1እናንተ፡ጽድቅን፡የምትከተሉ፡እግዚአብሔርንም፡የምትሹ፥ስሙኝ፤ከርሱ፡የተቈረጣችኹበትን፡ድንጋይ፡ ከርሱም፡የተቈፈራችኹበትን፡ጕድጓድ፡ተመልከቱ።
2ወደ፡አባታችኹ፡ወደ፡አብርሃም፥ወደ፡ወለደቻችኹም፡ወደ፡ሳራ፡ተመልከቱ፤አንድ፡ብቻውን፡በኾነ፡ ጊዜ፡ጠራኹት፥ባረክኹትም፥አበዛኹትም።
3እግዚአብሔርም፡ጽዮንን፡ያጽናናል፤በርሷም፡ባድማ፡የኾነውን፡ዅሉ፡ያጽናናል፥ምድረ፡በዳዋንም፡እንደ፡ ዔዴን፡በረሓዋንም፡እንደእግዚአብሔር፡ገነት፡ያደርጋል፤ደስታና፡ተድላ፡ምስጋናና፡የዝማሬ፡ድምፅ፡ ይገኝበታል።
4ወገኔ፡ሆይ፥አድምጠኝ፤ሕዝቤ፡ሆይ፥ስማኝ፤ሕግ፡ከእኔ፡ይወጣልና፥ፍርዴም፡ለአሕዛብ፡ብርሃን፡ ይኾናልና።
5ጽድቄ፡ፈጥኖ፡ቀርቧል፥ማዳኔም፡ወጥቷል፥ክንዴም፡በአሕዛብ፡ላይ፡ይፈርዳል፤ደሴቶች፡እኔን፡ በመተማመን፡ይጠባበቃሉ፥በክንዴም፡ይታመናሉ።
6ዐይናችኹን፡ወደ፡ሰማይ፡አንሡ፥ወደ፡ታችም፡ወደ፡ምድር፡ተመልከቱ፤ሰማያት፡እንደ፡ጢስ፡በነ፟ው፡ ይጠፋሉ፥ምድርም፡እንደ፡ልብስ፡ታረጃለች፥የሚኖሩባትም፡እንዲሁ፡ይሞታሉ፤ማዳኔ፡ግን፡ለዘለዓለም፡ ይኾናል፥ጽድቄም፡አይፈርስም።
7ጽድቅን፡የምታውቁ፡ሕጌም፡በልባችኹ፡ያለ፡ሕዝብ፡ሆይ፥ስሙኝ፤የሰውን፡ተግዳሮት፡ አትፍሩ፥በስድባቸውም፡አትደንግጡ።
8እንደ፡ልብስም፡ብል፡ይበላቸዋል፥እንደ፡በግ፡ጠጕርም፡ትል፡ይበላቸዋል፤ጽድቄ፡ግን፡ለዘለዓለም፡ ማዳኔም፡ለትውልድ፡ዅሉ፡ይኾናል።
9የእግዚአብሔር፡ክንድ፡ሆይ፥ተነሥ፥ተነሥ፥ኀይልንም፡ልበስ፤በቀድሞው፡ወራትና፡በጥንቱ፡ዘመን፡ በነበረው፡ትውልድ፡እንደኾነው፡ተነሥ።ረዓብን፡የቈራረጥኽ፡ዘንዶውንም፡የወጋኽ፡አንተ፡አይደለኽምን፧
10ባሕሩንና፡የታላቁን፡ጥልቅ፡ውሃ፡ያደረቅኸው፥የዳኑትም፡ይሻገሩ፡ዘንድ፡ጠሊቁን፡ባሕር፡መንገድ፡ ያደረግኽ፡አንተ፡አይደለኽምን፧
11እግዚአብሔርም፡የተቤዣቸው፡ይመለሳሉ፡ወደ፡ጽዮንም፡ይመጣሉ፤የዘለዓለምም፡ደስታ፡በራሳቸው፡ላይ፡ ይኾናል፤ደስታንና፡ተድላን፡ያገኛሉ፥ሐዘንና፡ልቅሶም፡ይሸሻል።
12የማጽናናችኹ፡እኔ፡ነኝ፥እኔ፡ነኝ፤የሚሞተውን፡ሰው፡እንደ፡ሣርም፡የሚጠወልገውን፡የሰው፡ልጅ፡ ትፈራ፡ዘንድ፡አንተ፡ማን፡ነኽ፧
