1ለዐመፀኛዎች፡ልጆች፡ወዮላቸው! ይላል፡እግዚአብሔር፤ከእኔ፡ዘንድ፡ያልኾነን፡ምክር፡ ይመክራሉ፥ኀጢአትንም፡በኀጢአት፡ላይ፡ይጨምሩ፡ዘንድ፡ከመንፈሴ፡ዘንድ፡ያልኾነውን፡ቃል፡ኪዳን፡ ያደርጋሉ።
2ከአፌም፡ነገርን፡ሳይጠይቁ፡በፈርዖን፡ኀይል፡ይጸኑ፡ዘንድ፡በግብጽም፡ጥላ፡ይታመኑ፡ዘንድ፡ወደ፡ግብጽ፡ እንዲወርዱ፡ይኼዳሉ።
3ስለዚህ፥የፈርዖን፡ኀይል፡ዕፍረት፥በግብጽም፡ጥላ፡መታመን፡ስድብ፡ይኾንባችዃል።
4አለቃዎች፡ምንም፡በጣኔዎስ፡ቢኾኑ፥መልክተኛዎችም፡ምንም፡ወደ፡ሓኔስ፡ቢደርሱ፥
5ዅላቸው፡ይጠቅሟቸው፡ዘንድ፡ስለማይችሉ፥ዕፍረትና፡ስድብ፡እንጂ፡ረድኤትና፡ረብ፡ስለማይኾኑ፡ሕዝብ፡ ያፍራሉ።
6በደቡብ፡ስላሉ፡እንስሳዎች፡የተነገረ፡ሸክም።ተባትና፡እንስት፡አንበሳ፡እፍኝትም፡ነዘር፡እባብም፡ በሚወጡባት፡በመከራና፡በጭንቀት፡ምድር፡በኩል፡ብልጥግናቸውን፡በአህያዎች፡ጫንቃ፡ላይ፡ መዛግብቶቻቸውንም፡በግመሎች፡ሻኛ፡ላይ፡እየጫኑ፡ወደማይጠቅሟቸው፡ሕዝብ፡ይኼዳሉ።
7የግብጽ፡ርዳታ፡ከንቱና፡ምናምን፡ነው፤ስለዚህ፥ስሙን፦በቤት፡የሚቀመጥ፡ረዓብ፡ብዬ፡ጠርቼዋለኹ።
8አኹንም፡ኺድ፥ለሚመጣውም፡ዘመን፡ለዘለዓለም፡እንዲኾን፡በሰሌዳ፡ላይ፡በመጽሐፍም፡ውስጥ፡ ጻፍላቸው።
9ዐመፀኛ፡ወገንና፡የእግዚአብሔርን፡ሕግ፡ለመስማት፡የማይወዱ፡የሐሰት፡ልጆች፡ናቸውና፤
10ባለራእዮችን፦አትመልከቱ፡ይላሉ፥ነቢያትንም፦ጣፋጩንና፡አታላዩን፡ነገር፡እንጂ፡ቅኑን፡ነገር፡ አትንገሩን፡ከመንገድ፡ፈቀቅ፡በሉ፥
11ከጐዳናውም፡ዘወር፡በሉ፥የእስራኤልንም፡ቅዱስ፡ከእኛ፡ዘንድ፡አስወግዱ፡ይሏቸዋል።
12ስለዚህ፥የእስራኤል፡ቅዱስ፡እንዲህ፡ይላል፦ይህችን፡ቃል፡አቃላ፟ችዃልና፥በግፍና፡በጠማምነት፡ ታምናችዃልና፥በርሱም፡ተደግፋችዃልና፥
13ስለዚህ፥ይህ፡በደል፡አዘብዝቦ፡ለመፍረስ፡እንደ፡ቀረበ፥አፈራረሱም፡ፈጥኖ፡ድንገት፡እንደሚመጣ፡ እንደ፡ረዥም፡ቅጥር፡ይኾንባችዃል።
14የሸክለኛ፡ማድጋ፡እንደሚሰበር፡ይሰብረዋል፥ሳይራራም፡ያደቀ፟ዋል፤ከስባሪውም፡እሳት፡ከማንደጃ፡ የሚወስዱበት፡ወይም፡ውሃ፡ከጕድጓድ፡የሚቀዱበት፡ገል፡አይገኝም።
15የእስራኤል፡ቅዱስ፥ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦በመመለስና፡በማረፍ፡ትድናላችኹ፤በጸጥታና፡ በመታመን፡ኀይል፡ይኾንላችዃል፤እናንተም፡እንቢ፡አላችኹ፥
16ነገር፡ግን፦በፈረስ፡ላይ፡ተቀምጠን፡እንሸሻለን፡እንጂ፡እንዲህ፡አይኾንም፡አላችኹ፥ስለዚህም፡ ትሸሻላችኹ፤ደግሞም፦በፈጣን፡ፈረስ፡ላይ፡እንቀመጣለን፡አላችኹ፥ስለዚህም፡የሚያሳድዷችኹ፡ፈጣኖች፡ ይኾናሉ።
17ካንድ፡ሰው፡ዛቻ፡የተነሣ፡ሺሕ፡ሰዎች፡ይሸሻሉ፤እናንተም፡በተራራ፡ራስ፡ላይ፡እንዳለ፡ ምሰሶ፥በኰረብታም፡ላይ፡እንዳለ፡ምልክት፡ኾናችኹ፡እስክትቀሩ፡ድረስ፥ከዐምስት፡ሰዎች፡ዛቻ፡የተነሣ፡ ትሸሻላችኹ።
18እግዚአብሔርም፡የፍርድ፡አምላክ፡ነውና፥ስለዚህ፡እግዚአብሔር፡ይራራላችኹ፡ዘንድ፡ ይታገሣል፥ይምራችኹም፡ዘንድ፡ከፍ፡ከፍ፡ይላል፤ርሱን፡በመተማመን፡የሚጠባበቁ፡ዅሉ፡ብፁዓን፡ናቸው።
