ዳዊት፡በመካከላቸው፡አለቃ፡ይኾናል፤እኔ፡ እግዚአብሔር፡ተናግሬያለኹ።
25የሰላምን፡ቃል፡ኪዳን፡ከነርሱ፡ጋራ፡እገባለኹ፡ክፉዎችንም፡አራዊት፡ከምድር፡አጠፋለኹ፤ተዘልለውም፡ በምድረ፡በዳ፡ይኖራሉ፡በዱርም፡ውስጥ፡ይተኛሉ።
26እነርሱንና፡በኰረብታዬ፡ዙሪያ፡ያሉትን፡ስፍራዎች፡ለበረከት፡አደርጋቸዋለኹ፥ዝናቡንም፡በጊዜው፡ አወርዳለኹ፤የበረከት፡ዝናብ፡ይኾናል።
27የምድረ፡በዳም፡ዛፍ፡ፍሬውን፡ይሰጣል፡ምድርም፡ቡቃያዋን፡ትሰጣለች፥በምድራቸውም፡ተዘልለው፡ ይኖራሉ፡የቀንበራቸውንም፡ማነቆ፡በሰበርኹ፡ጊዜ፡ከሚገዟቸውም፡እጅ፡ባዳንዃቸው፡ጊዜ፥እኔ፡እግዚአብሔር፡ እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ።
28እንግዲህም፡ለአሕዛብ፡ንጥቂያ፡አይኾኑም፡የምድርም፡አራዊት፡አይበሏቸውም፤ተዘልለውም፡ይቀመጣሉ፡ የሚያስፈራቸውም፡የለም።
29የዝናን፡ተክል፡አቆምላቸዋለኹ፡እንግዲህም፡ከራብ፡የተነሣ፡በምድር፡አያልቁም፤የአሕዛብንም፡ስድብ፡ ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አይሸከሙም።
30እኔ፡እግዚአብሔር፡አምላካቸው፡ከነርሱ፡ጋራ፡እንዳለኹ፥እነርሱም፡የእስራኤል፡ቤት፡ሕዝቤ፡እንደ፡ ኾኑ፡ያውቃሉ፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
31እናንተም፡በጎቼ፥የማሰማሪያዬ፡በጎች፥ሰዎች፡ናችኹ፡እኔም፡አምላካችኹ፡ነኝ፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።