1ርስትም፡አድርጋችኹ፡ምድርን፡በዕጣ፡በምታካፍሉበት፡ጊዜ፡ከምድር፡የተቀደሰውን፡የዕጣ፡ክፍል፡መባ፡ አድርጋችኹ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ታቀርባላችኹ።ርዝመቱ፡ኻያ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ክንድ፡ወርዱም፡ኻያ፡ሺሕ፡ ክንድ፡ይኾናል፤በዳርቻው፡ዅሉ፡ዙሪያውን፡የተቀደሰ፡ይኾናል።
2ከርሱም፡ርዝመቱ፡ዐምስት፡መቶ፡ወርዱም፡ዐምስት፡መቶ፡ክንድ፡አራት፡ማእዘን፡የኾነ፡ቦታ፡ ለመቅደሱ፡ይኾናል፤በዙሪያውም፡ባዶ፡ስፍራ፡የሚኾን፡ዐምሳ፡ክንድ፡ይኾናል።
3ከዚያው፡ልክ፡ደግሞ፡ርዝመቱ፡ኻያ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ክንድ፡ወርዱም፡ዐሥር፡ሺሕ፡ክንድ፡የኾነ፡ስፍራ፡ ትለካለኽ፤በርሱም፡ውስጥ፡ቅድስተ፡ቅዱሳን፡የኾነ፡መቅደስ፡ይኾናል።
4ከምድርም፡የተቀደሰ፡የዕጣ፡ክፍል፡ይኾናል፤እግዚአብሔርን፡ያገለግሉ፡ዘንድ፥ለሚቀርቡ፡ለመቅደሱ፡ አገልጋዮች፡ለካህናቱ፡ይኾናል፥ለቤቶቻቸውም፡የሚኾን፡ስፍራ፡ለመቅደስም፡የሚኾን፡የተቀደሰ፡ስፍራ፡ ይኾናል።
5ርዝመቱም፡ኻያ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ወርዱም፡ዐሥር፡ሺሕ፡የኾነ፡ስፍራ፡ለቤቱ፡አገልጋዮች፡ለሌዋውያን፡ ይኾናል፥ለሚቀመጡባቸውም፡ከተማዎች፡ለራሳቸውም፡የርስት፡ይዞታ፡ይኾናል።
6ለከተማዪቱም፡ይዞታ፡በተቀደሰው፡የዕጣ፡ክፍል፡መባ፡አጠገብ፡ወርዱ፡ዐምስት፡ሺሕ፡ርዝመቱም፡ኻያ፡ ዐምስት፡ሺሕ፡የኾነውን፡ስፍራ፡ታደርጋላችኹ።ርሱም፡ለእስራኤል፡ቤት፡ዅሉ፡ይኾናል።
7ለአለቃውም፡የኾነ፡የዕጣ፡ክፍል፡በተቀደሰው፡መባና፡በከተማዪቱ፡ይዞታ፡አጠገብ፡በዚህና፡በዚያ፡ ይኾናል፤በተቀደሰው፡መባና፡በከተማዪቱ፡ይዞታ፡ፊት፡በምዕራብ፡በኩል፡ወደ፡ምዕራብ፡በምሥራቅም፡በኩል፡ ወደ፡ምሥራቅ፡ይኾናል፤ርዝመቱም፡እንደ፡አንድ፡ነገድ፡ዕጣ፡ክፍል፡ኾኖ፡ከምድሩ፡ከምዕራቡ፡ዳርቻ፡ ዠምሮ፡እስከምሥራቁ፡ዳርቻ፡ድረስ፡ይኾናል።
8ይህም፡በእስራኤል፡ዘንድ፡ይዞታ፡ይኾንለታል፥አለቃዎቼም፡ለእስራኤል፡ቤት፡ምድሪቱን፡እንደ፡ነገዳቸው፡ መጠን፡ይሰጧቸዋል፡እንጂ፡ሕዝቤን፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አያስጨንቋቸውም።
9ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የእስራኤል፡አለቃዎች፡ሆይ፥ይብቃችኹ፤ግፍንና፡ብዝበዛን፡ አስወግዱ፥ፍርድንና፡ጽድቅንም፡አድርጉ፤ቅሚያችኹን፡ከሕዝቤ፡ላይ፡አርቁ፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
10እውነተኛ፡ሚዛን፡እውነተኛም፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡እውነተኛውም፡የባዶስ፡መስፈሪያ፡ይኹንላችኹ።
11የኢፍና፡የባዶስ፡መስፈሪያ፡አንድ፡ይኹን፤የባዶስ፡መስፈሪያ፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡ዐሥረኛ፡ክፍል፥የኢፍ፡ መስፈሪያውም፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡ዐሥረኛ፡ክፍል፡ይኹን።መስፈሪያው፡እንደ፡ቆሮስ፡መስፈሪያ፡ይኹን።
12ሰቅሉም፡ኻያ፡አቦሊ፡ይኹን፤ኻያ፡ሰቅል፥ኻያ፡ዐምስት፡ሰቅል፥ዐሥራ፡ዐምስት፡ሰቅል፥ምናን፡ ይኹንላችኹ።
