1እስራኤል፡ፍሬው፡የበዛለት፡የለመለመ፡ወይን፡ነው፤እንደ፡ፍሬው፡ብዛት፡መሠዊያውን፡ አብዝቷል፤እንደ፡ምድሩም፡ማማር፡መጠን፡ሐውልቶችን፡እያሳመሩ፡ሠርተዋል።
2ልባቸው፡ተከፈለ፤አኹንም፡በደላቸውን፡ይሸከማሉ፤ርሱ፡መሠዊያቸውን፡ያፈርሳል፥ሐውልቶቻቸውን፡ ያጠፋል።
3አኹንም፦ንጉሥ፡የለንም፥እግዚአብሔርን፡አልፈራንምና፤ንጉሥስ፡ምን፡ያደርግልናል፧ይላሉ።
4የማይረባውን፡ቃል፡ይናገራሉ፤ቃል፡ኪዳን፡በገቡ፡ጊዜ፡በሐሰት፡ይምላሉ፤ስለዚህ፥መርዛም፡ሣር፡ በዕርሻ፡ትልም፡ላይ፡እንደሚበቅል፥መቅሠፍት፡ይበቅልባቸዋል።
5የሰማርያ፡ሰዎች፡ስለቤትአዌን፡እንቦሳ፡ይፈራሉ፤ክብሩም፡ከርሱ፡ዘንድ፡ወጥቷልና፥ሕዝቡ፡ ያለቅሱለታል፥የጣዖቱ፡ካህናትም፡በሐዘን፡ይንተባተባሉ።
6ለንጉሡ፡ለኢያሪም፡እጅ፡መንሻ፡ይኾን፡ዘንድ፡ወደ፡አሶር፡ይማረካል፤ኤፍሬምን፡ዕፍረት፡ ይይዘዋል፥እስራኤልም፡በምክሩ፡ያፍራል።
7ሰማርያ፡ከንጉሧ፡ጋራ፡በውሃ፡ላይ፡እንዳለ፡ዐረፋ፡ጠፍታለች።
8የእስራኤል፡ኀጢአት፡የኾኑት፡የአዌን፡የኰረብታው፡መስገጃዎች፡ይፈርሳሉ፤ሾኽና፡አሜከላ፡ በመሠዊያዎቻቸው፡ላይ፡ይበቅላል፤ተራራዎችንም፦ክደኑን፥ኰረብታዎችንም፦ውደቁብን፡ይሏቸዋል።
9እስራኤል፡ሆይ፥ከጊብዓ፡ዘመን፡ዠምረኽ፡ኀጢአትን፡ሠርተኻል፤በዚያ፡ጸንተዋል፤በጊብዓ፡ላይ፡ሰልፍ፡ አይደርስባቸውምን፧
10በፈቀድኹም፡ጊዜ፡እገሥጻቸዋለኹ፤ስለ፡ኹለቱም፡ኀጢአታቸው፡በታሰሩ፡ጊዜ፡አሕዛብ፡ይሰበሰቡባቸዋል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
11ኤፍሬም፡ማበራየት፡እንደ፡ለመደች፡ጊደር፡ነው፥እኔ፡ግን፡በዐንገቱ፡ውበት፡እጫንበታለኹ፤በኤፍሬም፡ ላይ፡እጠምድበታለኹ፥ይሁዳም፡ያርሳል፥ያዕቆብም፡ዐፈሩን፡ያለሰልሳል።
12እግዚአብሔር፡መጥቶ፡ጽድቅን፡እስኪያዘንብላችኹ፡ድረስ፡ርሱን፡የምትሹበት፡ዘመን፡ነውና፥ለእናንተ፡ በጽድቅ፡ዝሩ፥እንደ፡ምሕረቱም፡መጠን፡ዕጨዱ፥ጥጋታችኹንም፡ዕረሱ።
13ክፋትን፡ዐርሳችዃል፥ኀጢአትንም፡ዐጭዳችዃል፥የሐሰትንም፡ፍሬ፡በልታችዃል፤በኀያላንኽ፡ ብዛት፥በመንገድኽም፡ላይ፡ታምነኻልና።
14በሕዝብኽም፡መካከል፡ሽብር፡ይነሣል፤እናትም፡ከልጆቿ፡ጋራ፡በተፈጠፈጠች፡ጊዜ፡ሰልማን፡ ቤትአርብኤልን፡በሰልፍ፡ቀን፡እንዳፈረሰ፥ዐምባዎችኽ፡ዅሉ፡ይፈርሳሉ።
15ከኀጢአታችኹም፡ክፋት፡የተነሣ፡ቤቴል፡እንዲሁ፡ያደርግባችዃል፤በነጋ፡ጊዜ፡የእስራኤል፡ንጉሥ፡ፈጽሞ፡ ይጠፋል።