1ደሴቶች፡ሆይ፥ስሙኝ፥እናንተም፡በሩቅ፡ያላችኹ፡አሕዛብ፥አድምጡ፤እግዚአብሔር፡ከማሕፀን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ጠርቶኛል፥ከእናቴም፡ሆድ፡ዠምሮ፡ስሜን፡አንሥቷል፤
2አፌንም፡እንደ፡ተሳለ፡ሰይፍ፡አድርጓል፥በእጁ፡ጥላ፡ሰውሮኛል፤እንደ፡ተሳለ፡ፍላጻም፡ አድርጎኛል፥በሰገባውም፡ውስጥ፡ሸሽጎኛል።
3ርሱም፦እስራኤል፡ሆይ፥አንተ፡ባሪያዬ፡ነኽ፡ባንተም፡እከበራለኹ፡አለኝ።
4እኔ፡ግን፦በከንቱ፡ደከምኹ፥ምንም፡ጥቅም፡ለሌለውና፡ለከንቱ፡ጕልበቴን፡ፈጀኹ፤ፍርዴ፡ግን፡ በእግዚአብሔር፡ዘንድ፥ዋጋዬም፡በአምላኬ፡ዘንድ፡ነው፡አልኹ።
5አኹንም፡በእግዚአብሔር፡ዐይን፡ከብሬያለኹና፥አምላኬም፡ጕልበት፡ኾኖኛልና፥ያዕቆብን፡ወደ፡ርሱ፡ እንድመልስ፡እስራኤልንም፡ወደ፡ርሱ፡እንድሰበስብ፡ባሪያ፡እኾነው፡ዘንድ፡ከማሕፀን፡ዠምሮ፡የሠራኝ፡ እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦
6ርሱም፦የያዕቆብን፡ነገዶች፡እንድታስነሣ፡ከእስራኤልም፡የዳኑትን፡እንድትመስል፡ባሪያዬ፡ትኾን፡ዘንድ፡ እጅግ፡ቀላል፡ነገር፡ነውና፥እስከምድር፡ዳር፡ድረስ፡መድኀኒት፡ትኾን፡ዘንድ፡ለአሕዛብ፡ብርሃን፡አድርጌ፡ ሰጥቼኻለኹ፡ይላል።
7የእስራኤል፡ታዳጊ፡ቅዱሱም፥እግዚአብሔር፥ሰዎች፡ለሚንቁት፡ሕዝብም፡ለሚጠላው፡ለገዢዎች፡ባሪያ፡ እንዲህ፡ይላል፦ስለ፡ታማኙ፡ስለ፡እግዚአብሔር፥ስለ፡መረጠኽም፡ስለእስራኤል፡ቅዱስ፡ነገሥታት፡አይተው፡ ይነሣሉ፥መሳፍንትም፡አይተው፡ይሰግዳሉ።
8እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በተወደደ፡ጊዜ፡ሰምቼኻለኹ፥በመድኀኒትም፡ቀን፡ ረድቼኻለኹ፤እጠብቅኽማለኹ፥ምድርንም፡ታቀና፡ዘንድ፥ውድማ፡የኾኑትንም፡ርስቶች፡ታወርስ፡ዘንድ፥
9የተጋዙትንም፦ውጡ፥በጨለማም፡የተቀመጡትን፦ተገለጡ፡ትል፡ዘንድ፥ቃል፡ኪዳን፡አድርጌ፡ለሕዝቡ፡ ሰጥቼኻለኹ።በመንገድም፡ላይ፡ይሰማራሉ፥ማሰማሪያቸውም፡በወና፡ኰረብታ፡ዅሉ፡ላይ፡ይኾናል።
10የሚራራላቸውም፡ይመራቸዋልና፥በውሃም፡ምንጮች፡በኩል፡ ይነዳቸዋልና፥አይራቡም፥አይጠሙም፥ትኵሳት፡ወይም፡ፀሓይ፡አይጐዳቸውም።
11ተራራዎቼንም፡ዅሉ፡መንገድ፡አደርጋለኹ፥ጐዳኖቼም፡ከፍ፡ከፍ፡ይላሉ።
12እንሆ፥እነዚህ፡ከሩቅ፥እንሆም፥እነዚህ፡ከሰሜንንና፡ከምዕራብ፥እነዚህም፡ከሢኒም፡አገር፡ይመጣሉ።
13እግዚአብሔር፡ሕዝቡን፡አጽናንቷልና፥ለችግረኛዎቹም፡ራርቷልና፥ሰማያት፡ሆይ፥ዘምሩ፥ምድር፡ ሆይ፥ደስ፡ይበልሽ፡ተራራዎችም፡ሆይ፥እልል፡በሉ።
