1ብርሃንሽ፡መጥቷልና፥የእግዚአብሔርም፡ክብር፡ወጥቶልሻልና፥ተነሺ፥አብሪ።
2እንሆ፥ጨለማ፡ምድርን፡ድቅድቅ፡ጨለማም፡አሕዛብን፡ይሸፍናል፤ነገር፡ግን፥ባንቺ፡ላይ፡እግዚአብሔር፡ ይወጣል፡ክብሩም፡ባንቺ፡ላይ፡ይታያል፤
3አሕዛብም፡ወደ፡ብርሃንሽ፡ነገሥታትም፡ወደ፡መውጫሽ፡ጸዳል፡ይመጣሉ።
4ዐይኖችሽን፡አንሥተሽ፡በዙሪያሽ፡ተመልከቺ፤እነዚህ፡ዅሉ፡ተሰብስበው፡ወደ፡አንቺ፡ይመጣሉ፤ወንዶች፡ ልጆችሽ፡ከሩቅ፡ይመጣሉ፥ሴቶች፡ልጆችሽንም፡በጫንቃ፡ላይ፡ይሸከሟቸዋል።
5በዚያን፡ጊዜ፡የባሕሩ፡በረከት፡ወደ፡አንቺ፡ስለሚመለስ፥የአሕዛብም፡ብልጥግና፡ወደ፡አንቺ፡ ስለሚመጣ፥አይተሽ፡ደስ፡ይልሻል፥ልብሽም፡ይደነቃል፡ይሰፋማል።
6የግመሎች፡ብዛት፥የምድያምና፡የጌፌር፡ግመሎች፥ይሸፍኑሻል፤ዅሉ፡ከሳባ፡ይመጣሉ፥ወርቅንና፡ ዕጣንን፡ያመጣሉ፡የእግዚአብሔርንም፡ምስጋና፡ያወራሉ።
7የቄዳር፡መንጋዎች፡ዅሉ፡ወደ፡አንቺ፡ይሰበሰባሉ፡የነባዮትም፡አውራ፡በጎች፡ያገለግሉሻል፤እኔን፡ደስ፡ ሊያሠኙ፡በመሠዊያዬ፡ላይ፡ይወጣሉ፥የክብሬንም፡ቤት፡አከብራለኹ።
8ርግቦች፡ወደ፡ቤታቸው፡እንደሚበሩ፟፥እነዚህ፡እንደ፡ደመና፡የሚበሩ፟፡እነማን፡ናቸው፧
9ርሱ፡አክብሮሻልና፥ለአምላክሽ፡ለእግዚአብሔር፡ስምና፡ለእስራኤል፡ቅዱስ፡ልጆችሽን፡ከሩቅ፡ከነርሱ፡ ጋራም፡ብራቸውንና፡ወርቃቸውን፡ያመጡ፡ዘንድ፡ደሴቶች፡የተርሴስ፡መርከቦችም፡አስቀድመው፡ ይጠባበቁኛል።
10በቍጣዬ፡ቀሥፌ፡በፍቅሬ፡ምሬሻለኹና፡መጻተኛዎች፡ቅጥርሽን፡ይሠራሉ፥ነገሥታታቸውም፡ያገለግሉሻል።
11በሮችሽም፡ዅልጊዜ፡ይከፈታሉ፤ሰዎች፡የአሕዛብን፡ብልጥግና፡የተማረኩትንም፡ነገሥታታቸውን፡ወደ፡ አንቺ፡ያመጡ፡ዘንድ፡ሌሊትና፡ቀን፡አይዘጉም።
12ለአንቺም፡የማይገዛ፡ሕዝብና፡መንግሥት፡ይጠፋል፥እነዚያ፡አሕዛብም፡ፈጽመው፡ይጠፋሉ።
13የመቅደሴንም፡ስፍራ፡ያስጌጡ፡ዘንድ፡የሊባኖስ፡ክብር፥ጥዱና፡አስታው፡ባርሰነቱም፥ወደ፡አንቺ፡ ይመጣሉ፥የእግሬንም፡ስፍራ፡አከብራለኹ።
14የአስጨናቂዎችሽም፡ልጆች፡ዐንገታቸውን፡ደፍተው፡ወደ፡አንቺ፡ይመጣሉ፥የናቁሽም፡ዅሉ፡ወደእግርሽ፡ ጫማ፡ይሰግዳሉ፤የእግዚአብሔርም፡ከተማ፥የእስራኤል፡ቅዱስ፡የኾንሽ፡ጽዮን፡ይሉሻል።
15ከሰውም፡ማንም፡እስከማያልፍብሽ፡ድረስ፡የተተውሽና፡የተጠላሽ፡ነበርሽ፤ነገር፡ግን፥የዘለዓለም፡ ትምክሕትና፡የልጅ፡ልጅ፡ደስታ፡አደርግሻለኹ።
16የአሕዛብንም፡ወተት፡ትጠጫለሽ፡የነገሥታትንም፡ጡት፡ትጠቢያለሽ፤እኔም፡እግዚአብሔር፡የያዕቆብ፡ ኀይል፥መድኀኒትሽና፡ታዳጊሽ፡እንደ፡ኾንኹ፡ታውቂያለሽ።
17በናስ፡ፋንታ፡ወርቅን፥በብረትም፡ፋንታ፡ብርን፥በዕንጨትም፡ፋንታ፡ናስን፥በድንጋይም፡ፋንታ፡ብረትን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org አመጣለኹ።አለቃዎችሽንም፡ሰላም፥የበላይ፡ገዢዎችሽንም፡ጽድቅ፡አደርጋለኹ፤
18ከዚያ፡በዃላ፡በምድርሽ፡ውስጥ፡ግፍ፥በዳርቻሽም፡ውስጥ፡ጕስቍልናና፡ቅጥቃጤ፡አይሰማም፤ቅጥርሽን፡ መዳን፡በሮችሽንም፡ምስጋና፡ብለሽ፡ትጠሪያለሽ፡
19ከዚያ፡በዃላ፡እግዚአብሔር፡የዘለዓለም፡ብርሃንሽ፥አምላክሽም፡ክብርሽ፡ይኾናልና፥ፀሓይ፡በቀን፡ብርሃን፡ አይኾንልሽም፥የጨረቃም፡ብርሃን፡በሌሊት፡አይበራልሽም።
20እግዚአብሔር፡የዘለዓለም፡ብርሃንሽ፡ይኾናልና፥የልቅሶሽም፡ወራት፡ታልቃለችና፡ፀሓይሽ፡ከዚያ፡በዃላ፡ አትጠልቅም፡ጨረቃሽም፡አይቋረጥም።
21ሕዝብሽም፡ዅሉ፡ጻድቃን፡ይኾናሉ፤እኔም፡እከብር፡ዘንድ፡የአታክልቴን፡ቡቃያ፥የእጄ፡ሥራ፡የምትኾን፡ ምድሪቱንም፡ለዘለዓለም፡ይወርሳሉ።
22ታናሹ፡ለሺሕ፡የዅሉም፡ታናሹ፡ለብርቱ፡ሕዝብ፡ይኾናል፤እኔ፡እግዚአብሔር፡በዘመኑ፡ይህን፡ አፋጥነዋለኹ።