Skip to content
← Ezekiel

Chapter 46 · Amharic

Ezekiel

1ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በውስጠኛው፡አደባባይ፡ወደ፡ምሥራቅ፡የሚመለከተው፡በር፡ሥራ፡ በሚሠራበት፡በስድስቱ፡ቀን፡ተዘግቶ፡ይቈይ፤ነገር፡ግን፥በሰንበት፡ቀንና፡በመባቻ፡ቀን፡ይከፈት።

2አለቃውም፡በስተውጭ፡ባለው፡በር፡በደጀ፡ሰላሙ፡መንገድ፡ገብቶ፡በበሩ፡መቃን፡አጠገብ፡ ይቁም፥ካህናቱም፡የርሱን፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕት፡ያቅርቡ፥ርሱም፡በበሩ፡ መድረክ፡ላይ፡ይስገድ፤ከዚያም፡በዃላ፡ይውጣ፥በሩ፡ግን፡እስከ፡ማታ፡ድረስ፡አይዘጋ።

3የአገሩም፡ሕዝብ፡በዚያ፡በር፡መግቢያ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡በሰንበታትና፡በመባቻ፡ይስገዱ።

4አለቃውም፡በሰንበት፡ቀን፡ለእግዚአብሔር፡የሚያቀርበው፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ነውር፡የሌለባቸው፡ ስድስት፡የበግ፡ጠቦቶች፡ነውርም፡የሌለበት፡አንድ፡አውራ፡በግ፡ይኹን፤

5የእኽሉም፡ቍርባን፡ለአውራ፡በጉ፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ይኹን፥ለጠቦቶቹም፡የእኽል፡ቍርባን፡ እንደሚቻል፡ያኽል፡ይኹን፥ለአንዱም፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡አንድ፡የኢን፡መስፈሪያ፡ዘይት፡ያቅርብ።

6በመባቻም፡ቀን፡ነውር፡የሌለበትን፡አንድ፡ወይፈን፥ነውር፡የሌለባቸውንም፡ስድስት፡ጠቦቶችና፡አንድ፡ አውራ፡በግ፡ያቅርብ፤

7ለወይፈኑም፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ለአውራውም፡በግ፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ለጠቦቶቹም፡እንደ፡ ተቻለው፡ያኽል፥ለአንዱም፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡አንድ፡የኢን፡መስፈሪያ፡ዘይት፡ለእኽሉ፡ቍርባን፡ያቅርብ።

8አለቃውም፡በሚገባበት፡ጊዜ፡በበሩ፡ደጀ፡ሰላም፡መንገድ፡ይግባ፡በዚያውም፡ይውጣ።

9የአገሩ፡ሕዝብ፡ግን፡በየክብረ፡በዓሉ፡ቀን፡ወደእግዚአብሔር፡ፊት፡በመጡ፡ጊዜ፡በሰሜን፡በር፡በኩል፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ሊሰግድ፡የሚገባው፡በደቡብ፡በር፡በኩል፡ይውጣ፥በደቡብም፡በር፡የሚገባው፡በሰሜን፡በር፡በኩል፡ ይውጣ፤በፊት፡ለፊት፡ይውጣ፡እንጂ፡በገባበቱ፡በር፡አይመለስ።

10በሚገቡበት፡ጊዜ፡አለቃው፡በመካከላቸው፡ይግባ፡በሚወጡበትም፡ጊዜ፡ይውጣ።

11በበዓላትና፡በክብረ፡በዓል፡ቀኖች፡የእኽሉ፡ቍርባን፡ለወይፈኑ፡አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፥ለአውራ፡በጉ፡ አንድ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፥ለጠቦቶቹም፡እንደሚቻለው፡ያኽል፥ለኢፍ፡መስፈሪያም፡አንድ፡የኢን፡መስፈሪያ፡ ዘይት፡ይኾናል።

12አለቃውም፡በፈቃዱ፡የሚያቀርበውን፡መሥዋዕት፥የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፥ወይም፡በፈቃዱ፡ ለእግዚአብሔር፡የሚያቀርበውን፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕት፥ባቀረበ፡ጊዜ፥ወደ፡ምሥራቅ፡የሚመለከተው፡በር፡ ይከፈትለት፥በሰንበትም፡ቀን፡እንደሚያደርግ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የደኅንነቱን፡መሥዋዕት፡ ያቅርብ፤ከዚያም፡በዃላ፡ይውጣ፥ከወጣም፡በዃላ፡በሩ፡ይዘጋ።

