1እንሆ፥እግዚአብሔር፡ምድርን፡ባዶ፡ያደርጋታል፥ባድማም፡ያደርጋታል፥ይገለብጣትማል፥በርሷም፡ የተቀመጡትን፡ይበትናል።
2እንደ፡ሕዝቡም፡እንዲሁ፡ካህኑ፥እንደ፡ባሪያውም፡እንዲሁ፡ጌታው፥እንደ፡ባሪያዪቱም፡እንዲሁ፡ እመቤቷ፥እንደሚገዛም፡እንዲሁ፡የሚሸጠው፥እንደ፡አበዳሪውም፡እንዲሁ፡ተበዳሪው፥እንደ፡ዕዳ፡አስከፋዩም፡ እንዲሁ፡ዕዳ፡ከፋዩ፡ይኾናል።
3ምድር፡መፈታትን፡ትፈታለች፥ፈጽማም፡ትበላሻለች፤እግዚአብሔር፡ይህን፡ቃል፡ተናግሯልና።
4ምድርም፡አለቀሰች፥ረገፈችም፤ዓለም፡ደከመች፥ረገፈችም፤የምድርም፡ሕዝብ፡ታላላቆች፡ደከሙ።
5ምድርም፡ከሚቀመጡባት፡በታች፡ረክሳለች፥ሕጉን፡ተላልፈዋልና፥ሥርዐቱንም፡ ለውጠዋልና፥የዘለዓለሙንም፡ቃል፡ኪዳን፡አፍርሰዋልና።
6ስለዚህ፥መርገም፡ምድርን፡ትበላለች፥በርሷም፡የተቀመጡ፡ይቀጣሉ፤ስለዚህ፥የምድር፡ሰዎች፡ ይቃጠላሉ፥ጥቂት፡ሰዎችም፡ይቀራሉ።
7የወይን፡ጠጅ፡አለቀሰች፥የወይን፡ንግድ፡ደከመች፥ልባቸው፡ደስ፡ያለው፡ዅሉ፡ተከዙ።
8የከበሮው፡ሐሤት፡ቀርቷል፥የደስተኛዎች፡ድምፅ፡ዝም፡ብሏል፥የመሰንቆ፡ደስታ፡ቀርቷል።
9እየዘፈኑም፡የወይን፡ጠጅን፡አይጠጡትም፥የሚያሰክርም፡መጠጥ፡ለሚጠጡት፡መራራ፡ይኾናል።
10ባድማ፡የኾነችው፡ከተማ፡ፈረሰች፤ቤት፡ዅሉ፡ማንም፡እንዳይገባበት፡ተዘጋ።
11ስለወይኑም፡ጠጅ፡በአደባባይ፡ጩኸት፡ይኾናል፤ደስታ፡ዅሉ፡ጨልሟል፥የምድርም፡ሐሤት፡ፈርሷል።
12ከተማዪቱም፡ባድማ፡ኾናለች፥በሯም፡በጥፋት፡ተመትቷል።
13የወይራን፡ዛፍ፡እንደ፡መምታት፥ከወይንም፡መከር፡በዃላ፡ቃርሚያውን፡እንደ፡መልቀም፥እንዲሁ፡ በምድር፡መካከል፡በአሕዛብም፡መካከል፡ይኾናል።
14እነዚህ፡ድምፃቸውን፡ያነሣሉ፥እልልም፡ይላሉ፥ስለእግዚአብሔር፡ክብርም፡ከባሕር፡ይጣራሉ።
15ስለዚህ፥እግዚአብሔርን፡በምሥራቅ፥የእስራኤልንም፡አምላክ፡የእግዚአብሔርንም፡ስም፡በባሕር፡ደሴቶች፡ አክብሩ።
16ለጻድቁ፡ክብር፡ይኹን፡የሚለውን፡ዝማሬ፡ከምድር፡ዳርቻ፡ሰምተናል።እኔ፡ ግን፦ከሳኹ፥ከሳኹ፥ወዮልኝ! ወንጀለኛዎች፡ወንጅለዋል፤ወንጀለኛዎች፡እጅግ፡ወንጅለዋል፡አልኹ።
17በምድር፡ላይ፡የምትኖር፡ሆይ፥ፍርሀትና፡ገደል፡ወጥመድም፡ባንተ፡ላይ፡አሉ።
18የሰማይ፡መስኮቶች፡ተከፍተዋልና፥የምድርም፡መሠረት፡ተናውጣለችና፥ከፍርሀት፡ድምፅ፡የሸሸ፡በገደል፡ ይወድቃል፥ከገደልም፡የወጣ፡በወጥመድ፡ይያዛል።
19ምድር፡ተሰባበረች፥ምድር፡ፈጽማ፡ደቀቀች፥ምድር፡ተነዋወጠች።
20ምድር፡እንደ፡ሰካር፡ሰው፡ትንገዳገዳለች፥እንደ፡ዳስም፡ትወዛወዛለች፤መተላለፏ፡ ይከብድባታል፥ትወድቅማለች፥ደግማም፡አትነሣም።
21በዚያም፡ቀን፡እንደዚህ፡ይኾናል፤እግዚአብሔር፡በከፍታ፡ያለውን፡ሰራዊት፡በከፍታ፡ላይ፥በምድርም፡ ያሉትን፡ነገሥታት፡በምድር፡ላይ፡ይቀጣቸዋል።
22ግዞተኛዎች፡በጕድጓድ፡እንደሚከማቹ፡በአንድነት፡ይከማቻሉ፥በግዞት፡ቤትም፡ውስጥ፡ተዘግተው፡ ይኖራሉ፥ከብዙ፡ቀንም፡በዃላ፡ይጐበኛሉ።
23የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔርም፡በጽዮን፡ተራራና፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡ይነግሣልና፥በሽማግሌዎቹም፡ፊት፡ ክብር፡ይኾናልና፥ጨረቃ፡ይታወካል፡ፀሓይም፡ያፍራል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org