Skip to content
← Hosea

Chapter 7 · Amharic

Hosea

1በሐሰት፡አድርገዋልና፥ሌባም፡ገብቷልና፥በውጭም፡ወንበዴዎች፡ቀምተዋልና፥እስራኤልን፡እፈውስ፡ዘንድ፡ በወደድኹ፡ጊዜ፡የኤፍሬም፡ኀጢአትና፡የሰማርያ፡ክፋት፡ተገለጠ።

2እኔም፡ክፋታቸውን፡ዅሉ፡እንዳሰብኹ፡በልባቸው፡አያስቡም፡አኹንም፡ሥራቸው፡ከባ፟ቸዋለች፥በፊቴም፡ አለች።

3ንጉሡን፡በክፋታቸው፥አለቃዎቹንም፡በሐሰታቸው፡ደስ፡አሰኝተዋል።

4ዅሉም፡አመንዝራዎች፡ናቸው፤ጋጋሪ፡እንደሚያነድ፟በት፡እንደ፡ምድጃ፡ናቸው፤ዅሉ፡እስኪቦካ፡ድረስ፡ እሳትን፡መቈስቈስና፡ርሾን፡መለወስ፡ይቈያል።

5በንጉሣችን፡ቀን፡አለቃዎች፡ከወይን፡ጠጅ፡ሙቀት፡የተነሣ፡ታመሙ፤ርሱም፡ከዋዘኛዎች፡ጋራ፡እጁን፡ ዘረጋ።

6እያደቡ፡ልባቸውን፡እንደ፡ምድጃ፡አዘጋጅተዋል፤አበዛቸውም፡ሌሊቱን፡ዅሉ፡አንቀላፋ፤በጠባም፡ጊዜ፡ እንደ፡እሳት፡ነበልባል፡ይነዳል።

7ዅሉም፡እንደ፡ምድጃ፡ግለዋል፥ፈራጆቻቸውንም፡በሉ፤ነገሥታታቸውም፡ዅሉ፡ወደቁ፤ከነርሱም፡ወደ፡ እኔ፡የሚጮኽ፡የለም።

8ኤፍሬም፡ከአሕዛብ፡ጋራ፡ተደባለቀ፤ኤፍሬም፡እንዳልተገላበጠ፡ቂጣ፡ነው።

9እንግዳዎች፡ጕልበቱን፡በሉት፥ርሱም፡አላወቀም፤ሽበትም፡ወጣበት፥ርሱም፡አላወቀም።

10የእስራኤልም፡ትዕቢቱ፡በፊቱ፡መሰከረ፤ወደ፡አምላካቸው፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ግን፡ አልተመለሱም፥በዚህም፡ዅሉ፡አልፈለጉትም።

11ኤፍሬምም፡አእምሮ፡እንደሌላት፡እንደ፡ሰነፍ፡ርግብ፡ነው፤ግብጽን፡ጠሩ፥ወደ፡አሶርም፡ኼዱ።

12ሲኼዱ፡አሽክላዬን፡እዘረጋባቸዋለኹ፤እንደሰማይ፡ወፎች፡አወርዳቸዋለኹ፤መከራቸውን፡ሲሰሙ፡ እገሥጻቸዋለኹ።

13ከእኔ፡ፈቀቅ፡ብለዋልና፥ወዮላቸው! በእኔም፡ላይ፡ዐምፀዋልና፥ጥፋት፡ይምጣባቸው! እኔ፡ልታደጋቸው፡ ወደድኹ፥እነርሱ፡ግን፡በሐሰት፡ተናገሩብኝ።

14በመኝታቸው፡ላይ፡ኾነው፡ያለቅሱ፡ነበር፡እንጂ፡በልባቸው፡ወደ፡እኔ፡አልጮኹም፤ስለ፡እኽልና፡ስለ፡ ወይን፡ጠጅ፡ይሰበሰቡ፡ነበር፤በእኔም፡ላይ፡ዐመፁ።

15እኔም፡ክንዳቸውን፡አስተማርኹና፡አጸናኹ፤እነርሱ፡ግን፡ክፉ፡ነገርን፡መከሩብኝ።

16ወደ፡ከንቱ፡ነገር፡ተመለሱ፤እንደ፡ተንኰለኛ፡ቀስት፡ኾኑ፤አለቃዎቻቸው፡ከምላሳቸው፡ቍጣ፡የተነሣ፡ በሰይፍ፡ይወድቃሉ፤ይህ፡በግብጽ፡ምድር፡ውስጥ፡መሳለቂያ፡ይኾንባቸዋል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source