13የምታቀርቡት፡መባ፡ይህ፡ነው፤ካንድ፡ቆሮስ፡መስፈሪያ፡ስንዴ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ስድስተኛ፡ ክፍል፥ከአንድም፡ቆሮስ፡መስፈሪያ፡ገብስ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ስድስተኛ፡ክፍል፡ትሰጣላችኹ።
14የዘይቱም፡ደንብ፥ከያንዳንዱ፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡የባዶስን፡ዐሥረኛ፡ክፍል፡ትሰጣላችኹ፤ዐሥር፡የባዶስ፡ መስፈሪያ፡አንድ፡የቆሮስ፡መስፈሪያ፡ነውና።
15ውሃም፡ካለበት፡ከእስራኤል፡ማሰማሪያ፡ከመንጋው፡ከኹለቱ፡መቶ፡አንዱን፡የበግ፡ጠቦት፡ ትሰጣላችኹ፤ይህ፡ያስተሰርይላችኹ፡ዘንድ፥ለእኽል፡ቍርባንና፡ለሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ለደኅንነትም፡ መሥዋዕት፡ይኾናል፥ይላል፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
16የአገሩም፡ሕዝብ፡ዅሉ፡ይህን፡መባ፡ለእስራኤል፡አለቃ፡ይሰጣሉ።
17በየበዓላቱም፡በየመባቻውም፡በየሰንበታቱም፡በእስራኤልም፡ቤት፡ዓመት፡በዓል፡ዅሉ፡የሚቃጠለውን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org መሥዋዕትና፡የእኽሉን፡ቍርባን፡የመጠጡንም፡ቍርባን፡መስጠት፡በአለቃው፡ላይ፡ይኾናል፤ርሱ፡ለእስራኤል፡ ቤት፡ያስተሰርይ፡ዘንድ፥የኀጢአቱን፡መሥዋዕትና፡የእኽሉን፡ቍርባን፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የደኅንነቱን፡ መሥዋዕት፡ያቀርባል።
18ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በመዠመሪያው፡ወር፡ከወሩም፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ነውር፡ የሌለበትን፡ወይፈን፡ውሰድ፡መቅደሱንም፡አንጻ።
19ካህኑም፡ከኀጢአቱ፡መሥዋዕት፡ደም፡ወስዶ፡በመቅደሱ፡መቃኖችና፡በመሠዊያው፡ዕርከን፡በአራቱ፡ ማእዘን፡በውስጠኛውም፡አደባባይ፡በበሩ፡መቃኖች፡ላይ፡ይርጨው።
20ከወሩም፡በሰባተኛው፡ቀን፡እንዲሁ፡አድርግ፥ይኸውም፡ስለሳተውና፡ስላላወቀው፡ዅሉ፡ነው።እንዲሁም፡ ስለ፡ቤቱ፡አስተስርዩ።
21በመዠመሪያ፡ወር፡ከወሩም፡በዐሥራ፡አራተኛው፡ቀን፡የፋሲካን፡በዓል፡ታደርጋላችኹ።እስከ፡ሰባት፡ ቀንም፡ድረስ፡ቂጣ፡እንጀራ፡ትበላላችኹ።
22በዚያም፡ቀን፡አለቃው፡ለራሱና፡ለአገሩ፡ሕዝብ፡ዅሉ፡የኀጢአት፡መሥዋዕት፡የሚኾነውን፡ወይፈን፡ ያቅርብ።
23በበዓሉም፡በሰባቱ፡ቀኖች፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ለእግዚአብሔር፡ያቅርብ፤ሰባቱን፡ቀኖች፡በየዕለቱ፡ ነውር፡የሌለባቸውን፡ሰባት፡ወይፈንና፡ሰባት፡አውራ፡በጎች፡ያቅርብ፤ለኀጢአትም፡መሥዋዕት፡በየዕለቱ፡አንድ፡ አውራ፡ፍየል፡ያቅርብ።
24ለአንድም፡ወይፈን፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ለአንድም፡አውራ፡በግ፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ ለአንድም፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡አንድ፡የኢን፡መስፈሪያ፡ዘይት፡ለእኽል፡ቍርባን፡ያቅርብ።
25በሰባተኛውም፡ወር፡ከወሩም፡በዐሥራ፡ዐምስተኛው፡ቀን፡በበዓሉ፡ሰባት፡ቀኖች፥የኀጢአቱን፡መሥዋዕት፡ የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕት፡የእኽሉንም፡ቍርባን፡ከዘይቱ፡ጋራ፡እንዲሁ፡ያቅርብ።