19በኢየሩሳሌም፡ውስጥ፡በጽዮን፡የምትኖሩ፡ሕዝብ፡ሆይ፥ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አታለቅስም፤በጩኸትም፡ ድምፅ፡ይራራልኻል፥በሰማኽም፡ጊዜ፡ይመልስልኻል።
20ጌታም፡የጭንቀትን፡እንጀራና፡የመከራን፡ውሃ፡ቢሰጥኽም፡አስተማሪኽ፡እንግዲህ፡ከአንተ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org አይሰወርም፤ዐይኖችኽ፡ግን፡አስተማሪኽን፡ያያሉ፥
21ወደ፡ቀኝም፡ወደ፡ግራም፡ፈቀቅ፡ብትል፡ዦሮዎችኽ፡በዃላኽ፦መንገዱ፡ይህች፡ናት፡በርሷም፡ኺድ፡ የሚለውን፡ቃል፡ይሰማሉ።
22በብርም፡የተለበጡትን፡የተቀረጹትን፡ምስሎችኽን፡በወርቅም፡የተለበጡትን፡ቀልጠው፡የተሠሩትን፡ ምስሎችኽን፡ታረክሳለኽ፤እንደ፡ርኩስም፡ነገር፡ትጥላቸዋለኽ፦ወግዱ፡ትላቸውማለኽ።
23በምድርም፡ለተዘራው፡ዘርኽ፡ዝናብ፡ይሰጣል፥ከምድርም፡ፍሬ፡የሚወጣ፡እንጀራ፡ወፍራምና፡ብዙ፡ ይኾናል።በዚያም፡ቀን፡ከብቶችኽ፡በሰፊ፡መስክ፡ይሰማራሉ፤
24መሬትንም፡የሚያርሱ፡በሬዎችና፡አህያዎች፡በመንሽና፡በወንፊት፡የነጻውን፡ጨው፡ጨው፡የሚለውን፡ ገፈራ፡ይበላሉ።
25በታላቅም፡እልቂት፡ቀን፡ግንቦች፡በወደቁ፡ጊዜ፡በረዥሙ፡ተራራ፡ዅሉ፡ከፍ፡ባለውም፡ኰረብታ፡ዅሉ፡ ላይ፡ወንዞችና፡የውሃ፡ፈሳሾች፡ይኾናሉ።
26እግዚአብሔርም፡የሕዝቡን፡ስብራት፡በጠገነ፡ዕለት፥መቅሠፍቱ፡የቈሰለውንም፡በፈወሰ፡ዕለት፥የጨረቃ፡ ብርሃን፡እንደ፡ፀሓይ፡ብርሃን፥የፀሓይም፡ብርሃን፡እንደ፡ሰባት፡ቀን፡ብርሃን፡ሰባት፡ዕጥፍ፡ይኾናል።
27እንሆ፥የእግዚአብሔር፡ስም፡ከሚነድ፟፡ቍጣ፡ከሚትጐለጐልም፡ጢስ፡ጋራ፡ከሩቅ፡ይመጣል፤ከንፈሮቹም፡ ቍጣን፡የሞሉ፡ናቸው፥ምላሱም፡እንደምትበላ፡እሳት፡ናት፤
28እስትንፋሱም፡አሕዛብን፡በአጥፊ፡ወንፊት፡ሊነፋቸው፡እንደሚያጥለቀልቅ፡እስከ፡ዐንገትም፡እንደሚደርስ፡ ወንዝ፡ነው፥በሕዝብም፡መንጋጋ፡የሚያስት፡ልጓም፡ይኾናል።
29ዝማሬ፡በተቀደሰች፡የዐውደ፡ዓመት፡ሌሊት፡እንደሚኾን፡ዝማሬ፡ይኾንላችዃል፤ወደእግዚአብሔርም፡ ተራራ፡ወደእስራኤል፡ዐምባ፡ይመጣ፡ዘንድ፡እንቢልታ፡ይዞ፡እንደሚኼድ፡ሰው፡የልብ፡ደስታ፡ይኾንላችዃል።
30እግዚአብሔርም፡ክቡር፡ድምፁን፡ያሰማል፥የክንዱንም፡መውረድ፡በሚነድ፟፡ቍጣውና፡በምትበላ፡እሳት፡ ነበልባል፡በዐውሎ፡ነፋስም፡በወጨፎም፡በበረዶ፡ጠጠርም፡ይገልጣል።
31አሶርም፡በበትር፡ከመታው፡ከእግዚአብሔር፡ድምፅ፡የተነሣ፡ይደነግጣል።
32እግዚአብሔር፡በላዩ፡በሚያወርድበት፡የታዘዘበቱ፡የበትር፡ድብደባ፡ዅሉ፡በከበሮና፡በመሰንቆ፡ ይኾናል፤በጦርነትም፡ክንዱን፡አንሥቶ፡ይዋጋቸዋል።
33ከቀድሞም፡ዠምሮ፡የማቃጠያ፡ስፍራ፡ተዘጋጅታለች፥ለንጉሥም፡ተበጅታለች፤ጥልቅና፡ሰፊም፡ አድርጓታል፤እሳትና፡ብዙ፡ማገዶ፡ተከምሯል፤የእግዚአብሔርም፡እስትንፋስ፡እንደ፡ዲን፡ፈሳሽ፡ያቃጥለዋል።