1ኤፍሬም፡በተናገረ፡ጊዜ፡ፍርሀት፡ነበረ፥በእስራኤልም፡ዘንድ፡ታበየ፤ነገር፡ግን፥በዓልን፡በማምለክ፡ በበደለ፡ጊዜ፡ሞተ።
2አኹንም፡ኀጢአትን፡ይሠሩ፡ዘንድ፡ጨመሩ፤በብራቸውም፡ለራሳቸው፡ቀልጦ፡የተሠራ፡ምስልን፥እንደ፡ ጥበባቸውም፡ጣዖታትን፡ሠርተዋል፤ዅሉም፡የሠራተኛ፡ሥራ፡ናቸው።ስለ፡እነርሱም፦የሚሠዉ፡ሰዎች፡ እንቦሳውን፡ይሳሙ፡ይላሉ።
3ስለዚህም፡እንደ፡ማለዳ፡ደመና፥በጧትም፡እንደሚያልፍ፡ጠል፥በዐውሎ፡ነፍስም፡ከዐውድማ፡ እንደሚበተን፡እብቅ፥ከመስኮትም፡እንደሚወጣ፡ጢስ፡ይኾናሉ።
4እኔ፡ግን፡ከግብጽ፡ምድር፡ዠምሬ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡ነኝ፤ከእኔም፡በቀር፡ሌላ፡አምላክ፡ አታውቅም፥ከእኔም፡በቀር፡ሌላ፡መድኀኒት፡የለም።
5በምድረ፡በዳ፥እጅግ፡በደረቀ፡ምድር፡ዐውቄኽ፡ነበር።
6ከተሰማሩ፡በዃላ፡ጠገቡ፥በጠገቡም፡ጊዜ፡ልባቸው፡ታበየ፤ስለዚህ፥ረሱኝ።
7ስለዚህም፡እኔ፡እንደ፡አንበሳ፡ኾንኹባቸው፥እንደ፡ነብርም፡በመንገድ፡አጠገብ፡አደባባቸዋለኹ፤
8ልጇ፡እንደ፡ተነጠቀባት፡ድብ፡እገጥማቸዋለኹ፥የልባቸውንም፡ስብ፡እቀዳ፟ለኹ፤በዚያም፡እንደ፡አንበሳ፡ እበላቸዋለኹ፥የምድረ፡በዳም፡አውሬ፡ይነጣጠቃቸዋል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
9እስራኤል፡ሆይ፥በእኔ፡በረዳትኽ፡ላይ፡በመነሣትኽ፡ጥፋትኽ፡ነው።
10በየከተማኽ፡ዅሉ፡ያድንኽ፡ዘንድ፡ንጉሥኽ፡ወዴት፡አለ፧ስለ፡እነርሱም፦ንጉሥንና፡አለቃዎችን፡ስጠኝ፡ ብለኽ፡የተናገርኸው፡መሳፍንቶችኽ፡ወዴት፡አሉ፧
11በቍጣዬ፡ንጉሥን፡ሰጠኹኽ፥በመዓቴም፡ሻርኹት።
12የኤፍሬም፡በደል፡ታስሯል፥ኀጢአቱም፡ተከማችቷል።
13ምጥ፡እንደ፡ያዛት፡ሴት፡ጭንቅ፡ይመጣበታል፤በሚወለድበት፡ጊዜ፡በማሕፀን፡አፍ፡ቀጥ፡ብሎ፡ አይወጣምና፡አእምሮ፡የሌለው፡ልጅ፡ነው።
14ከሲኦል፡እጅ፡እታደጋቸዋለኹ፥ከሞትም፡እቤዣቸዋለኹ፤ሞት፡ሆይ፥ቸነፈርኽ፡ወዴት፡አለ፧ሲኦል፡ ሆይ፥ማጥፋትኽ፡ወዴት፡አለ፧ርኅራኄ፡ከዐይኔ፡ተሰወረች።
15በወንድሞቹ፡መካከል፡ፍሬያማ፡ቢኾን፡የምሥራቅ፡ነፋስ፡ይመጣል፥የእግዚአብሔር፡ነፋስ፡ከምድረ፡በዳ፡ ይመጣል፤ምንጩንም፡ያደርቃል፥ፈሳሹንም፡ያጠፋል፥የተከበሩ፡ዕቃዎች፡ዅሉ፡ያሉበትን፡መዝገብ፡ ይበዘብዛል።
16ሰማርያ፡በአምላኳ፡ላይ፡ዐምፃለችና፡በደሏን፡ትሸከማለች፤በሰይፍ፡ይወድቃሉ፥ሕፃኖቻቸውም፡ ይፈጠፈጣሉ፥እርጕዞቻቸውም፡ይቀደዳሉ።