1መለከትን፡ወደ፡አፍኽ፡አቅርብ፤ቃል፡ኪዳኔን፡ተላልፈዋልና፥በሕጌም፡ላይ፡ዐምፀዋልና፥በእግዚአብሔር፡ ቤት፡ላይ፡እንደ፡ንስር፡ይመጣል።
2እነርሱም፦አምላክ፡ሆይ፥እኛ፡እስራኤል፡ዐወቅንኽ፡ብለው፡ወደ፡እኔ፡ይጮኻሉ።
3እስራኤል፡ደግነትን፡ጥሏል፤ጠላትም፡ያሳድዱታል።
4ለራሳቸው፡ነገሥታትን፡አነገሡ፥ከእኔም፡ዘንድ፡አይደለም፤አለቃዎችንም፡አደረጉ፥እኔም፡ አላወቅኹም፤ለጥፋታቸውም፡ከብራቸውና፡ከወርቃቸው፤ጣዖታትን፡ለራሳቸው፡አደረጉ።
5ሰማርያ፡ሆይ፥እንቦሳኽን፤ጥሏል፤ቍጣዬ፡በላያቸው፡ነዷ፟ል፤እስከ፡መቼ፡ድረስ፡ንጹሕ፡ሊኾኑ፡ አይችሉም፧
6ይህ፡ደግሞ፡ከእስራኤል፡ዘንድ፡ነው፤ሠራተኛ፡ሠራው፥ርሱም፡አምላክ፡አይደለም፤የሰማርያም፡እንቦሳ፡ ይቈራረጣል።
7ነፍስን፡ዘርተዋል፥ዐውሎ፡ነፍስንም፡ያጭዳሉ፤አገዳ፡የለውም፥ከፍሬውም፡ዱቄት፡አይገኝም፤ቢገኝም፡ እንግዳዎች፡ይበሉታል።
8እስራኤል፡ተውጧል፥በአሕዛብም፡መካከል፡ዛሬ፡እንደ፡ረከሰ፡ዕቃ፡ኾኗል።
9ለብቻውም፡እንደሚቀመጥ፡እንደ፡ምድረ፡በዳ፡አህያ፡ወደ፡አሶር፡ወጥተዋል፤ኤፍሬምም፡ወዳጆቹን፡ በእጅ፡መንሻ፡ገዛ።
10ነገር፡ግን፥ለአሕዛብ፡እጅ፡መንሻ፡ቢሰጡ፡እኔ፡አኹን፡እሰበስባቸዋለኹ፤ከንጉሥና፡ከአለቃዎችም፡ ሸክም፡የተነሣ፡ይደክማሉ።
11ኤፍሬም፡ኀጢአትን፡ለመሥራት፡መሠዊያ፡አብዝቷልና፥መሠዊያ፡ለኀጢአት፡ይኾንለታል።
12የሕጌን፡ብዛት፡ጽፌለታለኹ፤እነርሱ፡ግን፡እንደ፡እንግዳ፡ነገር፡ቈጥረውታል።
13መሥዋዕቴን፡ያቀርባሉ፥ሥጋንም፡ያርዳሉ፥ይበላሉም፤እግዚአብሔር፡ግን፡አይቀበላቸውም፤በደላቸውንም፡ ያስባል፥ኀጢአታቸውንም፡ይቀጣል፤እነርሱም፡ወደ፡ግብጽ፡ይመለሳሉ።
14እስራኤል፡ፈጣሪውን፡ረስቷል፥መስገጃዎችንም፡ሠርቷል፤ይሁዳም፡የተመሸጉትን፡ከተማዎች፡ አብዝቷል፤እኔ፡ግን፡በከተማዎች፡ላይ፡እሳትን፡እሰዳለኹ፥አዳራሾችንም፡ትበላለች።