Skip to content
← Ezekiel

Chapter 38 · Amharic

Ezekiel

1የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦

2የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ፊትኽን፡በጎግ፡ላይና፡በማጎግ፡ምድር፡ላይ፥በሞሳሕና፡በቶቤል፡ዋነኛ፡አለቃ፡ላይ፡ አቅናበት፥ትንቢትም፡ተናገርበት፥

3እንዲህም፡በል፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የሞሳሕና፡የቶቤል፡ዋነኛ፡አለቃ፡ጎግ፡ ሆይ፥እንሆ፥እኔ፡ባንተ፡ላይ፡ነኝ።

4እመልስኽማለኹ፥በመንጋጋኽም፡ልጓም፡አገባብኻለኹ፥አንተንና፡ሰራዊትኽንም፡ዅሉ፥ፈረሶችንና፡ ፈረሰኛዎችን፥የጦር፡ልብስ፡የለበሱትን፡ዅሉ፥ጋሻና፡ራስ፡ቍርን፡ሰይፍንም፡የያዙትን፡ዅሉ፥ታላቁን፡ወገን፡ አወጣለኹ፤

5ፋርስንና፡ኢትዮጵያን፡ፉጥንም፡ከነርሱ፡ጋራ፡ጋሻና፡የራስ፡ቍርን፡የለበሱትን፡ዅሉ፥

6ጋሜርንና፡ጭፍራዎቹን፡ዅሉ፥በሰሜን፡ዳርቻም፡ያለውን፡የቴርጋማን፡ቤትና፡ጭፍራዎቹን፡ ዅሉ፥ብዙዎችንም፡ሕዝቦች፡ከአንተ፡ጋራ፡አወጣለኹ።

7አንተና፡ወዳንተ፡የተሰበሰቡ፡ወገኖችኽ፡ዅሉ፡ተዘጋጁ፥አንተም፡ራስኽን፡አዘጋጅተኽ፡አለቃ፡ኹናቸው።

8ከብዙ፡ዘመንም፡በዃላ፡ትፈለጋለኽ፤በዃለኛውም፡ዘመን፥የዘለዓለም፡ባድማ፡በነበሩ፡በእስራኤል፡ ተራራዎች፡ላይ፡ከብዙ፡ሕዝብ፡ውስጥ፡ወደተሰበሰበች፥ከሰይፍ፡ወደተመለሰች፡ምድር፡ትገባለኽ፤ርሷም፡ ከሕዝብ፡ውስጥ፡ወጥታለች፡ዅሉም፡ሳይፈሩ፡ይቀመጡባታል።

9አንተም፡ትወጣለኽ፥እንደ፡ዐወሎ፡ነፋስም፡ትመጣለኽ፤አንተና፡ጭፍራዎችኽ፡ዅሉ፡ከአንተም፡ጋራ፡ ብዙ፡ሕዝብ፡ምድርን፡እንደ፡ደመና፡ትሸፍናላችኹ።

10ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዚያ፡ቀን፡ነገር፡ወደ፡ልብኽ፡ይገባል፥

11ክፉ፡ዐሳብንም፡ታስባለኽ፥እንዲህም፡ትላለኽ፦ቅጥርን፡ወደሌላቸው፡መንደሮች፡እወጣለኹ፤ተዘልለው፡ ወደሚኖሩ፥ዅላቸው፡ሳይፈሩ፡ያለቅጥርና፡ያለመወርወሪያ፡ያለመዝጊያም፡ወደሚቀመጡ፡እገባለኹ፤

12ምርኮን፡ትማርክ፡ዘንድ፥ብዝበዛንም፡ትበዘብዝ፡ዘንድ፥ባድማም፡በነበሩ፡አኹንም፡ሰዎች፡በሚኖሩባቸው፡ ስፍራዎች፡ላይ፥ከአሕዛብም፡በተሰበሰበ፥ከብትና፡ዕቃንም፡ባገኘ፥በምድርም፡መካከል፡በተቀመጠ፡ሕዝብ፡ ላይ፡እጅኽን፡ትዘረጋ፡ዘንድ።