13በየዕለቱም፡ለሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ነውር፡የሌለበትን፡የአንድ፡ዓመት፡በግ፡ጠቦት፡ለእግዚአብሔር፡ ያቅርብ፤በየማለዳው፡ያቅርበው።

14ከርሱም፡ጋራ፡የእኽልን፡ቍርባን፥በኢን፡መስፈሪያ፡ሢሶ፡ዘይት፡የተለወሰ፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ስድስተኛ፡ እጅ፡መልካም፡ዱቄትን፥በየማለዳው፡ያቅርብ፤ይህ፡በዘለዓለሙ፡ሥርዐት፡ለእግዚአብሔር፡የዘወትር፡የእኽል፡ ቍርባን፡ይኹን።

15እንዲሁ፡ዘወትር፡ለሚቃጠለው፡መሥዋዕት፡ጠቦቱንና፡የእኽሉን፡ቍርባን፡ዘይቱንም፡በየማለዳው፡ያቅርብ።

16ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦አለቃው፡ከልጆቹ፡ለአንዱ፡ከርስቱ፡ስጦታ፡ቢሰጥ፡ለልጆቹ፡ ይኹን፤የርስት፡ይዞታ፡ይኾንላቸዋል።

17ነገር፡ግን፥ከባሪያዎቹ፡ለአንዱ፡ከርስቱ፡ስጦታ፡ቢሰጥ፥እስከ፡ነጻነት፡ዓመት፡ድረስ፡ለርሱ፡ ይኹን፤ከዚያም፡በዃላ፡ለአለቃው፡ይመለስ፤ርስቱ፡ግን፡ለልጆቹ፡ይኹን።

18አለቃውም፡ሕዝቡን፡ከይዞታቸው፡ያወጣቸው፡ዘንድ፥ከርስታቸው፡በግድ፡አይውሰድ፤ሕዝቤ፡ዅሉ፡ ከይዞታቸው፡እንዳይነቀሉ፡ከገዛ፡ይዞታው፡ለልጆች፡ርስትን፡ይስጥ።

19በበሩም፡አጠገብ፡ባለው፡መግቢያ፡ወደ፡ሰሜን፡ወደሚመለከተው፡ለካህናት፡ወደሚኾን፡ወደተቀደሰው፡ ዕቃ፡ቤት፡አገባኝ፤እንሆም፥በዃላው፡በምዕራብ፡በኩል፡አንድ፡ስፍራ፡ነበረ።

20ርሱም፦ካህናቱ፡ሕዝቡን፡ለመቀደስ፡ወደ፡ውጭው፡አደባባይ፡እንዳያወጡ፡የበደሉን፡መሥዋዕትና፡ የኀጢአቱን፡መሥዋዕት፡የሚቀቅሉበት፥የእኽሉንም፡ቍርባን፡የሚጋግሩበት፡ስፍራ፡ይህ፡ነው፡አለኝ።

21በውጭው፡አደባባይ፡አወጣኝ፡በአደባባይም፡ወዳለው፡ወደ፡አራቱ፡ማእዘን፡አዞረኝ፤እንሆም፥በአደባባዩ፡ ማእዘን፡ዅሉ፡አደባባይ፡ነበረ።

22በአደባባዩ፡በአራቱ፡ማእዘን፡ርዝመቱ፡አርባ፡ክንድ፡ወርዱም፡ሠላሳ፡ክንድ፡የኾነ፡የታጠረ፡አደባባይ፡ ነበረ፤በማእዘኑ፡ላሉ፡ለእነዚህ፡ለአራቱ፡ስፍራዎች፡አንድ፡ልክ፡ነበረ።

23በአራቱም፡ዙሪያ፡ዅሉ፡ግንብ፡ነበረ፥በግንቡም፡ሥር፡በዙሪያው፡የመቀቀያ፡ቦታ፡ነበረ።

24ርሱም፦እነዚህ፡የቤቱ፡አገልጋዮች፡የሕዝቡን፡መሥዋዕት፡የሚቀቅሉባቸው፡ስፍራዎች፡ናቸው፡አለኝ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source