Skip to content
← Isaiah

Chapter 42 · Amharic

Isaiah

1እንሆ፥ደግፌ፡የያዝኹት፡ባሪያዬ፤ነፍሴ፡ደስ፡የተሠኘችበት፡ምርጤ፤በርሱ፡ላይ፡መንፈሴን፡ አድርጌያለኹ፥ርሱም፡ለአሕዛብ፡ፍርድን፡ያወጣል።

2አይጮኽም፡ቃሉንም፡አያነሣም፥ድምፁንም፡በሜዳ፡አያሰማም።

3የተቀጠቀጠን፡ሸምበቆ፡አይሰብርም፥የሚጤስንም፡ክር፡አያጠፋም፤በእውነት፡ፍርድን፡ያወጣል።

4በምድርም፡ፍርድን፡እስኪያደርግ፡ድረስ፡ይበራል፡እንጂ፡አይጠፋም፤አሕዛብም፡በስሙ፡ይታመናሉ።

5ሰማያትን፡የፈጠረ፡የዘረጋቸውም፥ምድርንና፡በውስጧ፡ያለውን፡ያጸና፥በርሷ፡ላይ፡ለሚኖሩ፡ሕዝብ፡ እስትንፋስን፥ለሚኼዱባትም፡መንፈስን፡የሚሰጥ፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦

7እኔ፡እግዚአብሔር፡በጽድቅ፡ጠርቼኻለኹ፥እጅኽንም፡እይዛለኹ፡እጠብቅኽማለኹ፥የዕውሩንም፡ዐይን፡ ትከፍት፡ዘንድ፡የተጋዘውንም፡ከግዞት፡ቤት፡በጨለማም፡የተቀመጡትን፡ከወህኒ፡ቤት፡ታወጣ፡ዘንድ፡ ለሕዝብ፡ቃል፡ኪዳን፡ለአሕዛብም፡ብርሃን፡አድርጌ፡እሰጥኻለኹ።

8እኔ፡እግዚአብሔር፡ነኝ፤ስሜ፡ይህ፡ነው፤ክብሬን፡ለሌላ፥ምስጋናዬንም፡ለተቀረጹ፡ምስሎች፡አልሰጥም።

9እንሆ፥የቀድሞው፡ነገር፡ተፈጸመ፥ዐዲስ፡ነገርንም፡እናገራለኹ፤አስቀድሞም፡ሳይበቅል፡ርሱን፡ አስታውቃችዃለኹ።

10ወደ፡ባሕር፡የምትወርዱ፡በርሷም፡ውስጥ፡ያላችኹ፡ዅሉ፥ደሴቶችና፡በእነርሱም፡ላይ፡የምትኖሩ፡ ሆይ፥ለእግዚአብሔር፡ዐዲስ፡መዝሙር፥ከምድርም፡ዳርቻ፡ምስጋናውን፡ዘምሩ።

11ምድረ፡በዳውና፡ከተማዎቹ፡የቄዳርም፡ሰዎች፡የሚቀመጡባቸው፡መንደሮች፡ድምፃቸውን፡ያንሡ፤በሴላ፡ የሚኖሩ፡እልል፡ይበሉ፥በተራራዎችም፡ራስ፡ላይ፡ኾነው፡ይጩኹ።

12ለእግዚአብሔር፡ክብርን፡ይስጡ፥ምስጋናውንም፡በደሴቶች፡ይናገሩ።

13እግዚአብሔር፡እንደ፡ኀያል፡ይወጣል፡እንደ፡ሰልፈኛም፡ቅንአትን፡ያስነሣል፤ይጮኻል፡ድምፁንም፡ ያሰማል፡በጠላቶቹም፡ላይ፡ይበረታል።

14ከድሮ፡ዘመን፡ዠምሮ፡ዝም፡ብያለኹ፥ዝም፡ብዬም፡ታግሻለኹ፤አኹን፡ምጥ፡እንደ፡ያዛት፡ሴት፡ እጮኻለኹ፤አጠፋለኹ፡በአንድነትም፡እጨርሳለኹ።

15ተራራዎችንና፡ኰረብታዎችን፡አፈርሳለኹ፥ቡቃያዎቻቸውንም፡ዅሉ፡አደርቃለኹ፤ወንዞችንም፡ደሴቶች፡ አደርጋለኹ፥ኵሬዎችንም፡አደርቃለኹ።

16ዕውሮችንም፡በማያውቋት፡መንገድ፡አመጣቸዋለኹ፥በማያውቋትም፡ጐዳና፡እመራቸዋለኹ፤በፊታቸውም፡ ጨለማውን፡ብርሃን፡አደርጋለኹ፥ጠማማውንም፡አቀናለኹ።ይህን፡አደርግላቸዋለኹ፥አልተዋቸውምም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

17በተቀረጹትም፡ምስሎች፡የሚታመኑ፥ቀልጠው፡የተሠሩትንም፡ምስሎች፦አምላኮቻችን፡ናችኹ፡የሚሉ፡ ወደ፡ዃላቸው፡ይመለሳሉ፡ፈጽመውም፡ያፍራሉ።

18እናንተ፡ደንቈሮዎች፥ስሙ፤እናንተም፡ዕውሮች፥ታዩ፡ዘንድ፡ተመልከቱ።

19ከባሪያዬ፡በቀር፡ዕውር፡ማን፡ነው፧እንደምልከው፡መልእክተኛዬስ፡በቀር፡ደንቈሮ፡የኾነ፡ማን፡ ነው፧እንደ፡ፍጹሙ፡ወይስ፡እንደእግዚአብሔር፡ባሪያ፡ዕውር፡የኾነ፡ማን፡ነው፧

20ብዙ፡ነገርን፡ታያላችኹ፥ነገር፡ግን፥አትጠባበቁትም፤ዦሯችኹም፡ተከፍተዋል፥ነገር፡ግን፥አትሰሙም።

21እግዚአብሔር፡ስለ፡ጽድቁ፡ሕጉን፡ታላቅ፡ያደርግና፡ያከብር፡ዘንድ፡ወደደ።

22ይህ፡ግን፡የተበዘበዘና፡የተዘረፈ፡ሕዝብ፡ነው፤ዅላቸው፡በዋሻ፡ውስጥ፡ተጠምደዋል፡በግዞት፡ቤትም፡ ተሸሽገዋል፤ብዝበዛ፡ኾነዋል፡የሚያድንም፡የለም፥ምርኮም፡ኾነዋል፥ማንም፦መልሱ፡አይልም።

23ከመካከላችኹ፡ይህን፡የሚያደምጥ፥ለሚመጣውም፡ጊዜ፡የሚያደምጥና፡የሚሰማ፡ማን፡ነው፧

24ያዕቆብን፡ለማረኩ፡እስራኤልንም፡ለበዘበዙ፡ሰዎች፡የሰጠ፡ማን፡ነው፧እኛ፡የበደልነው፥እነርሱም፡ በመንገዱ፡ይኼዱ፡ዘንድ፡ያልወደዱት፡ለሕጉም፡ያልታዘዙለት፡እግዚአብሔር፡ርሱ፡አይደለምን፧

25ስለዚህ፥የቍጣውን፡መዓትና፡የሰልፉን፡ጽናት፡አፈሰሰበት፤በዙሪያም፡አነደደው፥ርሱ፡ግን፡ አላወቀም፥አቃጠለውም፡ርሱ፡ግን፡ልብ፡አላደረገም።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source