1በስድስተኛውም፡ዓመት፡በስድስተኛው፡ወር፡ከወሩም፡በዐምስተኛው፡ቀን፡በቤቴ፡ተቀምጬ፡ሳለኹ፡ የይሁዳም፡ሽማግሌዎች፡በፊቴ፡ተቀምጠው፡ሳሉ፥በዚያ፡የጌታ፡የእግዚአብሔር፡እጅ፡በላዬ፡ወደቀች።
2እኔም፡አየኹ፥እንሆም፥እንደ፡እሳት፡የሚመስል፡አምሳያ፡ነበረ፤ከወገቡም፡ምሳሌ፡ወደ፡ታች፡እሳት፡ ነበረ፥ከወገቡም፡ወደ፡ላይ፡እንደ፡ጸዳል፡ምሳሌ፥እንደሚብለጨለጭም፡የወርቅ፡ምሳሌ፡ነበረ።
3እጅ፡መሳይንም፡ዘረጋ፡በራስ፡ጠጕሬም፡ያዘኝ፤መንፈስም፡በምድርና፡በሰማይ፡መካከል፡ አነሣኝ፥በእግዚአብሔርም፡ራእይ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ወደ፡ሰሜን፡ወደሚመለከተው፡ወደ፡ውስጠኛው፡ አደባባይ፡በር፡መግቢያ፡አመጣኝ፤በዚያም፡ቅንአት፡የሚያነሣሣ፡የቅንአት፡ጣዖት፡ተተክሎ፡ነበር።
4እንሆም፥በቈላው፡እንዳየኹት፡ራእይ፡የእስራኤል፡አምላክ፡ክብር፡በዚያ፡ነበረ።
5ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ዐይንኽን፡ወደ፡ሰሜን፡መንገድ፡አንሣ፡አለኝ።ዐይኔንም፡ወደ፡ሰሜን፡ መንገድ፡አነሣኹ፤እንሆም፥በመሠዊያው፡በር፡በሰሜን፡በኩል፡በመግቢያው፡ይህ፡የቅንአት፡ጣዖት፡ነበረ።
6ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የሚያደርጉትን፥ከመቅደሴ፡ያርቁኝ፡ዘንድ፡የእስራኤል፡ቤት፡በዚህ፡ የሚያደርጉትን፡ታላቁን፡ርኵሰት፡ታያለኽን፧ደግሞም፡ተመልሰኽ፡ከዚህ፡የበለጠ፡ታላቅ፡ርኵሰት፡ታያለኽ፡ አለኝ።
7ወዳደባባዩም፡መግቢያ፡አመጣኝ፤ባየኹም፡ጊዜ፥እንሆ፥በግንቡ፡ውስጥ፡ፉካ፡ነበረ።
8ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ግንቡን፡ንደለው፡አለኝ፤ግንቡንም፡በነደልኹት፡ጊዜ፡መዝጊያ፡አገኘኹ።
9ርሱም፦ግባ፥በዚህም፡የሚያደርጉትን፡ክፉውን፡ርኵሰት፡እይ፡አለኝ።
10እኔም፡ገባኹና፥እንሆ፥በግንቡ፡ዙሪያ፡ላይ፡የተንቀሳቃሾችና፡የርኩሳን፡አራዊት፡ምሳሌ፡የእስራኤልንም፡ ቤት፡ጣዖታት፡ዅሉ፡ተስለው፡አየኹ።
11በፊታቸውም፡ከእስራኤል፡ቤት፡ሽማግሌዎች፡ሰባ፡ሰዎች፡ቆመው፡ነበር፥በመካከላቸውም፡የሳፋን፡ልጅ፡ ያእዛንያ፡ቆሞ፡ነበር፥ሰውም፡ዅሉ፡እያንዳንዱ፡በእጁ፡ጥናውን፡ይዞ፡ነበር፥የዕጣኑም፡ጢስ፡ሽቱ፡ይወጣ፡ ነበር።
12ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥የእስራኤል፡ቤት፡ሽማግሌዎች፡በጨለማ፡እያንዳንዱ፡በሥዕሉ፡ቤት፡ የሚያደርጉትን፡አይተኻልን፧እነርሱ፦እግዚአብሔር፡አያየንም፤እግዚአብሔር፡ምድሪቱን፡ትቷታል፡ይላሉና፡ አለኝ።
13ርሱም፦ደግሞ፡ተመልሰኽ፡ከዚህ፡የበለጠውን፡የሚያደርጉትን፡ታላቅ፡ርኵሰት፡ታያለኽ፡አለኝ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
14ወደ፡ሰሜንም፡ወደሚመለከተው፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡በር፡መግቢያ፡አመጣኝ፤እንሆም፥ሴቶች፡ ለተሙዝ፡እያለቀሱ፡በዚያ፡ተቀምጠው፡ነበር።
15ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ይህን፡አይተኻልን፧ደግሞ፡ተመልሰኽ፡ከዚህ፡የበለጠ፡ርኵሰት፡ታያለኽ፡ አለኝ።
16ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡ወደ፡ውስጠኛው፡አደባባይ፡አመጣኝ፥እንሆም፥በእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ መግቢያ፡ፊት፡በወለሉና፡በመሠዊያው፡መካከል፡ኻያ፡ዐምስት፡የሚያኽሉ፡ሰዎች፡ነበሩ፡ዠርባቸውም፡ ወደእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ፊታቸውም፡ወደ፡ምሥራቅ፡ነበረ፤እነርሱም፡ወደ፡ምሥራቅ፡ለፀሓይ፡ይሰግዱ፡ ነበር።
17ርሱም፦የሰው፡ልጅ፡ሆይ፥ይህን፡አይተኻልን፧በዚህ፡የሚያደርጉትን፡ይህን፡ርኵሰት፡ያደርጉ፡ዘንድ፡ ለይሁዳ፡ቤት፡ጥቂት፡ነገር፡ነውን፧ምድሪቱን፡በግፍ፡ሞልተዋታል፡ያስቈጡኝም፡ዘንድ፡ ተመልሰዋል፤እንሆም፥ቅርንጫፉን፡ወደ፡አፍንጫው፡አቅርበዋል።
18ስለዚህ፥እኔ፡ደግሞ፡በመዓት፡እሠራለኹ፤ዐይኔ፡አይራራም፡እኔም፡አላዝንም፤ወደ፡ዦሮዬም፡በታላቅ፡ ድምፅ፡ቢጮኹ፡አልሰማቸውም፡አለኝ።