1እናንተ፡የእስራኤል፡ልጆች፡ሆይ፥እውነትና፡ምሕረት፡እግዚአብሔርንም፡ማወቅ፡በምድር፡ስለሌለ፡ እግዚአብሔር፡በምድሩ፡ላይ፡ከሚኖሩ፡ጋራ፡ክርክር፡አለውና፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ስሙ።
2ርግማንና፡ሐሰት፡ግዳይና፡ስርቆት፡ምንዝርናም፡ወጥተዋል፤ደምም፡ወደ፡ደም፡ደርሷል።
3ስለዚህ፥ምድሪቱ፡ታለቅሳለች፥በርሷም፡የሚቀመጡ፡ዅሉ፡ከምድር፡አራዊትና፡ከሰማይ፡ወፎች፡ጋራ፡ ይደክማሉ፤የባሕሩም፡ዓሣዎች፡ያልቃሉ።
4ነገር፡ግን፥ሕዝብኽ፡ከካህን፡ጋራ፡እንደሚከራከሩ፡ናቸውና፥ማንም፡አይከራከር፥ማንም፡አይዝለፍ።
5በቀንም፡ትሰናከላለኽ፥ነቢዩም፡ከአንተ፡ጋራ፡በሌሊት፡ይሰናከላል፤እናትኽንም፡አጠፋታለኹ።
6ሕዝቤ፡ዕውቀት፡ከማጣቱ፡የተነሣ፡ጠፍቷል፤አንተም፡ዕውቀትን፡ጠልተኻልና፥እኔ፡ካህን፡እንዳትኾነኝ፡ እጠላኻለኹ፤የአምላክኽንም፡ሕግ፡ረስተኻልና፥እኔ፡ደግሞ፡ልጆችኽን፡እረሳለኹ።
7እንደ፡ብዛታቸው፡መጠን፡ኀጢአት፡ሠሩብኝ፤እኔም፡ክብራቸውን፡ወደ፡ነውር፡እለውጣለኹ።
8የሕዝቤም፡ኀጢአት፡መብል፡ኾኖላቸዋል፥ልባቸውንም፡ወደ፡በደላቸው፡አድርገዋል።
9እንደ፡ሕዝቡም፡እንዲሁ፡ካህኑ፡ይኾናል፤በመንገዳቸውም፡እበቀላቸዋለኹ፥ሥራቸውንም፡ እመልስባቸዋለኹ።
10እግዚአብሔርንም፡መጠበቅ፡ትተዋልና፥ሲበሉ፡አይጠግቡም፥ሲያመነዝሩም፡አይበዙም።
11ግልሙትናና፡የወይን፡ጠጅ፡ስካርም፡አእምሮን፡ያጠፋል።
12የግልሙትና፡መንፈስ፡ሕዝቤን፡አስቷቸዋልና፥እነርሱም፡ከአምላካቸው፡ርቀው፡ አመንዝረዋልና፥በትራቸውን፡ይጠይቃሉ፥ዘንጋቸውም፡ይመልስላቸዋል።
13በተራራዎችም፡ራስ፡ላይ፡ይሠዋሉ፤ጥላውም፡መልካም፡ነውና፥ከኮምበልና፡ከልብን፣ከአሆማም፡ዛፍ፡ በታች፡በኰረብታዎች፡ላይ፡ያጥናሉ፤ስለዚህ፥ሴቶች፡ልጆቻችኹ፡ይገለሙታሉ፥ሙሽሮቻችኹም፡ያመነዝራሉ።
14ወንዶችም፡ደግሞ፡ከጋለሞታዎች፡ጋራ፡ይጫወታሉና፥ከጋለሞታዎችም፡ጋራ፡ይሠዋሉና፡ሴቶች፡ ልጆቻችኹ፡በገለሞቱ፡ጊዜ፥ሙሽሮቻችኹም፡ባመነዘሩ፡ጊዜ፡አልቀጣቸውም፤የማያስተውልም፡ሕዝብ፡ ይገለበጣል።
15እስራኤል፡ሆይ፥አንተ፡ብታመነዝር፡ይሁዳ፡አይበድል፤እናንተም፡ወደ፡ገልገላ፡አትግቡ፥ወደ፡ ቤትአዌንም፡አትውጡ፥ወይም፦ሕያው፡እግዚአብሔርን! ብላችኹ፡አትማሉ።
16እስራኤል፡እንደ፡እልከኛ፡ጊደር፡እንቢ፡ብሏል፤እግዚአብሔርስ፡በሰፊው፡ቦታ፡እንደ፡ጠቦት፡ ያሰማራዋልን፧
17ኤፍሬም፡ከጣዖታት፡ጋራ፡ተጋጠመ፤ተወው።
18ስካርን፡ፈጽመዋል፥ግልሙትናንም፡አብዝተዋል፤አለቃዎቿም፡ነውርን፡እጅግ፡ወደዱ።
19ነፋስ፡በክንፏ፡አስሯታል፤ከመሥዋዕታቸውም፡የተነሣ፡ያፍራሉ።