1አኹንም፡ባሪያዬ፡ያዕቆብ፡የመረጥኹኽም፡እስራኤል፡ሆይ፥ስማ።
2የፈጠረኽ፡ከማሕፀንም፡የሠራኽ፡የሚረዳኽም፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ባሪያዬ፡ያዕቆብ፡ የመረጥኹኽም፡ይሹሩን፡ሆይ፥አትፍራ።
3በተጠማ፡ላይ፡ውሃን፡በደረቅም፡መሬት፡ላይ፡ፈሳሾችን፡አፈሳ፟ለኹና፤መንፈሴን፡በዘርኽ፡ላይ፡በረከቴንም፡ በልጆችኽ፡ላይ፡አፈሳ፟ለኹ፥
4በፈሳሾችም፡አጠገብ፡እንደሚበቅሉ፡እንደ፡አሓያ፡ዛፎች፡በሣር፡መካከል፡ይበቅላሉ።
5ይህ፦እኔ፡የእግዚአብሔር፡ነኝ፡ይላል፥ያም፡በያዕቆብ፡ስም፡ይጠራል፤ይህም፦እኔ፡የእግዚአብሔር፡ ነኝ፡ብሎ፡በእጁ፡ይጽፋል፥በእስራኤልም፡የቍልምጫ፡ስም፡ይጠራል።
6የእስራኤል፡ንጉሥ፡እግዚአብሔር፥የሚቤዥም፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እኔ፡ ፊተኛ፡ነኝ፥እኔም፡ዃለኛ፡ነኝ፤ከእኔ፡ሌላም፡አምላክ፡የለም።
7እንደ፡እኔ፡ያለ፡ማን፡ነው፧ይነሣና፡ይጥራ፡ይናገርም፤ከጥንት፡የፈጠርኹትን፡ሕዝብ፡ ያዘጋጅልኝ፥የሚመጣውም፡ነገር፡ሳይደርስ፡ይንገሩኝ።
8አትፍሩ፡አትደንግጡም፤ከጥንቱ፡ዠምሬ፡አልነገርዃችኹምን፧ወይስ፡አላሳየዃችኹምን፧እናንተ፡ምስክሮቼ፡ ናችኹ።ከእኔ፡ሌላ፡አምላክ፡አለን፧ዐምባ፡የለም፤ማንንም፡አላውቅም። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
9የተቀረጸውን፡ምስል፡የሚሠሩ፡ዅሉ፡ከንቱዎች፡ናቸው፥የወደዱትም፡ነገር፡ አይረባቸውም፤ምስክሮቻቸውም፡አያዩምና፡አያውቁም፤ስለዚህ፥ያፍራሉ።
10አምላክን፡የሠራ፡ወይስ፡ለምንም፡የማይረባ፡ምስልን፡የቀረጸ፡ማን፡ነው፧
11እንሆ፥ባልንጀራዎቹ፡ዅሉ፡ያፍራሉ፥ሠራተኛዎቹም፡ከሰዎች፡ወገን፡ናቸው፤ዅላቸው፡ተሰብስበው፡ ይቁሙ፤ይፈራሉ፡በአንድነትም፡ያፍራሉ።
12ብረት፡ሠሪ፡መጥረቢያውን፡ይሠራል፥በፍምም፡ውስጥ፡ያደርገዋል፥በመዶሻም፡መቶ፟፡ቅርጽ፡ ይሰጠዋል፥በክንዱም፡ኀይል፡ይሠራዋል፥ርሱም፡ይራባል፡ይደክምማል፥ውሃም፡አይጠጣም፡ይታክትማል።
13ጠራቢውም፡ገመድ፡ይዘረጋል፡በበረቅም፡ያመለክተዋል፡በመቅረጫም፡ይቀርጸዋል፡በመለኪያም፡ ይለካዋል፤በቤትም፡ውስጥ፡ይቀመጥ፡ዘንድ፡በሰው፡አምሳልና፡በሰው፡ውበት፡ያስመስለዋል።
14የዝግባን፡ዛፎች፡ይቈርጣል፤የዞጲንና፡የኮምቦልን፡ዛፍ፡ይመርጣል፥ከዱር፡ዛፎችም፡መካከል፡ይጠነክር፡ ዘንድ፡ይተወዋል፤የጥድንም፡ዛፍ፡ይተክላል፡ዝናብም፡ያበቅለዋል።
