1ጽዮን፡ሆይ፥ተነሺ፥ተነሺ፥ኀይልሽን፡ልበሺ፤ቅድስቲቱ፡ከተማ፡ኢየሩሳሌም፡ሆይ፥ያልተገረዘና፡ርኩስ፡ ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አይገባብሽምና፡ጌጠኛ፡ልብስሽን፡ልበሺ።
2ኢየሩሳሌም፡ሆይ፥ትቢያን፡አራግፊ፤ተነሺ፥ተቀመጪ፤ምርኮኛዪቱ፡የጽዮን፡ልጅ፡ሆይ፥የዐንገትሽን፡ እስራት፡ፍቺ።
3እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በከንቱ፡ተሽጣችኹ፡ነበር፥ያለገንዘብም፡ትቤዣላችኹ።
4ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ወገኔ፡በዚያ፡እንግዳ፡ኾኖ፡ይቀመጥ፡ዘንድ፡አስቀድሞ፡ወደ፡ ግብጽ፡ወረደ፥አሶርም፡ያለምክንያት፡በደለው።
5ወገኔ፡በከንቱ፡ተወስዷልና፥አኹን፡ከዚህ፡ምን፡አለኝ፧ይላል፡እግዚአብሔር፤የሚገዟቸው፡ ይጮኻሉ፥ይላል፡እግዚአብሔር፥ስሜም፡ዅልጊዜ፡ቀኑን፡ዅሉ፡ይሰደባል።
6ስለዚህ፥ወገኔ፡ስሜን፡ያውቃል፥ስለዚህም፡የምናገር፡እኔ፡እንደ፡ኾንኹ፡በዚያ፡ቀን፡ ያውቃሉ፤እንሆ፥እኔ፡ነኝ።
7የምሥራች፡የሚናገር፥ሰላምንም፡የሚያወራ፥የመልካምንም፡ወሬ፡የምሥራች፡የሚናገር፥መድኀኒትንም፡ የሚያወራ፥ጽዮንንም፦አምላክሽ፡ነግሧል፡የሚል፡ሰው፡እግሩ፡በተራራዎች፡ላይ፡እጅግ፡ያማረ፡ነው።
8እንሆ፥ጕበኛዎችሽ፡ጮኸዋል፤እግዚአብሔር፡ወደ፡ጽዮን፡በተመለሰ፡ጊዜ፡ዐይን፡በዐይን፡ይተያያሉና፡ ድምፃቸውን፡ያነሣሉ፥በአንድነትም፡ይዘምራሉ።
9እናንተ፡የኢየሩሳሌም፡ፍርስራሾች፡ሆይ፥እግዚአብሔር፡ሕዝቡን፡አጽናንቷልና፥ኢየሩሳሌምንም፡ ታድጓልና፥ደስ፡ይበላችኹ፥በአንድነትም፡ዘምሩ።
10እግዚአብሔር፡የተቀደሰውን፡ክንዱን፡በአሕዛብ፡ዅሉ፡ፊት፡ገልጧል፥በምድር፡ዳርቻ፡የሚኖሩትም፡ዅሉ፡ የአምላካችንን፡መድኀኒት፡ያያሉ።
11እናንተ፡የእግዚአብሔር፡ዕቃ፡የምትሸከሙ፡ሆይ፥እልፍ፡በሉ፥እልፍ፡በሉ፥ከዚያ፡ውጡ፥ርኩስን፡ነገር፡ አትንኩ፥ከመካከሏ፡ውጡ፥ንጹሓን፡ኹኑ።
12እግዚአብሔር፡ይቀድማችዃልና፥የእስራኤልም፡አምላክ፡ይከተላችዃልና፥በችኰላ፡አትወጡም፡ በመኰብለልም፡አትኼዱም።
13እንሆ፥ባሪያዬ፡በማስተዋል፡ያደርጋል፤ይከብራል፡ከፍ፡ከፍም፡ይላል፥እጅግ፡ታላቅም፡ይኾናል።
14ፊቱ፡ከሰዎች፡ዅሉ፡ይልቅ፥መልኩም፡ከሰዎች፡ልጆች፡ይልቅ፡ተጐሳቍሏልና፥ብዙ፡ሰዎች፡ስለ፡አንተ፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እንደ፡ተደነቁ፥እንዲሁ፡ብዙ፡አሕዛብን፡ያስደንቃል፤
15ያልተነገረላቸውንም፡ያያሉና፥ያልሰሙትንም፡ያስተውላሉና፡ነገሥታት፡ስለ፡ርሱ፡አፋቸውን፡ይዘጋሉ።