Skip to content
← Isaiah

Chapter 26 · Amharic

Isaiah

1በዚያም፡ቀን፡ይህ፡ቅኔ፡በይሁዳ፡ምድር፡ይዘመራል።የጸናች፡ከተማ፡አለችን፤ለቅጥርና፡ለምሽግ፡ መድኀኒትን፡ያኖርባታል።

2እውነትን፡የሚጠብቅ፡ጻድቅ፡ሕዝብ፡ይገባ፡ዘንድ፡በሮችን፡ክፈቱ።

3ባንተ፡ታምናለችና፡ባንተ፡ለምትደገፍ፡ነፍስ፡ፈጽመኽ፡በሰላም፡ትጠብቃታለኽ።

4ጌታ፡እግዚአብሔር፡የዘለዓለም፡ዐምባ፡ነውና፥ለዘለዓለም፡በእግዚአብሔር፡ታመኑ።

5በከፍታ፡የሚኖሩትን፡ሰዎች፡ዝቅ፡ያደርጋል፤ከፍ፡ያለችውን፡ከተማ፡ያዋርዳል፥እስከ፡መሬትም፡ድረስ፡ ያዋርዳታል፥እስከ፡ዐፈርም፡ድረስ፡ይጥላታል።

6እግር፥የድኻ፡እግርም፡የችግረኛም፡አረጋገጥ፥ትረግጣታለች።

7የጻድቃን፡መንገድ፡ቅን፡ናት፤አንተ፡ቅን፡የኾንኽ፡የጻድቃንን፡መንገድ፡ታቃናለኽ።

8አቤቱ፥በፍርድኽ፡መንገድ፡ተስፋ፡አድርገንኻል፥ስምኽም፡መታሰቢያኽም፡የነፍሳችን፡ምኞት፡ነው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

9ፍርድኽን፡በምድር፡ባደረግኽ፡ጊዜ፡በዓለም፡የሚኖሩት፡ጽድቅን፡ይማራሉና፡ነፍሴ፡በሌሊት፡ ትናፍቅኻለች፥መንፈሴም፡በውስጤ፡ወዳንተ፡ትገሠግሣለች።

10ለኀጢአተኛ፡ሞገስ፡ቢደረግለት፡ጽድቅን፡አይማርም፤በቅኖች፡ምድር፡ክፉን፡ነገር፡ ያደርጋል፥የእግዚአብሔርንም፡ግርማ፡አያይም።

11አቤቱ፥እጅኽ፡ከፍ፡ከፍ፡አለች፡አላዩምም፤ነገር፡ግን፥በሕዝብኽ፡ላይ፡ያለኽን፡ቅንአት፡አይተው፡ ያፍራሉ፤እሳትም፡ጠላቶችኽን፡ትበላለች።

12አቤቱ፥ሥራችንን፡ዅሉ፡ሠርተኽልናልና፥ሰላምን፡ትሰጠናለኽ።

13አቤቱ፡አምላካችን፡ሆይ፥ከአንተ፡በቀር፡ሌላዎች፡ጌታዎች፡ገዝተውናል፤ነገር፡ግን፥ባንተ፡ብቻ፡ ስምኽን፡እናስባለን።

14እነርሱ፡ሞተዋል፥በሕይወት፡አይኖሩም፤ጠፍተዋል፥አይነሡም፤ስለዚህ፥አንተ፡ ጐብኝተኻቸዋል፥አጥፍተኻቸውማል፥መታሰቢያቸውንም፡ዅሉ፡ምንም፡ምን፡አድርገኻል።

15ሕዝብን፡አበዛኽ፥አቤቱ፥ሕዝብን፡አበዛኽ፤አንተም፡ተከበርኽ፥የአገሪቱንም፡ዳርቻ፡ዅሉ፡አሰፋኽ።

16አቤቱ፥በመከራ፡ጊዜ፡ፈለጉኽ፥በገሰጽኻቸውም፡ጊዜ፡ልመናቸውን፡ወዳንተ፡አፈሰሱ።

17የፀነሰች፡ሴት፡ለመውለድ፡ስትቀርብ፡እንደምትጨነቅና፡በምጥ፡እንደምትጮኽ፥አቤቱ፥እንዲሁ፡በፊትኽ፡ ኾነናል።

18እኛ፡ፀንሰናል፡ምጥም፡ይዞናል፥ነፋስንም፡እንደምንወልድ፡ኾነናል፤በምድርም፡ደኅንነት፡ አላደረግነም፤በዓለምም፡የሚኖሩ፡ይወድቃሉ።

19ሙታንኽ፡ሕያዋን፡ይኾናሉ፥ሬሳዎችም፡ይነሣሉ።በምድር፡የምትኖሩ፡ሆይ፥ጠልኽ፡የብርሃን፡ጠል፡ ነውና፥ምድርም፡ሙታንን፡ታወጣለችና፡ንቁ፡ዘምሩም።

20ሕዝቤ፡ሆይ፥ና፡ወደ፡ቤትኽም፡ግባ፥ደጅኽን፡በዃላኽ፡ዝጋ፡ቍጣ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡ጥቂት፡ጊዜ፡ ተሸሸግ።

21በምድር፡በሚኖሩት፡ላይ፡በበደላቸው፡ምክንያት፡ቍጣውን፡ያመጣባቸው፡ዘንድ፥እንሆ፥እግዚአብሔር፡ ከስፍራው፡ይወጣል፤ምድርም፡ደሟን፡ትገልጣለች፥ሙታኗንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አትከድንም።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source