1ዳዊት፡ለሰፈረባት፡ከተማ፡ለአርኤል፡ወዮላት! ዓመት፡በዓመት፡ላይ፡ጨምሩ፥በዓላትም፡ይመለሱ።
2አርኤልንም፡አስጨንቃለኹ፥ልቅሶና፡ዋይታም፡ይኾንባታል፤እንደ፡አርኤልም፡ትኾንልኛለች።
3በዙሪያሽም፡እሰፍራለኹ፥በቅጥርም፡ከብቤ፡አስጨንቅሻለኹ፥ዐምባም፡በላይሽ፡አቆማለኹ።
4ትዋረጂማለሽ፥በመሬትም፡ላይ፡ኾነሽ፡ትናገሪያለሽ፥ቃልሽም፡ዝቅ፡ብሎ፡ከዐፈር፡ይወጣል፤ድምፅሽም፡ ከመሬት፡እንደሚወጣ፡እንደ፡መናፍስት፡ጠሪ፡ድምፅ፡ይኾናል፥ቃልሽም፡ከዐፈር፡ወጥቶ፡ይጮኻል።
5ነገር፡ግን፥የጠላቶችሽ፡ብዛት፡እንደ፡ደቀቀ፡ትቢያ፥የጨካኞችም፡ብዛት፡እንደሚያልፍ፡ገለባ፡ይኾናል።
6ድንገትም፡ፈጥኖ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡በነጐድጓድ፥በምድርም፡መናወጥ፥በታላቅም፡ ድምፅ፥በዐውሎ፡ነፋስም፥በወጨፎም፥በምትበላም፡በእሳት፡ነበልባል፡ይጐበኛታል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
7በአርኤልም፡ላይ፡የሚዋጉ፥ርሷንና፡ምሽጓንም፡የሚወጉ፡የሚያስጨንቋትም፥የአሕዛብ፡ዅሉ፡ብዛት፡እንደ፡ ሕልምና፡እንደ፡ሌሊት፡ራእይ፡ይኾናል።
8ተርቦም፡እንደሚያልም፡ሰው፡ይኾናል፤በሕልሙም፥እንሆ፥ይበላል፥ነገር፡ግን፥ይነቃል፡ሰውነቱም፡ባዶ፡ ነው፤ተጠምቶም፡እንደሚያልም፡ሰው፡ይኾናል፤በሕልሙም፥እንሆ፥ይጠጣል፥ነገር፡ ግን፥ይነቃል፥እንሆም፥ይዝላል፡ሰውነቱም፡አምሮት፡አለው፤እንዲሁ፡የጽዮንን፡ተራራ፡የሚወጉ፡የአሕዛብ፡ ዅሉ፡ብዛት፡ይኾናል።
9ተደነቁ፡ደንግጡም፤ተጨፈኑም፡ዕውሮችም፡ኹኑ፤በወይን፡ጠጅ፡አይኹን፡እንጂ፡ሰከሩ፤በሚያሰክር፡ መጠጥ፡አይኹን፡እንጂ፡ተንገደገዱ።
10እግዚአብሔር፡የእንቅልፍ፡መንፈስ፡አፍሶ፟ባችዃል፡ዐይኖቻችኹን፡ነቢያትንም፡ጨፍኖባችዃል፡ራሶቻችኹን፡ ባለራእዮችን፡ሸፍኖባችዃል።
11ራእዩም፡ዅሉ፡እንደ፡ታተመ፡መጽሐፍ፡ቃል፡ኾኖባችዃል፤ማንበብንም፡ለሚያውቅ፦ይህን፡አንብ፟፡ ብለው፡በሰጡት፡ጊዜ፡ርሱ፦ታትሟልና፥አልችልም፡ይላቸዋል፤
