1አንተም፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ለእስራኤል፡ተራራዎች፡ትንቢት፡ተናግረኽ፦የእስራኤል፡ተራራዎች፡ ሆይ፥የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፡በል።
2ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ጠላት፡በእናንተ፡ላይ፦ዕሠይ፥የጥንት፡ከፍታዎች፡ለእኛ፡ርስት፡ ኾነዋል፡ብሏልና፥
3ስለዚህ፥ትንቢት፡ተናገር፡እንዲህም፡በል፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ለቀሩት፡አሕዛብ፡ርስት፡ ትኾኑ፡ዘንድ፥በዙሪያችኹ፡ያሉ፡ባድማ፡አድርገዋችዃልና፥ውጠዋችኹማልና፥እናንተም፡የተናጋሪዎች፡ከንፈር፡ መተረቻና፡የአሕዛብ፡ማላገጫ፡ኾናችዃልና፥
4ስለዚህ፥እናንተ፡የእስራኤል፡ተራራዎች፡ሆይ፥የጌታን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ ለተራራዎችና፡ለኰረብታዎች፥ለፈሳሾችና፡ለሸለቆዎች፡ለምድረ፡በዳዎች፡ባዶ፡ለኾኑትም፡በዙሪያ፡ላሉት፡ ለቀሩት፡አሕዛብ፡ምርኮና፡መሳቂያ፡ለኾኑት፡ከተማዎች፡እንዲህ፡ይላል፤
5ስለዚህ፥ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ያሳድዷትና፡ይበዘብዟት፡ዘንድ፥በልባቸው፡ዅሉ፡ደስታና፡ በነፍሳቸው፡ንቀት፡ምድሬን፡ርስት፡አድርገው፡ለራሳቸው፡በሰጡ፡በቀሩት፡አሕዛብና፡በኤዶምያስ፡ዅሉ፡ላይ፡ በቅንአቴ፡እሳት፡ተናግሬያለኹ፤
6ስለዚህ፥ስለእስራኤል፡ምድር፡ትንቢት፡ተናገር፥ለተራራዎችና፡ለኰረብታዎችም፡ለፈሳሾችና፡ለሸለቆዎችም፡ እንዲህ፡በል፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥የአሕዛብን፡ስድብ፡ስለ፡ተሸከማችኹ፡በቅንአቴና፡ በመዓቴ፡ተናግሬያለኹ፤
7ስለዚህ፥ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዙሪያችኹ፡ያሉ፡አሕዛብ፡ስድባቸውን፡በርግጥ፡ይሸከማሉ፡ ብዬ፡ምያለኹ።
8የእስራኤል፡ተራራዎች፡ሆይ፥እናንተ፡ግን፡ቅርንጫፎቻችኹን፡ታቈጠቍጣላችኹ፥ይመጡም፡ዘንድ፡ ቀርበዋልና፥ለሕዝቤ፡ለእስራኤል፡ፍሬያችኹን፡ትሰጣላችኹ።
9እንሆ፥እኔ፡ለእናንተ፡ነኝና፤ወደ፡እናንተም፡እመለከታለኹ፥እናንተም፡ትታረሳላችኹ፡ይዘራባችኹማል፤
10እኔም፡የእስራኤልን፡ቤት፡ሰዎች፡ዅሉ፡ዅሉንም፡አበዛባችዃለኹ፥በከተማዎችም፡ሰዎች፡ይኖሩባቸዋል፡ ባድማዎቹም፡ስፍራዎች፡ይሠራሉ፤
11ሰውንና፡እንስሳውንም፡አበዛባችዃለኹ፥እነርሱም፡ይበዛሉ፡ያፈሩማል፤እንደ፡ጥንታችኹም፡ሰዎችን፡ አኖርባችዃለኹ፥ቀድሞም፡ካደረግኹላችኹ፡ይልቅ፡መልካም፡አደርግላችዃለኹ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ ኾንኹ፡ታውቃላችኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
12ሰዎችንም፥ሕዝቤን፡እስራኤልን፥በእናንተ፡ላይ፡አስኼዳቸዋለኹ፤እነርሱም፡ይወርሱሻል፡ርስትም፡ ትኾኛቸዋለሽ፥ከእንግዲህም፡ወዲያ፡ልጅ፡አልባ፡አታደርጊያቸውም።
13ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እነርሱ፦ሰው፡በሊታ፡ምድር፡ነሽ፡ሕዝብሽንም፡ልጅ፡አልባ፡ የምታደርጊ፡ነሽ፡ብለዋችዃልና፥
14ስለዚህ፥ዳግመኛ፡ሰው፡በሊታ፡አትኾኚም፥ዳግመኛም፡ሕዝብሽን፡ልጅ፡አልባ፡አታደርጊም፥ይላል፡ ጌታ፡እግዚአብሔር፤
15ዳግመኛም፡የአሕዛብን፡ውርደት፡አላሰማብሽም፥ዳግመኛም፡የአሕዛብን፡ስድብ፡አትሸከሚም፥ዳግመኛም፡ ሕዝብሽን፡አታሰናክዪም፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
16የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
17የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የእስራኤል፡ቤት፡በምድራቸው፡በተቀመጡ፡ጊዜ፡በመንገዳቸውና፡በሥራቸው፡ አረከሷት፥መንገዳቸውም፡በፊቴ፡እንደ፡መርገም፡አደፍ፡ነበረ።
