1ላልጠየቁኝ፡ተገለጥኹ፥ላልፈለጉኝም፡ተገኘኹ፤በስሜም፡ያልተጠራውን፡ሕዝብ፦እንሆኝ፥እንሆኝ፡ አልኹት።
2መልካም፡ባልኾነው፡መንገድ፥ዐሳባቸውን፡እየተከተሉ፥ወደሚኼዱ፡ወደ፡ዐመፀኛ፡ሕዝብ፡ቀኑን፡ዅሉ፡ እጆቼን፡ዘረጋኹ።
3ይህ፡ሕዝብ፡ዘወትር፡የሚያስቈጡኝ፡ናቸው፤እነርሱ፡በአትክልት፡ውስጥ፡የሚሠዉ፡በጡብም፡ላይ፡ የሚያጥኑ፥
4በመቃብርም፡መካከል፡የሚቀመጡ፥በስውርም፡ስፍራ፡የሚያድሩ፥የዕሪያ፡ሥጋም፡የሚበሉ፡ ናቸው።የረከሰው፡መረቅ፡በዕቃቸው፡ውስጥ፡አለ።
5እነርሱም፦ለራስኽ፡ቁም፥እኔ፡ከአንተ፡ይልቅ፡ቅዱስ፡ነኝና፡ወደ፡እኔ፡አትቅረብ፡ይላሉ፤እነዚህ፡ በአፍንጫዬ፡ዘንድ፡ጢስ፡ቀኑንም፡ዅሉ፡የምትነድ፟፡እሳት፡ናቸው።
6እንሆ፥በፊቴ፡ተጽፏል፦ኀጢአታችኹና፡የአባቶቻችኹን፡ኀጢአት፡ባንድ፡ላይ፡ወደ፡ብብታቸው፡ፍዳ፡ አድርጌ፡እመልሳለኹ፡እንጂ፡ዝም፡አልልም፥ይላል፡እግዚአብሔር፤
7በተራራዎችም፡ላይ፡ስላጠኑ፥በኰረብታዎችም፡ላይ፡ስለ፡ሰደቡኝ፥ስለዚህ፡አስቀድመው፡የሠሩትን፡ ሥራቸውን፡በብብታቸው፡እሰፍራለኹ።
8እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ወይን፡በዘለላው፡በተገኘች፡ጊዜ፦በረከት፡በርሷ፡ላይ፡አለና፡አታጥፉት፡ እንደሚባለው፥ዅሉን፡እንዳላጠፉ፡ስለ፡ባሪያዎቼ፡እንዲሁ፡አደርጋለኹ።
9ከያዕቆብ፡ዘርን፡ከይሁዳም፡ተራራዎቼን፡የሚወርሰውን፡አወጣለኹ፤እኔም፡የመረጥዃቸው፡ ይወርሷታል፥ባሪያዎቼም፡በዚያ፡ይኖራሉ።
10ሳሮንም፡የበጎች፡ማሰማሪያ፥የዐኮርም፡ሸለቆ፡የላሞች፡መመሰጊያ፡ለፈልጉኝ፡ሕዝቤ፡ይኾናል።
11እናንተን፡ግን፡እግዚአብሔርን፡የተዋችኹትን፥ቅዱሱንም፡ተራራዬን፡የረሳችኹትን፥ጕድ፡ለተባለ፡ ጣዖትም፡ማእድ፡ያዘጋጃችኹትን፥ዕድል፡ለተባለ፡ጣዖትም፡የወይን፡ጠጅ፡ለመጠጥ፡ቍርባን፡የቀዳችኹትን፥
12ዕድላችኹን፡ለሰይፍ፡አደርገዋለኹ፥ዅላችኹም፡ለመታረድ፡ትጐነበሳላችኹ፤በፊቴም፡ክፉ፡ነገርን፡ አደረጋችኹ፥ያልወደድኹትንም፡መረጣችኹ፡እንጂ፡በጠራኹ፡ጊዜ፡አልመለሳችኹልኝምና፥በተናገርኹም፡ጊዜ፡ አልሰማችኹኝምና።