14ጽዮን፡ግን፦እግዚአብሔር፡ትቶኛል፡ጌታም፡ረስቶኛል፡አለች።
15በእውኑ፡ሴት፡ከማሕፀኗ፡ለተወለደው፡ልጅ፡እስከማትራራ፡ድረስ፡ሕፃኗን፡ትረሳ፡ዘንድ፡ ትችላለችን፧አዎን፥ርሷ፡ትረሳ፡ይኾናል፥እኔ፡ግን፡አልረሳሽም።
16እንሆ፥እኔ፡በእጄ፡መጻፍ፡ቀርጬሻለኹ፥ቅጥሮችሽም፡ዅልጊዜ፡በፊቴ፡አሉ።
17ልጆችሽ፡ይፈጥናሉ፤ያፈረሱሽና፡ያወደሙሽ፡ከአንቺ፡ዘንድ፡ይወጣሉ።
18ዐይንሽን፡አንሥተሽ፡በዙሪያሽ፡ተመልከቺ፤እነዚህ፡ዅሉ፡ተሰብስበው፡ወደ፡አንቺ፡ይመጣሉ።እኔ፡ ሕያው፡ነኝና፡እነዚህን፡ዅሉ፡እንደ፡ጌጥ፡ትለብሻቸዋለሽ፥እንደ፡ሙሽራም፡ትጐናጸፊአቸዋለሽ፥ይላል፡ እግዚአብሔር።
19ባድማሽና፡ውድማሽ፡ወናም፡የኾነው፡ምድርሽ፡ከሚኖሩብሽ፡የተነሣ፡ዛሬ፡ጠባብ፡ ትኾናለችና፥የዋጡሽም፡ይርቃሉና።
20የወላድ፡መካን፡ከኾንሽ፡በዃላ፡የተወለዱልሽ፡ልጆችሽ፡በዦሮሽ፦ስፍራ፡ጠቦ፟ኛልና፥እቀመጥ፡ዘንድ፡ ቦታ፡አስፊልኝ፡ይላሉ።
21አንቺም፡በልብሽ፥የወላድ፡መካን፡ኾኛለኹና፥እኔም፡ብቻዬን፡ተሰድጃለኹና፡ተቅበዝብዣለኹምና፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እነዚህን፡ማን፡ወለደልኝ፧እነዚህንስ፡ማን፡አሳደጋቸው፧እንሆ፥ብቻዬን፡ቀርቼ፡ነበር፤እነዚህስ፡ወዴት፡ ነበሩ፧ትያለሽ።
22ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥እጄን፡ወደ፡አሕዛብ፡አነሣለኹ፥ዓላማዬንም፡ወደ፡ ወገኖች፡አቆማለኹ፤ወንዶች፡ልጆችሽንም፡በብብታቸው፡ያመጧቸዋል፥ሴቶች፡ልጆችሽንም፡በጫንቃቸው፡ ላይ፡ይሸከሟቸዋል።
23ነገሥታትም፡አሳዳጊ፡አባቶችሽ፡ይኾናሉ፥እቴጌዎቻቸውም፡ሞግዚቶችሽ፡ይኾናሉ፤ግንባራቸውንም፡ወደ፡ ምድር፡ዝቅ፡አድርገው፡ይሰግዱልሻል፥የእግርሽንም፡ትቢያ፡ይልሳሉ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡ ታውቂያለሽ፥እኔንም፡በመተማመን፡የሚጠባበቁ፡አያፍሩም።
24በእውኑ፡ብዝበዛ፡ከኀያል፡እጅ፡ይወሰዳልን፧ወይስ፡የጨካኙ፡ምርኮኛዎች፡ያመልጣሉን፧
25እግዚአብሔር፡ግን፡እንዲህ፡ይላል፦በኀያላን፡የተማረኩ፡ይወሰዳሉ፥የጨካኞችም፡ብዝበዛ፡ ያመልጣል፤ከአንቺ፡ጋራ፡የሚጣሉትን፡እጣላቸዋለኹ፥ልጆችሽንም፡አድናለኹ።
26አስጨናቂዎችሽንም፡ሥጋቸውን፡አስበላቸዋለኹ፥እንደ፡ጣፋጭም፡ወይን፡ጠጅ፡ደማቸውን፡ጠጥተው፡ ይሰክራሉ፤ሥጋ፡ለባሹም፡ዅሉ፡እኔ፡እግዚአብሔር፡መድኀኒትሽና፡ታዳጊሽ፥የያዕቆብ፡ኀያል፡እንደ፡ኾንኹ፡ ያውቃል።