1ስለ፡ግብጽ፡የተነገረ፡ሸክም፦እንሆ፥እግዚአብሔር፡በፈጣን፡ደመና፡እይበረረ፡ወደ፡ግብጽ፡ ይመጣል፤የግብጽም፡ጣዖታት፡በፊቱ፡ይርዳሉ፥የግብጽም፡ልብ፡በውስጧ፡ይቀልጣል።
2ግብጻውያንን፡በግብጻውያን፡ላይ፡አስነሣለኹ፤ወንድምም፡ወንድሙን፥ሰውም፡ባልንጀራውን፥ከተማም፡ ከተማን፥መንግሥትም፡መንግሥትን፡ይወጋል።
3የግብጽም፡መንፈስ፡በውስጧ፡ባዶ፡ይኾናል፥ምክራቸውንም፡አጠፋለኹ፤እነርሱም፡ጣዖቶቻቸውን፡ በድግምት፡የሚጠነቍሉትንም፡መናፍስት፡ጠሪዎቻቸውንም፡ጠንቋዮቻቸውንም፡ይጠይቃሉ።
4ግብጻውያንንም፡በጨካኝ፡ጌታ፡እጅ፡አሳልፌ፡እሰጣለኹ፤ጨካኝ፡ንጉሥም፡ይገዛቸዋል፡ይላል፡የሰራዊት፡ ጌታ፡እግዚአብሔር።
5ውሃዎችም፡ከባሕር፡ይደርቃሉ፥ወንዙም፡ያንሳል፡ደረቅም፡ይኾናል።
6ወንዞቹም፡ይገማሉ፥የግብጽም፡መስኖች፡ያንሳሉ፡ይደርቃሉም፤ደንገልና፡ቄጤማ፡ይጠወልጋሉ።
7በአባይ፡ወንዝ፡ዳር፡ያለው፡መስክ፡በአባይም፡ወንዝ፡አጠገብ፡የተዘራ፡ዕርሻ፡ዅሉ፡ ይደርቃል፥ይበተንማል፥አይገኝምም።
8ዓሣ፡አጥማጆቹ፡ያዝናሉ፥በአባይም፡ወንዝ፡መቃጥን፡የሚጥሉት፡ዅሉ፡ያለቅሳሉ፥በውሃዎችም፡ላይ፡ መረብ፡የሚዘረጉት፡ይዝላሉ።
9የተበጠረውንም፡የተልባ፡እግር፡የሚሠሩ፥ነጩንም፡ልብስ፡የሚሠሩ፡ሸማኔዎች፡ያፍራሉ።
10ደገፋዎቿም፡ዅሉ፡ይሰባበራሉ፥የደመ፡ወዘኛዎችም፡ነፍስ፡ትተክዛለች።
11የጣኔዎስ፡አለቃዎች፡ፍጹም፡ሰነፎች፡ናቸው፤ፈርዖንን፡የሚመክሩ፡ጥበበኛዎች፡ምክራቸው፡ድንቍርና፡ ኾነች።ፈርዖንን፦እኛ፡የጥበበኛዎች፡ልጆች፡የቀደሙም፡ነገሥታት፡ልጆች፡ነን፡እንዴት፡ትሉታላችኹ፧
12አኹንሳ፡ጥበበኛዎችኽ፡የት፡አሉ፧አኹን፡ይንገሩኽ፤የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡በግብጽ፡ላይ፡ ያሰበውን፡ይወቁ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
13የጣኔዎስ፡አለቃዎች፡ሰነፎች፡ኾነዋል፥የሜምፎስም፡አለቃዎች፡ተሸንግለዋል፤የነገዶቿ፡የማእዘን፡ ድንጋዮች፡የኾኑ፡ግብጽን፡አሳቱ።
14እግዚአብሔር፡የጠማምነትን፡መንፈስ፡በውስጧ፡ደባልቋል፤ሰካር፡በትፋቱ፡እንዲስት፡እንዲሁ፡ግብጽን፡ በሥራዋ፡ዅሉ፡አሳቱ።
15ራስ፡ወይም፡ዥራት፡የሰሌን፡ቅርንጫፍ፡ወይም፡እንግጫ፡ቢኾን፡ሊሠራ፡የሚችል፡ሥራ፡ለግብጽ፡ አይኾንላትም።
16በዚያ፡ቀን፡ግብጻውያን፡እንደ፡ሴቶች፡ይኾናሉ፥የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔርም፡በእነርሱ፡ላይ፡ ከሚያንቀሳቅሳት፡ከእጁ፡መንቀሳቀስ፡የተነሣ፡ይሸበራሉ፡ይፈሩማል።
17የይሁዳም፡ምድር፡ግብጽን፡የምታስደነግጥ፡ትኾናለች፤የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡ከመከረባት፡ምክር፡ የተነሣ፡ወሬዋን፡የሚሰማ፡ዅሉ፡ይፈራል።
18በዚያ፡ቀን፡በግብጽ፡ምድር፡በከነዓን፡ቋንቋ፡የሚናገሩ፥በሰራዊት፡ጌታ፡በእግዚአብሔርም፡የሚምሉ፡ ዐምስት፡ከተማዎች፡ይኾናሉ፤ከነዚህም፡አንዲቱ፡የጥፋት፡ከተማ፡ተብላ፡ትጠራለች።
19በዚያ፡ቀን፡በግብጽ፡ምድር፡መካከል፡ለእግዚአብሔር፡መሠዊያ፥በዳርቻዋም፡ለእግዚአብሔር፡ዐምድ፡ ይኾናል።
20ይህም፡ለሰራዊት፡ጌታ፡ለእግዚአብሔር፡በግብጽ፡ምድር፡ምልክትና፡ምስክር፡ይኾናል፤ከሚያስጨንቋቸው፡ የተነሣ፡ወደ፡እግዚአብሔር፡ይጮኻሉና፥ርሱም፡መድኀኒትንና፡ኀያልን፡ሰዶ፟፡ያድናቸዋልና።
21በዚያም፡ቀን፡እግዚአብሔር፡በግብጽ፡የታወቀ፡ይኾናል፥ግብጻውያንም፡እግዚአብሔርን፡ ያውቃሉ፤በመሥዋዕትና፡በቍርባን፡ያመልካሉ፥ለእግዚአብሔርም፡ስእለት፡ይሳላሉ፡ይፈጽሙትማል።
22እግዚአብሔርም፡ግብጽን፡ይመታታል፤ይመታታል፡ይፈውሳታልም፤ወደ፡እግዚአብሔርም፡ይመለሳሉ፡ ርሱም፡ይለመናቸዋል፡ይፈውሳቸውማል።
23በዚያ፡ቀን፡ከግብጽ፡ወደ፡አሶር፡መንገድ፡ይኾናል፥አሶራዊውም፡ወደ፡ግብጽ፥ግብጻዊውም፡ወደ፡ አሶር፡ይገባል፤ግብጻውያንም፡ከአሶራውያን፡ጋራ፡ይሰግዳሉ።
25የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፦ሕዝቤ፡ግብጽ፥የእጄም፡ሥራ፡አሶር፥ርስቴም፡እስራኤል፡የተባረከ፡ ይኹን፡ብሎ፡ይባርካቸዋልና፥በዚያ፡ቀን፡እስራኤል፡ለግብጽና፡ለአሶር፡ሦስተኛ፡ይኾናል፥በምድርም፡መካከል፡ በረከት፡ይኾናል።