13ሳባና፡ድዳን፡የተርሴስም፡ነጋዴዎች፡መንደሮቿም፡ዅሉ፦ምርኮን፡ትማርክ፡ ዘንድ፥መጥተኻልን፧ብዝበዛንስ፡ትበዘብዝ፡ዘንድ፥ብርንና፡ወርቅንስ፡ትወስድ፡ዘንድ፥ከብትንና፡ዕቃንስ፡ ትወስድ፡ዘንድ፥እጅግስ፡ብዙ፡ምርኮ፡ትማርክ፡ዘንድ፥ወገንኽን፡ሰብስበኻልን፧ይሉኻል።

14አንተ፥የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ስለዚህ፡ትንቢት፡ተናገር፡ጎግንም፡እንዲህ፡በለው፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ እንዲህ፡ይላል፦በዚያ፡ቀን፡ሕዝቤ፡እስራኤል፡ሳይፈራ፡በተቀመጠ፡ጊዜ፡አንተ፡አታውቀውምን፧

15አንተም፥ከአንተም፡ጋራ፡ብዙ፡ሕዝብ፡ዅላቸው፡በፈረሶች፡ላይ፡የተቀመጡ፥ታላቅ፡ወገንና፡ብርቱ፡ ሰራዊት፥ከሰሜን፡ዳርቻ፡ከስፍራችኹ፡ትመጣላችኹ።

16ምድርንም፡ትሸፍን፡ዘንድ፥እንደ፡ደመና፡በሕዝቤ፡በእስራኤል፡ላይ፡ትወጣለኽ።በዃለኛው፡ዘመን፡ ይኾናል፥ጎግ፡ሆይ፥በዐይናቸው፡ፊት፡በተቀደስኩብኽ፡ጊዜ፡አሕዛብ፡ያውቁኝ፡ዘንድ፥በምድሬ፡ላይ፡ አመጣኻለኹ።

17ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእነርሱ፡ላይ፡እንደማመጣኽ፡በዚያች፡ዘመን፡ብዙ፡ዓመት፡ ትንቢት፡በተናገሩ፡በባሪያዎቼ፡በእስራኤል፡ነቢያት፡በቀደመው፡ዘመን፡ስለ፡ርሱ፡የተናገርኹ፡አንተ፡ነኽን፧

18በዚያም፡ቀን፡ጎግ፡በእስራኤል፡ምድር፡ላይ፡በመጣ፡ጊዜ፡መቅሠፍቴ፡በመዓቴ፡ይመጣል፥ይላል፡ጌታ፡ እግዚአብሔር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

19በቅንአቴና፡በመዓቴ፡እሳት፡ተናግሬያለኹ።በርግጥ፡በዚያ፡ቀን፡በእስራኤል፡ምድር፡ጽኑ፡መናወጥ፡ ይኾናል፤

20ከፊቴም፡የተነሣ፡የባሕር፡ዓሣዎችና፡የሰማይ፡ወፎች፡የምድረ፡በዳም፡አራዊት፡በምድርም፡ላይ፡ የሚንቀሳቀሱ፡ተንቀሳቃሾች፡ዅሉ፥በምድርም፡ላይ፡የሚኖሩ፡ሰዎች፡ዅሉ፡ይንቀጠቀጣሉ፥ተራራዎችም፡ ይገለባበጣሉ፥ገደላገደሎችም፡ይወድቃሉ፥ቅጥርም፡ዅሉ፡ወደ፡ምድር፡ይወድቃል።

21በተራራዎቼም፡ዅሉ፡በርሱ፡ላይ፡ሰይፍን፡እጠራለኹ፥የሰውም፡ዅሉ፡ሰይፍ፡በወንድሙ፡ላይ፡ ይኾናል፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።

22በቸነፈርና፡በደም፡እፈርድበታለኹ፤ዶፍም፡የበረዶም፡ድንጋይ፡እሳትና፡ድኝም፡በርሱና፡በጭፍራዎቹ፡ ከርሱም፡ጋራ፡ባሉ፡በብዙ፡ሕዝብ፡ላይ፡አዘንባለኹ።

23ታላቅ፡እኾናለኹ፡እቀደስማለኹ፡በብዙ፡አሕዛብም፡ዐይን፡የታወቅኹ፡እኾናለኹ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡ እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source