1ስለ፡ጢሮስ፡የተነገረ፡ሸክም።የተርሴስ፡መርከቦች፡ሆይ፥አልቅሱ፤ፈርሷልና፥ቤት፡የለም፥መግባትም፡ የለም፤ከኪቲም፡አገር፡ዠምሮ፡ተገልጦላቸዋል።
2እናንተ፡በደሴት፡የምትኖሩ፡በባሕርም፡የምትሻገሩ፡የሲዶና፡ነጋዴዎች፡ንግድ፡የሞሉባችኹ፡ሆይ፥ጸጥ፡ በሉ።
3የሺሖር፡ዘርና፡የአባይ፡ወንዝ፡መከር፡በብዙ፡ውሃዎች፡ላይ፡ገቢዋ፡ነበረ፤ርሷም፡የአሕዛብ፡መናገጃ፡ ነበረች።
4ሲዶና፡ሆይ፥ባሕር፥የባሕር፡ምሽግ፦አላማጥኹም፥አልወለድኹም፤ጐበዛዝትንም፡ አላሳደግኹም፥ደናግልንም፡አላሳደግኹም፡ብሎ፡ተናግሯልና፥ዕፈሪ።
5ወሬዋ፡ወደ፡ግብጽ፡በደረሰ፡ጊዜ፡በጢሮስ፡ወሬ፡ምጥ፡ይይዛቸዋል።
6ወደ፡ተርሴስ፡ተሻገሩ፤እናንተ፡በደሴት፡የምትኖሩ፡አልቅሱ።
7በቀድሞ፡ዘመን፡ተመሥርታ፡የነበረችው፥በዚያም፡እንደ፡እንግዳ፡ኾና፡ትኖር፡ዘንድ፡እግሮቿ፡ወደ፡ሩቅ፡ ያፈለሷት፡የደስታችኹ፡ከተማ፡ይህች፡ናትን፧
8አክሊል፡ባስጫነች፡ከተማ፡በጢሮስ፡ላይ፡ይህን፡የወሰነ፡ማን፡ነው፧ነጋዴዎቿ፡አለቃዎች፡ ናቸው፥በርሷም፡የሚሸጡና፡የሚለውጡ፡የምድር፡ክቡራን፡ናቸው።
9የክብርን፡ዅሉ፡ትዕቢት፡ይሽር፡ዘንድ፡የምድርንም፡ክቡራን፡ዅሉ፡ያስንቅ፡ዘንድ፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር፡ወስኖታል።
10የተርሴስ፡ልጅ፡ሆይ፥የሚከለክልሽ፡የለምና፡እንደ፡አባይ፡ወንዝ፡በአገርሽ፡ላይ፡ጐርፈሽ፡ዕለፊ።
11በባሕር፡ላይ፡እጁን፡ዘረጋ፡መንግሥታትንም፡አናወጠ፤ምሽጎቿንም፡ያጠፉ፡ዘንድ፡እግዚአብሔር፡ ስለከነዓን፡አገር፡አዘዘ።
12ርሱም፦አንቺ፡የተበደልሽ፡የሲዶና፡ድንግል፡ልጅ፡ሆይ፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ደስ፡አይበልሽ፤ተነሥተሽ፡ ወደ፡ኪቲም፡ተሻገሪ፥በዚያም፡ደግሞ፡አታርፊም፡አለ።
13እንሆ፥የከለዳውያን፡አገር! ይህ፡ሕዝብ፡ኾኖ፡አይገኝም፤አሶራውያን፡ለምድረ፡በዳ፡አራዊት፡ ሰጥተውታል፤ግንቦቻቸውን፡ሠሩ፥አዳራሾቿንም፡አፈረሱ፥ባድማም፡አደረጓት።
14እናንተ፡የተርሴስ፡መርከቦች፡ሆይ፥ምሽጋችኹ፡ፈርሷልና፥ዋይ፡በሉ።
15በዚያም፡ቀን፡እንዲህ፡ይኾናል፤ጢሮስ፡እንደ፡አንድ፡ንጉሥ፡ዘመን፡ሰባ፡ዓመት፡ያኽል፡የተረሳች፡ ትኾናለች፤ከሰባ፡ዓመት፡በዃላ፡ግን፡ለጢሮስ፡በጋለሞታ፡ዘፈን፡እንደሚኾን፡እንዲሁ፡ይኾናል።
16አንቺ፡የተረሳሽ፡ጋለሞታ፡ሆይ፥መሰንቆ፡ያዢ፡በከተማ፡ላይም፡ዙሪ፤መታሰቢያም፡ይኾንልሽ፡ዘንድ፡ ዜማን፡አሳምሪ፡ዘፈንሽንም፡አብዢ።
17ከሰባ፡ዓመትም፡በዃላ፡እግዚአብሔር፡ጢሮስን፡ይጐበኛታል፥ወደ፡ዋጋዋም፡ትመለሳለች፥ደግሞም፡ በምድር፡ፊት፡ላይ፡ከኾኑ፡ከዓለም፡መንግሥታት፡ዅሉ፡ጋራ፡ትገለሙታለች።
18ንግዷና፡ዋጋዋ፡ለእግዚአብሔር፡የተቀደሰ፡ይኾናል፤ንግዷም፡በልተው፡ይጠግቡ፡ዘንድ፡ማለፊያም፡ልብስ፡ ይለብሱ፡ዘንድ፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ለሚኖሩ፡ይኾናል፡እንጂ፡በዕቃ፡ቤትና፡በግምጃ፡ቤት፡ውስጥ፡ አይከተትም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org