12ደግሞም፡መጽሐፉን፡ማንበብን፡ለማያውቅ፦ይህን፡አንብ፟፡ብለው፡በሰጡት፡ጊዜ፡ርሱ፦ማንበብ፡ አላውቅም፡ይላቸዋል።
13ጌታም፦ይህ፡ሕዝብ፡በአፉ፡ወደ፡እኔ፡ይቀርባልና፥በከንፈሮቹም፡ያከብረኛልና፥ልቡ፡ግን፡ከእኔ፡የራቀ፡ ነውና፥በሰዎች፡ሥርዐትና፡ትምህርት፡ብቻ፡ይፈራኛልና፥
14ስለዚህ፥እንሆ፥ድንቅ፡ነገርን፡በዚህ፡ሕዝብ፡መካከል፥ድንቅ፡ነገርን፡ተኣምራትንም፥እንደ፡ገና፡ አደርጋለኹ፤የጥበበኛዎችም፡ጥበብ፡ትጠፋለች፥የአስተዋዮችም፡ማስተዋል፡ትሰወራለች።
15ምክራቸውን፡ጥልቅ፡አድርገው፡ከእግዚአብሔር፡ለሚሰውሩ፥ሥራቸውንም፡በጨለማ፡ውስጥ፡ አድርገው።ማን፡ያየናል፧ወይስ፡ማን፡ያውቀናል፧ለሚሉ፡ወዮላቸው!
16ይህ፡የእናንተ፡ጠማምነት፡ነው፤እንደ፡ሸክላ፡ሠሪ፡ጭቃ፡የምትቈጠሩ፡አይደላችኹምን፧በእውኑ፡ሥራ፡ ሠሪውን፦አልሠራኸኝም፡ይለዋልን፧ወይስ፡የተደረገው፡አድራጊውን፦አታስተውልም፡ይለዋልን፧
17ሊባኖስ፡እንደ፡ፍሬያማ፡ዕርሻ፡ሊለወጥ፡ፍሬያማውም፡ዕርሻ፡እንደ፡ዱር፡ሊቈጠር፡ጥቂት፡ዘመን፡ የቀረ፡አይደለምን፧
18በዚያም፡ቀን፡ደንቈሮዎች፡የመጽሐፍን፡ቃል፡ይሰማሉ፥የዕውሮችም፡ዐይኖች፡ከጭጋግና፡ከጨለማ፡ ተለይተው፡ያያሉ።
19የዋሃን፡ደስታቸውን፡በእግዚአብሔር፡ያበዛሉ፥በሰዎች፡መካከል፡ያሉ፡ችግረኛዎችም፡ሐሤትን፡በእስራኤል፡ ቅዱስ፡ያደርጋሉ።
20ጨካኙ፡ሰው፡አልቋልና፥ፌዘኛውም፡ጠፍቷልና፥ለኀጢአትም፡የደፈጡ፡ዅሉ፡ይቈረጣሉና፤
21እነዚህም፡ሰውን፡በነገር፡በደለኛ፡የሚያደርጉ፥በበርም፡ለሚገሥጸው፡አሽክላ፡የሚያኖሩ፥ጻድቁንም፡ በከንቱ፡ነገር፡የሚያስቱ፡ናቸው።
22ስለዚህ፥አብርሃምን፡የተቤዠ፡እግዚአብሔር፥ስለያዕቆብ፡ቤት፡እንዲህ፡ይላል፦ያዕቆብ፡አኹን፡ አያፍርም፥ፊቱም፡አኹን፡አይለወጥም።
23ነገር፡ግን፥የእጄን፡ሥራ፡ልጆቹን፡በመካከሉ፡ባያቸው፡ጊዜ፡ስሜን፡ይቀድሳሉ፤የያዕቆብንም፡ቅዱስ፡ ይቀድሳሉ፥የእስራኤልንም፡አምላክ፡ይፈራሉ።
24በመንፈስም፡የሳቱ፡ማስተዋልን፡ያውቃሉ፥የሚያጕረመርሙም፡ትምህርትን፡ይቀበላሉ።