15ለሰውም፡ማገዶ፡ይኾናል፤ከርሱም፡ወስዶ፡ይሞቃል፥አንድዶም፡እንጀራ፡ይጋግርበታል፤ከርሱም፡አምላክ፡ አበጅቶ፡ይሰግድለታል፥የተቀረጸውንም፡ምስል፡ሠርቶ፡በርሱ፡ፊት፡ይንበረከካል።
16ግማሹን፡በእሳት፡ያቃጥላል፥በዚያ፡በግማሹ፡ሥጋ፡ይበላል፥ሥጋም፡ይጠብስበትና፡ ይጠግባል፤ይሞቃልና፦ዕሠይ፡ሞቅኹ፥እሳቱን፡አይቻለኹ፡ይላል።
17የቀረውንም፡ዕንጨት፡አምላክ፡አድርጎ፡ምስል፡ይቀርጽበታል፤በፊቱም፡ተጐንብሶ፡ይሰግዳል፡ወደ፡ርሱም፡ እየጸለየ፦አምላኬ፡ነኽና፥አድነኝ፡ይላል።
18አያውቁም፥አያስቡም፤እንዳያዩ፡ዐይኖቻቸውን፥እንዳያስተውሉ፡ልቦቻቸውን፡ጨፍነዋል።
19በልቡም፡ማንም፡አያስብም፦ግማሿን፡በእሳት፡አቃጥያለኹ፥በፍሟም፡ላይ፡እንጀራን፡ ጋግሬያለኹ፥ሥጋም፡ጠብሼ፡በልቻለኹ፤የቀረውንም፡አስጸያፊ፡ነገር፡አደርጋለኹን፧ለዛፍስ፡ግንድ፡ እሰግዳለኹን፧እንዲልም፡ዕውቀትና፡ማስተዋል፡የለውም።
20ዐመድ፡ይበላል፥የተታለለ፡ልብ፡አስቶታል፥ነፍሱን፡ለማዳን፡አይችልም፥ወይም፦በቀኝ፡እጄ፡ሐሰት፡ አለ፡አይልም።
21ያዕቆብ፡ሆይ፥አንተም፡እስራኤል፥ባሪያዬ፡ነኽና፥ይህን፡ዐስብ፤እኔ፡ሠርቼኻለኹ፡አንተም፡ባሪያዬ፡ ነኽ፤እስራኤል፡ሆይ፥በእኔ፡ዘንድ፡ያልተረሳ፡ትኾናለኽ።
22መተላለፍኽን፡እንደ፡ደመና፥ኀጢአትኽንም፡እንደ፡ጭጋግ፡ደምስሻለኹ፤ተቤዥቼኻለኹና፡ወደ፡እኔ፡ ተመለስ።
23ሰማያት፡ሆይ፥እግዚአብሔር፡አድርጎታልና፥ዘምሩ፤እግዚአብሔር፡ያዕቆብን፡ተቤዥቷልና፥በእስራኤልም፡ ዘንድ፡ይከበራልና፥አንተ፡የምድር፡ጥልቅ፡ሆይ፥ጩኽ፤እናንተም፡ተራራዎች፡አንተም፡ዱር፡ባንተም፡ያለ፡ ዛፍ፡ዅሉ፥እልል፡በሉ።
24ከማሕፀን፡የሠራኽ፥የሚቤዥኽ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ዅሉን፡የፈጠርኹ፥ሰማያትን፡ለብቻዬ፡ የዘረጋኹ፡ምድርንም፡ያጸናኹ፡እግዚአብሔር፡እኔ፡ነኝ፤ከእኔ፡ጋራ፡ማን፡ነበረ፧
25የሐሰተኛዎችን፡ምልክት፡ከንቱ፡አደርጋለኹ፥ሟርተኛዎችንም፡አሳብዳለኹ፥ጥበበኛዎቹንም፡ወደ፡ዃላ፡ እመልሳለኹ፡ዕውቀታቸውንም፡ስንፍና፡አደርጋለኹ፤
26የባሪያዬን፡ቃል፡አጸናለኹ፥የመልእክተኛዎቼንም፡ምክር፡እፈጽማለኹ፤ኢየሩሳሌምን፦የሰው፡መኖሪያ፡ ትኾኛለሽ፥የይሁዳንም፡ከተማዎች።ትታነጻላችኹ፡ፍራሾቻችኹንም፡አቆማለኹ፡እላለኹ፤
27ቀላዩንም፦ደረቅ፡ኹን፥ፈሳሾችኽንም፡አደርቃለኹ፡እላለኹ፤
28ቂሮስንም፦ርሱ፡እረኛዬ፡ነው፤ርሱም፡ኢየሩሳሌምን፦ትታነጺ᎗ያለሽ፡ቤተ፡መቅደስም፡ይመሠረታል፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ብሎ፡ፈቃዴን፡ዅሉ፡ይፈጽማል፡እላለኹ።