1እስራኤል፡ሕፃን፡በነበረ፡ጊዜ፡ወደድኹት፥ልጄንም፡ከግብጽ፡ጠራኹት።
2አብዝቼ፡ብጠራቸው፡አጥብቀው፡ከፊቴ፡ራቁ፤ለበዓሊምም፡ይሠዉ፡ነበር፥ለተቀረጹ፡ምስሎችም፡ያጥኑ፡ ነበር።
3እኔም፡ኤፍሬምን፡ክንዱን፡ይዤ፡በእግሩ፡እንዲኼድ፡መራኹት፤እኔም፡እፈውሳቸው፡እንደ፡ነበር፡ አላወቁም።
4በሰው፡ገመድ፡በፍቅርም፡እስራት፡ሳብዃቸው፤ለእነርሱም፡ቀምበርን፡ከጫንቃቸው፡ላይ፡እንደሚያነሣ፡ ኾንኹ፥ድርቆሽም፡ጣልኹላቸው።
5ወደ፡እኔ፡ይመለሱ፡ዘንድ፡አልወደዱምና፡ወደ፡ግብጽ፡ምድር፡ይመለሳሉ፥አሶርም፡ንጉሣቸው፡ይኾናል።
6ከመከሩትም፡ምክር፡የተነሣ፡ሰይፍ፡በከተማዎቻቸው፡ላይ፡ይወድቃል፥ከበርቴዎችንም፡ያጠፋል።
7ሕዝቤም፡ከእኔ፡ይመለሱ፡ዘንድ፡ወደዱ፤ወደ፡ላይም፡ቢጠሯቸው፡ማንም፡ከፍ፡ከፍ፡ያደርጋቸው፡ዘንድ፡ አይችልም።
8ኤፍሬም፡ሆይ፥እንዴት፡እጥልኻለኹ፧እስራኤል፡ሆይ፥እንዴትስ፡አሳልፌ፡እሰጥኻለኹ፧እንዴትስ፡እንደ፡ አዳማ፡እጥልኻለኹ፧እንዴትስ፡እንደ፡ሲባዮ፡አደርግኻለኹ፧ልቤ፡በውስጤ፡ተናውጣለች፥ምሕረቴም፡ ተነሣሥታለች።
9እኔ፡አምላክ፡ነኝ፡እንጂ፡ሰው፡አይደለኹምና፥በመካከልኽም፡ቅዱሱ፡ነኝና፡የቍጣዬን፡መቅሠፍት፡ አላደርግም፥ኤፍሬምንም፡አጠፋ፡ዘንድ፡አልመለስም፤በመዓትም፡አልመጣም።
10እግዚአብሔርን፡ይከተላሉ፥ርሱም፡እንደ፡አንበሳ፡ያገሣል፤ባገሣም፡ጊዜ፡ልጆች፡እየተንቀጠቀጡ፡ ከምዕራብ፡ይመጣሉ።
11እንደ፡ወፍም፡ከግብጽ፥እንደ፡ርግብም፡ከአሶር፡ምድር፡እየተንቀጠቀጡ፡ይመጣሉ፤በቤታቸውም፡ አኖራቸዋለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።