13ስለዚህ፥ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥ባሪያዎቼ፡ይበላሉ፥እናንተ፡ግን፡ ትራባላችኹ፤እንሆ፥ባሪያዎቼ፡ይጠጣሉ፡እናንተ፡ግን፡ትጠማላችኹ፤እንሆ፥ባሪያዎቼ፡ደስ፡ይላቸዋል፡ እናንተ፡ግን፡ታፍራላችኹ፤
14እንሆ፥ባሪያዎቼ፡ከልባቸው፡ደስታ፡የተነሣ፡ይዘምራሉ፥እናንተ፡ግን፡ከልባችኹ፡ሐዘን፡የተነሣ፡ ትጮኻላችኹ፥መንፈሳችኹም፡ስለ፡ተሰበረ፡ወዮ፡ትላላችኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
15ስማችኹንም፡ለተመረጡት፡ሕዝቤ፡ርግማን፡አድርጋችኹ፡ትተዋላችኹ፥ጌታ፡እግዚአብሔርም፡ ይገድላችዃል፥ባሪያዎቹንም፡በሌላ፡ስም፡ይጠራቸዋል።
16እንዲሁም፡በምድር፡ላይ፡የተባረከ፡በእውነት፡አምላክ፡ይባረካል፥በምድርም፡ላይ፡የማለ፡በእውነት፡ አምላክ፡ይምላል፤የቀድሞው፡ጭንቀት፡ተረስቷልና፥ከዐይኔም፡ተሰውሯልና።
17እንሆ፥ዐዲስ፡ሰማይና፡ዐዲስ፡ምድር፡እፈጥራለኹና፤የቀደሙትም፡አይታሰቡም፥ወደ፡ልብም፡አይገቡም።
18ነገር፡ግን፥በፈጠርኹት፡ደስ፡ይበላችኹ፡ለዘለዓለምም፡ሐሤት፡አድርጉ፤እንሆ፥ኢየሩሳሌምን፡ ለሐሤት፥ሕዝቧንም፡ለደስታ፡እፈጥራለኹና።
19እኔም፡በኢየሩሳሌም፡ሐሤት፡አደርጋለኹ፡በሕዝቤም፡ደስ፡ይለኛል፤ከዚያም፡ወዲያ፡የልቅሶ፡ድምፅና፡ የዋይታ፡ድምፅ፡አይሰማባትም።
20ከዚያም፡ወዲያ፡ጥቂት፡ዘመን፡ብቻ፡የሚኖር፡ሕፃን፥ወይም፡ዕድሜውን፡ያልፈጸመ፡ሽማግሌ፡ አይገኝም፤ጕልማሳው፡የመቶ፡ዓመት፡ኾኖት፡ይሞታልና፥ኀጢአተኛውም፡የመቶ፡ዓመት፡ኾኖት፡የተረገመ፡ ይኾናልና።
21ቤቶችንም፡ይሠራሉ፡ይቀመጡባቸውማል፤ወይኑንም፡ይተክላሉ፡ፍሬውንም፡ይበላሉ።
22ሌላ፡እንዲቀመጥበት፡አይሠሩም፥ሌላም፡እንዲበላው፡አይተከሉም፤የሕዝቤ፡ዕድሜ፡እንደ፡ዛፍ፡ዕድሜ፡ ይኾናልና፥እኔም፡የመረጥዃቸው፡በእጃቸው፡ሥራ፡ረዥም፡ዘመን፡ደስ፡ይላቸዋልና።
23እነርሱ፡ከነልጆቻቸው፡የእግዚአብሔር፡ቡሩካን፡ዘር፡ናቸውና፥በከንቱ፡አይደክሙም፡ለጥፋትም፡ አይወልዱም።
24እንዲህም፡ይኾናል፤ሳይጠሩ፡እመልስላቸዋለኹ፥ገናም፡ሲናገሩ፡እሰማለኹ።
25ተኵላና፡ጠቦት፡በአንድነት፡ይሰማራሉ፥አንበሳም፡እንደ፡በሬ፡ገለባ፡ይበላል፥የእባብም፡መብል፡ትቢያ፡ ይኾናል።በተቀደሰው፡ተራራዬ፡ዅሉ፡አይጐዱም፥አያጠፉምም፥ይላል፡እግዚአብሔር።