Skip to content
← Isaiah

Chapter 11 · Amharic

Isaiah

1ከእሴይ፡ግንድ፡በትር፡ይወጣል፥ከሥሩም፡ቍጥቋጥ፡ያፈራል።

2የእግዚአብሔር፡መንፈስ፥የጥበብና፡የማስተዋል፡መንፈስ፥የምክርና፡የኀይል፡መንፈስ፥የዕውቀትና፡ እግዚአብሔርን፡የመፍራት፡መንፈስ፡ያርፍበታል።

3እግዚአብሔርን፡በመፍራት፡ደስታውን፡ያያል።ዐይኑም፡እንደምታይ፡አይፈርድም፥ዦሮውም፡እንደምትሰማ፡ አይበይንም፤

4ነገር፡ግን፥ለድኻዎች፡በጽድቅ፡ይፈርዳል፥ለምድርም፡የዋሆች፡በቅንነት፡ይበይናል፤በአፉም፡በትር፡ ምድርን፡ይመታል፥በከንፈሩም፡እስትንፋስ፡ክፉዎችን፡ይገድላል።

5የወገቡ፡መታጠቂያ፡ጽድቅ፥የጐኑም፡መቀነት፡ታማኝነት፡ይኾናል።

6ተኵላ፡ከበግ፡ጠቦት፡ጋራ፡ይቀመጣል፥ነብርም፡ከፍየል፡ጠቦት፡ጋራ፡ይተኛል፤ጥጃና፡የአንበሳ፡ደቦል፡ ፍሪዳም፡በአንድነት፡ያርፋሉ፤ታናሽም፡ልጅ፡ይመራቸዋል።

7ላምና፡ድብ፡ዐብረው፡ይሰማራሉ፥ግልገሎቻቸውም፡በአንድነት፡ያርፋሉ፤አንበሳም፡እንደ፡በሬ፡ገለባ፡ ይበላል።

8የሚጠባውም፡ሕፃን፡በእባብ፡ጕድጓድ፡ላይ፡ይጫወታል፥ጡት፡የጣለውም፡ሕፃን፡በእፍኝት፡ቤት፡ላይ፡ እጁን፡ይጭናል።

9በተቀደሰው፡ተራራዬ፡ዅሉ፡ላይ፡አይጐዱም፡አያጠፉምም፤ውሃ፡ባሕርን፡እንደሚከድን፡ምድር፡ እግዚአብሔርን፡በማወቅ፡ትሞላለችና።

10በዚያም፡ቀን፡እንዲህ፡ይኾናል፤ለአሕዛብ፡ምልክት፡ሊኾን፡የቆመውን፡የእሴይን፡ሥር፡አሕዛብ፡ ይፈልጉታል፤ማረፊያውም፡የተከበረ፡ይኾናል።

11በዚያም፡ቀን፡እንዲህ፡ይኾናል፤የቀረውን፡የሕዝቡን፡ቅሬታ፡ከአሶርና፡ከግብጽ፥ከጳትሮስና፡ ከኢትዮጵያ፥ከዔላምና፡ከሰናዖር፡ከሐማትም፥ከባሕርም፡ደሴቶች፡ይመልስ፡ዘንድ፡ጌታ፡እንደ፡ገና፡እጁን፡ ይገልጣል።

12ለአሕዛብም፡ምልክትን፡ያቆማል፥ከእስራኤልም፡የተጣሉትን፡ይሰበስባል፥ከይሁዳም፡የተበተኑትን፡ከአራቱ፡ የምድር፡ማእዘኖች፡ያከማቻል።

13የኤፍሬምም፡ምቀኝነት፡ይርቃል፥ይሁዳንም፡የሚያስጨንቁ፡ይጠፋሉ፤ኤፍሬምም፡በይሁዳ፡ አይቀናም፥ይሁዳም፡ኤፍሬምን፡አያስጨንቅም።

14በምዕራብም፡በኩል፡በፍልስጥኤማውያን፡ጫንቃ፡ላይ፡እየበረሩ፡ይወርዳሉ፥የምሥራቅንም፡ልጆች፡ በአንድነት፡ይበዘብዛሉ፤በኤዶምያስና፡በሞዐብም፡ላይ፡እጃቸውን፡ይዘረጋሉ፥የዐሞንም፡ልጆች፡ለእነርሱ፡ ይታዘዛሉ።

15እግዚአብሔርም፡የግብጽን፡ባሕር፡ያጠፋል፤በትኵሱም፡ነፋስ፡እጁን፡በወንዙ፡ላይ፡ያነሣል፥ሰባት፡ ፈሳሾችንም፡አድርጎ፡ይመታዋል፥ሰዎችም፡በጫማቸው፡እንዲሻገሩ፡ያደርጋቸዋል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

16ከግብጽም፡በወጣ፡ጊዜ፡ለእስራኤል፡እንደ፡ነበረ፥ለቀረው፡ለሕዝቡ፡ቅሬታ፡ከአሶር፡ጐዳና፡ይኾናል።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source