13ሰማያትንም፡የዘረጋው፡ምድርንም፡የመሠረተውን፡ፈጣሪኽን፡እግዚአብሔርን፡ረስተኻል፤ያጠፋ፡ዘንድ፡ ባዘጋጀ፡ጊዜ፡ካስጨናቂው፡ቍጣ፡የተነሣ፡ዅልጊዜ፡ቀኑን፡ዅሉ፡ፈርተኻል፤የአስጨናቂው፡ቍጣ፡የት፡አለ፧
14ምርኮኛ፡ፈጥኖ፡ይፈታል፤አይሞትም፡ወደ፡ጕድጓድም፡አይወርድም፥እንጀራም፡አይጐድልበትም።
15ሞገዱም፡እንዲተም፟፡ባሕርን፡የማናውጥ፡አምላክኽ፡እግዚአብሔር፡እኔ፡ነኝ፥ስሜም፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር፡ነው።
16ሰማያትን፡እዘረጋ፡ዘንድ፡ምድርንም፡እመሠርት፡ዘንድ፥ጽዮንንም፦አንቺ፡ሕዝቤ፡ነሽ፡እል፡ዘንድ፡ ቃሌን፡በአፍኽ፡አድርጌያለኹ፥በእጄም፡ጥላ፡ጋርጄኻለኹ።
17ከእግዚአብሔር፡እጅ፡የቍጣውን፡ጽዋ፡የጠጣሽ፡ኢየሩሳሌም፡ሆይ፥ንቂ፥ንቂ፥ቁሚ፤የሚያንገደግድን፡ ዋንጫ፡ጠጥተሻል፡ጨልጠሽውማል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
18ከወለደቻቸው፡ልጆች፡ዅሉ፡የሚመራት፡የለም፥ካሳደገቻቸውም፡ልጆች፡ዅሉ፡እጇን፡የሚይዝ፡የለም።
19እነዚህ፡ኹለት፡ነገሮች፡ኾነውብሻል፥ማንስ፡ያስተዛዝንሻል፧መፈታትና፡ጥፋት፡ራብና፡ሰይፍ፡ ናቸው፤እንዴትስ፡አድርጌ፡አጽናናሻለኹ፧
20ልጆችሽ፡ዝለዋል፤በወጥመድ፡እንደተያዘ፡ሚዳቋ፡በአደባባይ፡ዅሉ፡ራስ፡ላይ፡ ተኝተዋል፤በእግዚአብሔር፡ቍጣና፡በአምላክሽ፡ተግሣጽ፡ተሞልተዋል።
21ስለዚህም፡ያለወይን፡ጠጅ፡የሰከርሽ፡አንቺ፡ችግረኛ፥ይህን፡ስሚ፤
22ስለ፡ወገኑ፡የሚሟገት፡አምላክሽ፡ጌታሽ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥የሚያንገደግድን፡ጽዋ፡ የቍጣዬንም፡ዋንጫ፡ከእጅሽ፡ወስጃለኹ፤ደግመሽም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አትጠጪውም።
23ነፍስሽንም፦እንሻገር፡ዘንድ፡ዝቅ፡በዪ፡በሚሏት፡በአስጨናቂዎችሽ፡እጅ፡አኖረዋለኹ፤ዠርባሽንም፡ ለሚሻገሩት፡እንደ፡መሬትና፡እንደ፡መንገድ፡አደረግሽላቸው።