1እንሆ፥የእግዚአብሔር፡እጅ፡ከማዳን፡አላጠረችም፥ዦሮውም፡ከመስማት፡አልደነቈረችም፤
2ነገር፡ግን፥በደላችኹ፡በእናንተና፡በአምላካችኹ፡መካከል፡ለይታለች፥እንዳይሰማም፡ኀጢአታችኹ፡ፊቱን፡ ከእናንተ፡ሰውሮታል።
3እጃችኹ፡በደም፡ጣታችኹም፡በበደል፡ረክሳለች፥ከንፈራችኹም፡ሐሰትን፡ተናግሯል፥ምላሳችኹም፡ ኀጢአትን፡አሰምቷል።
4በጽድቅ፡የሚጠራ፡በእውነትም፡የሚፈርድ፡የለም፤በምናምንቴ፡ነገር፡ታምነዋል፡ሐሰትንም፡ ተናግረዋል፤ጕዳትን፡ፀንሰዋል፡በደልንም፡ወልደዋል፤
5የእባብን፡ዕንቍላል፡ቀፈቀፉ፥የሸረሪትንም፡ድር፡አደሩ፟፤ዕንቍላላቸውንም፡የሚበላ፡ሰው፡ ይሞታል፥ዕንቍላሉም፡ሲሰበር፡እፍኝት፡ይወጣል።
6ድሮቻቸውም፡ልብስ፡አይኾኑላቸውም፥በሥራቸውም፡አይሸፈኑም፤ሥራቸውም፡የበደል፡ሥራ፡ ነው፥የግፍም፡ሥራ፡በእጃቸው፡ነው።
7እግሮቻቸው፡ወደ፡ክፋት፡ይሮጣሉ፥ንጹሑን፡ደም፡ለማፍሰስ፡ይፈጥናሉ፤ዐሳባቸው፡የኀጢአት፡ዐሳብ፡ ነው፥ጕስቍልናና፡ቅጥቃጤ፡በመንገዳቸው፡አለ።
8የሰላምን፡መንገድ፡አያውቁም፥በአካኼዳቸውም፡ፍርድ፡የለም፤መንገዳቸውን፡አጣ፟መ፟ዋል፥የሚኼድባትም፡ ዅሉ፡ሰላምን፡አያውቅም።
9ስለዚህ፥ፍርድ፡ከእኛ፡ዘንድ፡ርቋል፥ጽድቅም፡አላገኘንም፤ብርሃንን፡በተስፋ፡እንጠባበቅ፡ ነበር፥እንሆም፥ጨለማ፡ኾነ፤ጸዳልን፡በተስፋ፡እንጠባበቅ፡ነበር፥ነገር፡ግን፥በጨለማ፡ኼድን።
10እንደ፡ዕውሮች፡ወደ፡ቅጥሩ፡ተርመሰመስን፥ዐይን፡እንደሌላቸው፡ተርመሰመስን፤በቀትር፡ጊዜ፡ በድግዝግዝታ፡እንዳለ፡ሰው፡ተሰናከልን፥እንደ፡ሙታን፡በጨለማ፡ስፍራ፡ነን።
11ዅላችን፡እንደ፡ድቦች፡እንጮኻለን፥እንደ፡ርግብ፡እንለቃቀሳለን፤ፍርድን፡በተስፋ፡እንጠባበቅ፡ ነበር፥ርሱም፡የለም፤መዳንም፡ከእኛ፡ዘንድ፡ርቋል።
12ዐመፃችን፡ባንተ፡ፊት፡በዝቷልና፥ኀጢአታችን፡መስክሮብናልና፥ዐመፃችን፡ከእኛ፡ጋራ፡ ነውና፥በደላችንን፡እናውቃለንና።
13ዐምፀናል፥ሐሰትን፡ተናግረናል፥አምላካችንንም፡ከመከተል፡ተመልሰናል፤ግፍንና፡ዐመፅንም፡ ተናግረናል፥የኀጢአት፡ቃልንም፡ፀንሰን፡ከልብ፡አውጥተናል።
14ፍርድም፡ወደ፡ዃላ፡ተመልሷል፥ጽድቅም፡በሩቅ፡ቆሟል፤እውነትም፡በአደባባይ፡ላይ፡ ወድቋልና፥ቅንነትም፡ሊገባ፡አልቻለምና።
15እውነትም፡ታጥቷል፥ከክፋትም፡የራቀ፡ሰው፡ለብዝበዛ፡ኾኗል። እግዚአብሔርም፡አየ፥ፍርድም፡ስለሌለ፡ተከፋ።
16ሰውም፡እንደሌለ፡አየ፥ወደ፡ርሱ፡የሚማልድ፡እንደሌለ፡ተረዳ፥ተደነቀም፤ስለዚህ፥የገዛ፡ክንዱ፡ መድኀኒት፡አመጣ፟ለት፥ጽድቁም፡አገዘው።
17ጽድቅንም፡እንደ፡ጥሩር፡ለበሰ፥በራሱም፡ላይ፡የማዳንን፡ራስ፡ቍር፡አደረገ፤የበቀልንም፡ልብስ፡ ለበሰ፥በቅንአትም፡መጐናጸፊያ፡ተጐናጸፈ።
18እንደ፡ሥራቸው፡መጠን፡እንዲሁ፡ቍጣን፡ለባላጋራዎቹ፥ፍዳንም፡ለጠላቶቹ፡ይከፍላል፤ለደሴቶችም፡ ፍዳቸውን፡ይከፍላል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
19ርሱ፡የእግዚአብሔር፡ነፋስ፡እንደሚነዳው፡እንደ፡ጐርፍ፡ፈሳሽ፡ይመጣልና፥በምዕራብ፡ያሉት፡ የእግዚአብሔርን፡ስም፥በፀሓይ፡መውጫም፡ያሉት፡ክብሩን፡ይፈራሉ።
20ለጽዮን፡ታዳጊ፡ይመጣል፥በያዕቆብም፡ዘንድ፡ከኀጢአት፡ለሚርቁ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
21ከርሱ፡ጋራ፡ያለው፡ቃል፡ኪዳኔ፡ይህ፡ነው፡ይላል፡እግዚአብሔር፥ባንተ፡ላይ፡ያለው፡መንፈሴ፡ በአፍኽም፡ውስጥ፡ያደረግኹት፡ቃሌ፡ከዛሬ፡ዠምሮ፡እስከ፡ዘለዓለም፡ድረስ፡ከአፍኽ፡ከዘርኽም፡አፍ፡ከዘር፡ ዘርኽም፡አፍ፡አያልፍም፥ይላል፡እግዚአብሔር።