1በኢትዮጵያ፡ወንዞች፡ማዶ፡ላለች፥ክንፍ፡ያላቸው፡መርከቦች፡ላሉባት፥
2መልእክተኛዎችን፡በባሕር፡ላይ፡የደንገል፡መርከቦችንም፡በውሃ፡ላይ፡ለምትልክ፡ምድር፡ወዮላት! እናንተ፡ ፈጣኖች፡መልእክተኛዎች፡ሆይ፥ወደ፡ረዥምና፡ወደ፡ለስላሳ፡ሕዝብ፥ከመዠመሪያው፡አስደንጋጭ፡ወደ፡ኾነ፡ ወገን፥ወደሚሰፍርና፡ወደሚረግጥ፥ወንዞችም፡ምድራቸውን፡ወደሚከፍሉት፡ሕዝብ፡ኺዱ።
3በዓለም፡የምትኖሩ፡ዅሉና፡በምድር፡የምትቀመጡ፡ሆይ፥ምልክት፡በተራራዎች፡ላይ፡በተነሣ፡ጊዜ፡ እዩ፤መለከትም፡በተነፋ፡ጊዜ፡ስሙ።
4እግዚአብሔር፦በፀሓይ፡ጮራ፡እንደ፡ደረቅ፡ትኵሳት፥በዐጨዳም፡ወራት፡እንደ፡ጠል፡ደመና፡ኾኜ፡ በማደሪያዬ፡በጸጥታ፡ተቀምጬ፡እመለከታለኹ፡ብሎኛልና።
5ርሱ፡ከመከር፡በፊት፡አበባ፡በረገፈ፡ጊዜ፡የወይንም፡ፍሬ፡ጨርቋ፡ሲይዝ፡የወይኑን፡ዘንግ፡በማጭድ፡ ይቈርጣል፥ጫፎቹንም፡ይመለምላል፣ያስወግድማል።
6በተራራ፡ላይ፡ላሉ፡ነጣቂዎች፡ወፎች፥ለምድርም፡አውሬዎች፡በአንድነት፡ይቀራሉ፤ነጣቂዎችም፡ወፎች፡ ይባጁባቸዋል፥የምድርም፡አውሬዎች፡ዅሉ፡ይከርሙባቸዋል።
7በዚያን፡ዘመን፡ለሰራዊት፡ጌታ፡ለእግዚአብሔር፥ከረዥምና፡ከለስላሳ፡ሕዝብ፥ከመዠመሪያው፡አስደንጋጭ፡ ከኾነ፡ወገን፥ከሚሰፍርና፡ከሚረግጥ፥ወንዞችም፡ምድራቸውን፡ከሚከፍሉት፡ሕዝብ፡ዘንድ፡እጅ፡መንሻ፡ የሰራዊት፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ስም፡ወደሚገኝበት፡ስፍራ፡ወደጽዮን፡ተራራ፡ይቀርባል።