1ስለ፡ደማስቆ፡የተነገረ፡ሸክም፦እንሆ፥ደማስቆ፡ከተማ፡ከመኾን፡ተቋርጣለች፤ባድማና፡የፍርስራሽ፡ ክምር፡ትኾናለች።
2ከተማዎቿ፡ለዘለዓለም፡የተፈቱ፡ይኾናሉ፤ለመንጋ፡ማሰማሪያ፡ይኾናሉ፤መንጋዎች፡በዚያ፡ያርፋሉ፡ የሚያስፈራቸውም፡የለም።
3ምሽግም፡ከኤፍሬም፥መንግሥትም፡ከደማስቆ፡ተወገደች፤የሶርያም፡ቅሬታ፡እንደ፡እስራኤል፡ልጆች፡ ክብር፡ይኾናል፡ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
4በዚያም፡ቀን፡እንዲህ፡ይኾናል፤የያዕቆብ፡ክብር፡ይደክማል፡የሥጋውም፡ውፍረት፡ይከሳል።
5ዐጫጅ፡የቆመውን፡እኽል፡በእጁ፡ሰብስቦ፡ዛላውን፡እንደሚያጭድ፡ይኾናል፤በራፋይም፡ሸለቆ፡ቃርሚያ፡ እንደሚለቅም፡እንዲሁ፡ይኾናል።
6ወይራ፡በተመታ፡ጊዜ፡ኹለት፡ወይም፡ሦስት፡ፍሬ፡በራሱ፡ላይ፡እንደሚቀር፥አራት፡ወይም፡ዐምስት፡ በዛፊቱ፡ጫፍ፡እንደሚገኝ፥በርሱ፡ዘንድ፡ቃርሚያ፡ይቀራል፡ይላል፡የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር።
7በዚያ፡ቀን፡ሰው፡ወደ፡ፈጣሪው፡ይመለከታል፥ዐይኖቹም፡ወደእስራኤል፡ቅዱስ፡ያያሉ።
8እጁም፡የሠራችውን፡መሠዊያ፡አይመለከትም፤ጣቶቹም፡ወዳበጇቸው፥ወደማምለኪያ፡ዐጸዶች፡ወይም፡ ወደፀሓይ፡ምስሎች፥አያይም።
9በዚያም፡ቀን፡በእስራኤል፡ልጆች፡ፊት፡የአሞራውያንና፡የኤውያውያን፡ከተማዎች፡እንደ፡ተፈቱ፥እንዲሁ፡ ከተማዎችኽ፡ይፈታሉ፥ባድማም፡ይኾናሉ።
10የደኅንነትኽን፡አምላክ፡ረስተኻል፥የረድኤትኽንም፡ጌታ፡አላሰብኽም፤ስለዚህ፥ያማረውን፡ተክል፡ ተክለኻል፥እንግዳንም፡ዘር፡ዘርተኻል።
11በተከልኽበት፡ቀን፡ታበቅለዋለኽ፥በነጋውም፡ዘርኽን፡እንዲያብብ፡ታደርገዋለኽ፤ነገር፡ግን፥በሐዘንና፡ በትካዜ፡ቀን፡መከሩ፡ይሸሻል።
12እንደ፡ባሕር፡ሞገድ፡ድምፅ፡ለሚተምሙ፡ለወገኖች፡ብዛት፥እንደ፡ኀይለኛም፡ውሃ፡ጩኸት፡ለሚጮኹ፡ አሕዛብ፡ወዮላቸው!
13አሕዛብ፡እንደ፡ብዙ፡ውሃ፡ጩኸት፡ይጮኻሉ፤ርሱ፡ግን፡ይገሥጻቸዋል፥እነርሱም፡እየሸሹ፡ ይርቃሉ፥በተራራም፡ላይ፡እንዳለ፡እብቅ፡በነፋስ፡ፊት፥ዐውሎ፡ነፋስ፡እንደሚያዞረው፡ትቢያ፡ይበተናሉ።
14በመሸ፡ጊዜ፥እንሆ፥ድንጋጤ፡አለ፤ከማለዳም፡በፊት፡አይገኙም።የዘረፉን፡ሰዎች፡ዕድል፡ ፈንታ፥የበዘበዙን፡ዕጣ፡ይህ፡ነው።