18በምድር፡ላይ፡ስላፈሰሱት፡ደም፡በጣዖቶቻቸውም፡ስላረከሷት፡መዓቴን፡አፈሰስኹባቸው፤
19ወደ፡አሕዛብም፡በተንዃቸው፡ወደ፡አገሮችም፡ተዘሩ፤እንደ፡መንገዳቸውና፡እንደ፡ሥራቸው፡መጠን፡ ፈረድኹባቸው።
20ወደመጡባቸውም፡ወደ፡አሕዛብ፡በመጡ፡ጊዜ፥ሰዎች፡እነርሱን፦ከምድሩ፡የወጡ፡የእግዚአብሔር፡ ሕዝብ፡እነዚህ፡ናቸው፡ሲሏቸው፡ቅዱስ፡ስሜን፡አረከሱ።
21እኔ፡ግን፡የእስራኤል፡ቤት፡በመጡባቸው፡በአሕዛብ፡መካከል፡ስላረከሱት፡ስለ፡ቅዱስ፡ስሜ፡ስል፡ ራራኹላቸው።
22ስለዚህ፥ለእስራኤል፡ቤት፡እንዲህ፡በል፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የእስራኤል፡ቤት፡ ሆይ፥በመጣችኹባቸው፡በአሕዛብ፡መካከል፡ስላረከሳችኹት፡ስለ፡ቅዱስ፡ስሜ፡ነው፡እንጂ፡ስለ፡እናንተ፡ የምሠራ፡አይደለኹም።
23በአሕዛብም፡ዘንድ፡የረከሰውን፥በመካከላቸው፡ያረከሳችኹትን፡ስሜን፡እቀድሰዋለኹ፤በዐይናቸውም፡ ዘንድ፡በተቀደስኹባችኹ፡ጊዜ፡እኔ፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡አሕዛብ፡ያውቃሉ፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።
24ከአሕዛብም፡መካከል፡አወጣችዃለኹ፡ከየአገሩም፡ዅሉ፡እሰበስባችዃለኹ፡ወደገዛ፡ምድራችኹም፡ አመጣችዃለኹ።
25ጥሩ፡ውሃንም፡እረጭባችዃለኹ፡እናንተም፡ትጠራላችኹ፥ከርኵሰታችኹም፡ዅሉ፡ከጣዖቶቻችኹም፡ዅሉ፡ አጠራችዃለኹ።
26ዐዲስም፡ልብ፡እሰጣችዃለኹ፡ዐዲስም፡መንፈስ፡በውስጣችኹ፡አኖራለኹ፤የድንጋዩንም፡ልብ፡ ከሥጋችኹ፡አወጣለኹ፤የሥጋንም፡ልብ፡እሰጣችዃለኹ።
27መንፈሴንም፡በውስጣችኹ፡አኖራለኹ፥በትእዛዜም፡አስኼዳችዃለኹ፥ፍርዴንም፡ ትጠብቃላችኹ፥ታደርጉትማላችኹ።
28ለአባቶቻችኹም፡በሰጠዃት፡ምድር፡ትኖራላችኹ፤ሕዝብም፡ትኾኑኛላችኹ፡እኔም፡አምላክ፡ እኾናችዃለኹ።
29ከርኵሰታችኹም፡ዅሉ፡አድናችዃለኹ፤እኽልንም፡እጠራዋለኹ፡አበዛውማለኹ፡ራብንም፡ አላመጣባችኹም።
30ደግሞም፡የራብን፡ስድብ፡ከአሕዛብ፡ዘንድ፡እንዳትሸከሙ፡የዛፍን፡ፍሬና፡የዕርሻውን፡ቡቃያ፡አበዛለኹ።
31ክፉውን፡መንገዳችኹንና፡መልካም፡ያይደለውን፡ሥራችኹንም፡ታስባላችኹ፥ስለ፡በደላችኹና፡ስለ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ርኵሰታችኹም፡ራሳችኹን፡ትጸየፋላችኹ።
32ይህን፡የሠራኹ፡ስለ፡እናንተ፡እንዳይደለ፡በእናንተ፡ዘንድ፡የታወቀ፡ይኹን፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር፤የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥ስለ፡መንገዳችኹ፡ዕፈሩና፡ተዋረዱ።
33ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ከኀጢአታችኹ፡ዅሉ፡ባነጻዃችኹበት፡ቀን፡በከተማዎች፡ሰዎችን፡ አኖራለኹ፥ባድማዎቹም፡ስፍራዎች፡ይሠ፟ራ፟ሉ።
34ባድማ፡የነበረች፡በመንገደኛም፡ዅሉ፡ዐይን፡ዘንድ፡ባድማ፡የነበረች፡ምድር፡ትታረሳለች።
35ሰዎችም፦ባድማ፡የነበረች፡ይህች፡ምድር፡እንደ፡ዔዴን፡ገነት፡ኾናለች፤የፈረሱት፣ባድማ፡ የኾኑት፣የጠፉትም፡ከተማዎች፡ተመሽገዋል፥ሰውም፡የሚኖርባቸው፡ኾነዋል፡ይላሉ።
36በዙሪያችኹም፡የቀሩት፡አሕዛብ፡እኔ፡እግዚአብሔር፡የፈረሱትን፡ስፍራዎች፡እንደ፡ሠራኹ፡ውድማ፡ የኾነውንም፡እንደ፡ተከልኹ፡ያውቃሉ፤እኔ፡እግዚአብሔር፡ተናግሬያለኹ፥እኔም፡አደርገዋለኹ።
37ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ስለዚህ፡ደግሞ፡ኣደርግላቸው፡ዘንድ፥የእስራኤል፡ቤት፡ ይሹኛል፤ሰውንም፡እንደ፡መንጋ፡አበዛላቸዋለኹ።
38እንደ፡ተቀደሱ፡በጎች፥በበዓላቷ፡ቀን፡እንደሚኾኑ፡እንደ፡ኢየሩሳሌም፡በጎች፥እንዲሁ፡የፈለሱት፡ ከተማዎች፡በሰዎች፡መንጋ፡ይሞላሉ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ።