1የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ፊትኽን፡ወደእስራኤል፡ተራራዎች፡አቅና፡ትንቢትም፡ተናገርባቸው።
3እንዲህም፡በል፦የእስራኤል፡ተራራዎች፡ሆይ፥የጌታን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ፤ጌታ፡እግዚአብሔር፡ ለተራራዎችና፡ለኰረብታዎች፡ለምንጮችና፡ለሸለቆዎች፡እንዲህ፡ይላል፦እኔ፥እንሆ፥እኔ፡ሰይፍን፡ አመጣባችዃለኹ፡የኰረብታው፡መስገጃዎቻችኹንም፡አጠፋለኹ።
4መሠዊያዎቻችኹም፡ይፈርሳሉ፥የፀሓይም፡ምስሎቻችኹ፡ይሰበራሉ፤ተወግተውም፡የሞቱትን፡ሰዎቻችኹን፡ በጣዖቶቻችኹ፡ፊት፡እጥላለኹ።
5የእስራኤልንም፡ልጆች፡ሬሳዎች፡በጣዖቶቻቸው፡ፊት፡አኖራለኹ፥ዐጥንቶቻችኹንም፡በመሠዊያዎቻችኹ፡ ዙሪያ፡እበትናለኹ።
6በምትኖሩበትም፡ስፍራ፡ዅሉ፡ከተማዎቹ፡ይፈርሳሉ፥የኰረብታው፡መስገጃዎችም፡ዅሉ፡ውድማ፡ ይኾናሉ፥መሠዊያዎቻችኹም፡ይፈርሳሉ፡ባድማም፡ይኾናሉ፥ጣዖቶቻችኹም፡ይሰበራሉ፡ያልቃሉም፥የፀሓይም፡ ምስሎቻችኹ፡ይቈረጣሉ፥ሥራችኹም፡ይሻራል።
7ተወግተውም፡የሞቱት፡በመካከላችኹ፡ይወድቃሉ፥እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ታውቃላችኹ።
8ነገር፡ግን፥በአገሮች፡በተበተናችኹ፡ጊዜ፡ከሰይፍ፡ያመለጡትን፡ቅሬታ፡በአሕዛብ፡መካከል፡ አስቀርላችዃለኹ።
9ከእናንተም፡የዳኑት፡ከእኔ፡በራቀው፡በአመንዝራ፡ልባቸውና፡ጣዖቶቻቸውን፡በተከተሉ፡በአመንዝራ፡ ዐይኖቻቸው፡የተሰበርኹትን፡እኔን፡ወደ፡እነርሱ፡በተማረኩት፡አሕዛብ፡መካከል፡ኾነው፡ ያስቡኛል፤በርኵሰታቸውም፡ዅሉ፡ስላደረጉት፡ክፋት፡ራሳቸውን፡ይጸየፋሉ።
10እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ፤ይህን፡ክፉ፡ነገር፡ኣደርግባቸው፡ዘንድ፡መናገሬ፡በከንቱ፡ አይደለም።
11ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእጅኽ፡አጨብጭብ፡በእግርኽም፡አሸብሽብ፡እንዲህም፡ በል፦በሰይፍና፡በራብ፡በቸነፈርም፡ይወድቃሉና፡ስለእስራኤል፡ቤት፡ስለ፡አስጸያፊ፡ሥራዎቻቸው፡ዅሉ፡ወዮ!
12በሩቅ፡ያለው፡በቸነፈር፡ይሞታል፥በቅርብም፡ያለው፡በሰይፍ፡ይወድቃል፥የቀረውና፡የዳነውም፡በራብ፡ ይሞታል፤እንዲሁ፡መዓቴን፡እፈጽምባቸዋለኹ።
13ተወግተውም፡የሞቱ፡ሰዎቻቸው፡በጣዖቶቻቸው፡መካከልና፡በመሠዊያዎቻቸው፡ዙሪያ፥ለጣዖቶቻቸው፡ ጣፋጭ፡ሽታ፡ባቀረቡበት፡ስፍራ፥ከፍ፡ባለው፡ኰረብታ፡ዅሉ፡በተራራዎችም፡ራስ፡ዅሉ፡ ላይ፥ከለመለመውም፡ዛፍ፡ዅሉ፡በታች፡ቅጠሉም፡ከበዛ፡ከአድባር፡ዛፍ፡ዅሉ፡በታች፡በኾኑ፡ጊዜ፡እኔ፡ እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ታውቃላችኹ።
14እጄንም፡እዘረጋባቸዋለኹ፥በሚኖሩበትም፡ስፍራ፡ዅሉ፡ምድሪቱን፡ከዴብላታ፡ምድረ፡በዳ፡ይልቅ፡ ውድማና፡በረሓ፡አደርጋታለኹ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ያውቃሉ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org