Skip to content
← Isaiah

Chapter 3 · Amharic

Isaiah

1እንሆ፥የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡ከኢየሩሳሌምና፡ከይሁዳ፡ድጋፍንና፡ብርታትን፥የእንጀራን፡ድጋፍ፡ ዅሉ፡የውሃውንም፡ድጋፍ፡ዅሉ፥

2ኀያሉንም፥ተዋጊውንም፥ፈራጁንም፥ነቢዩንም፥ሟርተኛውንም፥

3ሽማግሌውንም፥የዐምሳ፡አለቃውንም፥ከበርቴውንም፥አማካሪውንም፥ብልኁንም፡ሠራተኛ፥አስማት፡ ዐዋቂውንም፡ይነቅላል።

4አለቃዎቻቸው፡እንዲኾኑ፡ብላቴናዎችን፡አስነሣባቸዋለኹ፥ሕፃናትም፡ይገዟቸዋል።

5ሕዝቡም፥ሰው፡በሰው፡ላይ፡ሰውም፡በባልንጀራው፡ላይ፥ይገፋፋል፤ብላቴናውም፡በሽማግሌው፡ላይ፡ የተጠቃውም፡በከበርቴው፡ላይ፡ይኰራል።

6ሰውም፡በአባቱ፡ቤት፡ውስጥ፡ወንድሙን፡ይዞ፦አንተ፡ልብስ፡አለኽ፡አለቃም፡ኹንልን፡ይህችም፡ባድማ፡ ከእጅኽ፡በታች፡ትኹን፡ሲለው፥

7በዚያ፡ቀን፡ድምፁን፡ከፍ፡አድርጎ፦እኔ፡በቤቴ፡ውስጥ፡እንጀራ፡ወይም፡ልብስ፡የለኝምና፡ባለመድኀኒት፡ አልኾንም፤በሕዝቡም፡ላይ፡አለቃ፡አታደርጉኝም፡ይላል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

8የክብሩን፡ዐይን፡ያስቈጡ፡ዘንድ፡ምላሳቸውና፡ሥራቸው፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ነውና፥ኢየሩሳሌም፡ ተፈታች፥ይሁዳም፡ወደቀ።

9የፊታቸውም፡ዕፍረት፡ይመሰክርባቸዋል፤እንደ፡ሰዶምም፡ኀጢአታቸውን፡ ያወራሉ፥አይሰውሯትም።በራሳቸው፡ላይ፡ክፉ፡ነገርን፡ሠርተዋልና፥ለነፍሳቸው፡ወዮ!

10የሥራቸውን፡ፍሬ፡ይበላሉና፡ጻድቁን፦መልካም፡ይኾንልኻል፡በሉት።

11እንደ፡እጁ፡ሥራ፡ፍዳው፡ይደረግበታልና፥ለበደለኛ፡ወዮ! ክፉም፡ደርሶበታል።

12ሕዝቤንስ፡አስገባሪዎቻቸው፡ይገፏቸዋል፥አስጨናቂዎችም፡ይሠለጥኑባቸዋል።ሕዝቤ፡ሆይ፥የመሯችኹ፡ ያስቷችዃል፡የምትኼዱበትንም፡መንገድ፡ያጠፋሉ።

13እግዚአብሔር፡ለፍርድ፡ተነሥቷል፡በሕዝቡም፡ላይ፡ሊፈርድ፡ቆሟል።

14እግዚአብሔር፡ከሕዝቡ፡ሽማግሌዎችና፡ከአለቃዎቻቸው፡ጋራ፡ይፋረዳል፤የወይኑን፡ቦታ፡የጨረሳችኹ፡ እናንተ፡ናችኹ፤ከድኻዎች፡የበዘበዛችኹት፡በቤታችኹ፡አለ፤

15ሕዝቤንም፡ለምን፡ታደቋ፟ቸዋላችኹ፧የድኻዎችንስ፡ፊት፡ለምን፡ትፈጫላችኹ፧ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።

16ደግሞም፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡አለ፦የጽዮን፡ቈነዣዥት፡ኰርተዋልና፥ዐንገታቸውንም፡እያሰገጉ፡ በዐይናቸውም፡እያጣቀሱ፥ፈንጠርም፡እያሉ፥በእግራቸውም፡እያቃጨሉ፡ይኼዳሉና፥

17ስለዚህ፥ጌታ፡የጽዮንን፡ቈነዣዥት፡ዐናት፡በቡሓነት፡ይመታል፥እግዚአብሔርም፡ኀፍረተ፡ሥጋቸውን፡ ይገልጣል።

18በዚያም፡ቀን፡ጌታ፡የእግር፡አልቦውን፡ክብር፥መርበብንም፥ጨረቃ፡የሚመስለውንም፡ጌጥ፥የዦሮ፡ እንጥልጥሉንም፥

19አንባሩንም፥መሸፈኛውንም፥ቀጸላውንም፥

20ሰንሰለቱንም፥መቀነቱንም፥የሽቱውንም፡ዕቃ፥

21ዐሸን፡ክታቡንም፥የእጅና፡የአፍንጫ፡ቀለበቱንም፥

22የዓመት፡በዓልንም፡ልብስ፥መጐናጸፊያውንም፥ልግም፡በገላውንም፥ከረጢቱንም፥

23መስተዋቱንም፥ከጥሩ፡በፍታ፡የተሠራውንም፡ልብስ፥ራስ፡ማሰሪያውንም፥ዐይነ፡ርግቡንም፡ያስወግዳል።

24እንዲህም፡ይኾናል፤በሽቱ፡ፋንታ፡ግማት፥በመታጠቂያውም፡ፋንታ፡ገመድ፥ጠጕርንም፡በመንቀስ፡ ፋንታ፡ቡሓነት፥በመጐናጸፊያ፡ፋንታ፡ማቅ፥በውበትም፡ፋንታ፡ጠባሳ፡ይኾናል።

25ጕልማሳዎችሽ፡በሰይፍ፥ኀያላንሽም፡በውጊያ፡ይወድቃሉ።

26በሮቿ፡ያዝናሉ፡ያለቅሱማል፤ርሷም፡ብቻዋን፡በምድር፡ላይ፡ትቀመጣለች።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source