Skip to content
← Ezra

Chapter 3 · Amharic

Ezra

1ሰባተኛውም፡ወር፡በደረሰ፡ጊዜ፥የእስራኤልም፡ልጆች፡በከተማዎቻቸው፡ሳሉ፥ሕዝቡ፡እንደ፡አንድ፡ሰው፡ ኾነው፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡ተሰበሰቡ።

2የኢዮሴዴቅም፡ልጅ፡ኢያሱ፥ወንድሞቹም፡ካህናቱ፥የሰላትያልም፡ልጅ፡ዘሩባቤል፡ወንድሞቹም፡ተነሥተው፡ በእግዚአብሔር፡ሰው፡በሙሴ፡ሕግ፡እንደ፡ተጻፈ፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ያቀርቡበት፡ዘንድ፡የእስራኤልን፡ አምላክ፡መሠዊያ፡ሠሩ።

3በአገሩም፡ካሉት፡አሕዛብ፡ፈርተው፡ነበርና፥መሠዊያውን፡በስፍራው፡ላይ፡አስቀመጡት፥በጧትና፡ በማታም፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡ለእግዚአብሔር፡አቀረቡበት።

4እንደተጻፈውም፡የዳስ፡በዓል፡አደረጉ፤እንደ፡ሥርዐቱም፡ለየዕለቱ፡የተገባውን፡የየዕለቱን፡የሚቃጠል፡ መሥዋዕት፡በቍጥር፡አቀረቡ።

5ከዚያም፡በዃላ፡ዘወትር፡የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፥የመባቻውንም፡መሥዋዕት፥የተቀደሱትንም፡ የእግዚአብሔር፡በዓላት፡ዅሉ፡መሥዋዕት፥ሰውም፡ዅሉ፡ለእግዚአብሔር፡በፈቃድ፡የሰጠውን፡ቍርባን፡ አቀረቡ።

6በሰባተኛው፡ወር፡በመዠመሪያው፡ቀን፡ለእግዚአብሔር፡የሚቃጠል፡መሥዋዕት፡ማቅረብ፡ ዠመሩ፤የእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ገና፡አልተመሠረተም፡ነበር።

7ለጠራቢዎችና፡ለዐናጢዎችም፡ገንዘብ፡ሰጡ፤የፋርስም፡ንጉሥ፡ቂሮስ፡እንደ፡ፈቀደላቸው፡የዝግባ፡ዛፍ፡ ከሊባኖስ፡በባሕር፡ወደ፡ኢዮጴ፡ያመጡ፡ዘንድ፡ለሲዶናና፡ለጢሮስ፡ሰዎች፡መብልና፡መጠጥ፡ዘይትም፡ሰጡ።

8በኢየሩሳሌም፡ወዳለው፡ወደእግዚአብሔር፡ቤት፡በመጡ፡በኹለተኛው፡ዓመት፡በኹለተኛው፡ወር፡ የሰላትያል፡ልጅ፡ዘሩባቤል፥የኢዮሴዴቅም፡ልጅ፡ኢያሱ፥የቀሩትም፡ወንድሞቻቸው፡ካህናትና፡ሌዋውያን፥ወደ፡ ኢየሩሳሌምም፡የተመለሱት፡ምርኮኛዎች፡ዅሉ፡ዠመሩ፤ሌዋውያንንም፡ከኻያ፡ዓመት፡ዠምሮ፡ከዚያም፡በላይ፡ የእግዚአብሔርን፡ቤት፡ሥራ፡እንዲያሠሩት፡ሾሟቸው።

9ኢያሱም፡ልጆቹም፡ወንድሞቹም፥የይሁዳም፡ልጆች፡ቀድምኤልና፡ልጆቹ፥የኤንሐዳድም፡ ልጆች፥ልጆቻቸውና፡ወንድሞቻቸው፡ሌዋውያንም፡የእግዚአብሔርን፡ቤት፡የሚሠሩትን፡ያሠሩ፡ዘንድ፡ በአንድነት፡ቆሙ።

10ዐናጢዎቹም፡የእግዚአብሔርን፡መቅደስ፡በመሠረቱ፡ጊዜ፡ካህናቱ፡ልብሳቸውን፡ለብሰው፡መለከቱን፡ ይዘው፥የአሣፍም፡ልጆች፡ሌዋውያን፡ጸናጽል፡ይዘው፡እንደ፡እስራኤል፡ንጉሥ፡እንደ፡ዳዊት፡ሥርዐት፡ እግዚአብሔርን፡ያመሰግኑ፡ዘንድ፡ቆሙ።

11ደግሞ፦ቸር፡ነውና፥ለእስራኤልም፡ምሕረቱ፡ለዘለዓለም፡ነውና፥እያሉ፡እግዚአብሔርንም፡እያመሰገኑና፡ እያከበሩ፡ርስ፡በርሳቸው፡ያስተዛዝሉ፡ነበር፤የእግዚአብሔርም፡ቤት፡ስለ፡ተመሠረተ፡ሕዝቡ፡ዅሉ፡ እግዚአብሔርን፡እያመሰገኑ፡በታላቅ፡ድምፅ፡እልል፡አሉ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

12የፊተኛውን፡ቤት፡ያዩ፡ሽማግሌዎች፡የኾኑ፡ብዙ፡ካህናትና፡ሌዋውያን፡የአባቶችም፡ቤቶች፡አለቃዎች፡ ግን፡ይህ፡መቅደስ፡በፊታቸው፡በተመሠረተ፡ጊዜ፡በታላቅ፡ድምፅ፡ያለቅሱ፡ነበር፤ብዙ፡ሰዎችም፡በደስታ፡ ይጮኹ፡ነበር፤

13ደስ፡ብሏቸው፡የሚጮኹትን፡ድምፅ፡ከሕዝቡ፡ልቅሶ፡ድምፅ፡መለየት፡የሚችል፡አልነበረም፤ሕዝቡም፡ በታላቅ፡ድምፅ፡ይጮኽ፡ነበር፥ድምፁም፡ከሩቅ፡ይሰማ፡ነበር።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source